በጀርመን የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረትና መፍትሄው | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 07.08.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

በጀርመን የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረትና መፍትሄው

ጀርመን በከፍተኛ ደረጃ የሰው ኃይል እጥረት ካለባቸው ሃገራት አንዷ ናት ። ይህን ችግር ለማቃለልም የፌደራል ጀርመን መንግሥት ልዩ ልዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል ። ይሁንና እነዚህ እርምጃዎች

በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የሚፈለገውን በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠነ ሰው ኃይል እጥረትን ማቃለል አልቻሉም ። ጀርመን በከፍተኛ ደረጃ የሰው ኃይል እጥረት ካለባቸው ሃገራት አንዷ ናት ። ይህን ችግር ለማቃለልም የፌደራል ጀርመን መንግሥት ልዩ ልዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል ። ይሁንና እነዚህ እርምጃዎች በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የሚፈለገውን በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠነ ሰው ኃይል እጥረትን ማቃለል አልቻሉም ። በጀርመን የስራ አጡ ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ በሚጠቀስበት በአሁኑ ወቅት ሃገሪቱ በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት እንዳለባትም ተደጋግሞ ይወሳል ። የጀርመን የሥራ ሚኒስቴር በቅርቡ ባወጣው መረጃ መሠረት ባለፈው በሐምሌ ወር ብቻ 67 ሺህ ሰዎች በስራ አጥነት ተመዝግበዋል ። ይህም በመላ ሃገሪቱ በአሁኑ ሰአት ሥራ አጥ የሆኑትን ሰዎች ቁጥር ወደ 2.876 ሚሊዮን ከፍ አድርጎታል ። በአንፃሩ ጀርመን ውስጥ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ የሥራ ገበታዎች መኖራቸው የተረጋገጠ ነው ። ሆኖም ክፍቱ የሥራ ቦታ በአዲስ ሠራተኛ እስኪያዝ ድረስ ረዘም ያለ ጊዜ መውሰዱ አይቀርም ። በዚህ ላይ በተደረገ ጥናት መሠረት አዲሱ ተቀጣሪ ክፍት ቦታ እስኪያገኝ ድረስ 74 ቀናት ይወስዳል ከአምናው ጋር ሲነፃፀር ደግሞ ዘንድሮ ይህ በ13 ቀናት ብልጫ አሳይቷል ።

ጀርመን ከውጭ ማስገባት ከምትፈልገው ባለሙያዎች መካከል መሀንዲሶች ፣ እጅግ ከፍተኛ ሥልጠና የወሰዱ የኢንፎርሜሽም ቴክኖሎጂ ምሁራን ፣ ሐኪሞች እንዲሁም አዛውንት የሚንከባከቡ ባለሞያዎች ይገኙበታል ። እጎአ እስከ 2025 ማለትም እስከ ዛሬ 13 አመት ድረስ በነዚህና በመሳሰሉት የሥራ ዘርፎች ጀርመን 3 ሚሊዮን በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠነ የሰው ኃይል ያስፈልጋታል ። ይህ የጀርመን ፍላጎት ሲሆን በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠኑ ባለሞያዎችስ በርግጥ ወደ ጀርመን መጥተው መሥራት ይፈልጋሉ ወይ ? ሌላው በዚህ ወቅት የሚያነጋግር ጉዳይ ነው ። በጀርመን እጅግ የሚፈለጉ ሙያተኞች ምንጭ ልትሆን እንደምትችል የምትታሰበው አንዷ አገር ህንድ ናት ። ይሁንና አብዛኛዎቹ ህንዶች ጀርመን መጥተው መሥራት ያን ያህል የሚስባቸው ሆኖ አልተገኘም ። ጃስሮፕ አኔጃ ህንድ መዲና ኒው ዴልሂ አቅራቢያ በሚገኘው አሚቲ ዩኒቨርስቲ ለዶክትሬት ዲግሪ ማይክሮ ባዮሎጂ እያጠናች ነው ። የ26 አመትዋ አኔጃ ጀርመንን ወደ መሳሰሉ የውጭ ሃገራት ሄዳ የመሥራት ፍላጎት የላትም ። ምክንያቷ

« የተለየ ሃገር ነው ። ከህንድ ከወጣህ ምናልባትም የሥራ ባህሉ የተለየ ይሆናል ። በማንኛውም ሌላ አገር የሥራ ባህሉ ይለያያል ። ህንድ የራሷ የሥራ ባህል አላት ። እዚህ ተመሳሳይ ሁኔታ ተመሳሲይ እድል የማገኝ ከሆነ ጀርመን ወይም ሌላ አገር መሄድ አልፈግም በሃገሬ ከቤተሰቦቼ ጋር መሆን ነው የምፈልገው ። »

ህንዶች በሙሉ የአኔጃ አይነት አስተሳሰብ የላቸውም ። ጀርመን መጥተው መሥራት የሚፈልጉ ምሁራንም አሉ ። ይሁንና የብዙ ህንዳውያን ምርጫዎች ግን ጀርመን ሳይሆን ዩናይትድ ስቴትስ ብሪታኒያ ፣ ሲንጋፖር ና ኒውዚላንድ ናቸው ። ህንዳዊቷ ሳቪታ ሜህታ እንደተናገረችው ጀርመን ህንድ ውስጥ ያን ያህል ታዋቂ አገር አይደለም ። ሃገሪቱ የህንድ ሠራተኖችን የምትፈልግ ከሆነ ህንድ ውስጥ ራስዋን ይበልጥ ማስሰተዋወቅ ይገባታል እንደ ሜሃታ።

« ጀርመን ራሷን ማስተዋወቅ አለባት ። ሌሎች አገሮች ህንድ ውስጥ የንግድ ትርዒቶችን እያዘጋጁ ወይም የባህል ልውውጥ ዝግጅቶችን አለያም የሙዚቃና የዳንስ ፌስቲቫሎችን እያዘጋጁ ራሳቸውን እያስተዋወቁ ነው ። የፊልም ፌስቲቫልም ቢሆን እንዲሁ ስለዚህ ጀርመን ሌሎችን በወዳጅነት እንድትሰብ እንደዚህ ላሉ ጉዳዮች ነው ይበልጥ ትኩረት ተሰጥቶት መሠራት ያለበት ። »

በነዚህ የሥራ መስኮች ያጋጠመውን የሰው ኃይል እጥረት ለመቋቋም ማለትም ክፍት የሥራ ቦታዎችን በባለሞያዎች ለመሙላት መንግሥት ከ 1 አመት ወዲህ የተለያዩ ጥረቶች በማድረግ ላይ ይገኛል ። የፌደራል ጀርመን መንግሥት የሥራ ሚኒስትር ኡርዙላ ፎን ዴር ላይን እንዳሉት አሁን ጀርመን ችግሩን በመፍታት ረገድ ጥሩ አቅጣጫ ላይ ትገኛለች ። በርሳቸው አባባል ባለፈው አንድ አመት በከፍትኛ ደረጃ የሠለጠኑ የውጭ ዜጎች ጀርመን እንዲሠሩና እንዲኖሩ ለሚያስችለው ብሉ ካርድ ለተባለው ህግ እንዲያመች መንግሥት የውጭ ዜጎች የትምህርትና የሥራ ምስክር ወረቀቶች በህግ ተቀባይነት እንዲያገኙ ማደረጉ ከነዚህ ጥረቶች ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው ። ባለፈው አመት መረጃ መሰረትም የሥራ አመልካች ሴቶች እንዲሁም በእድሜ ጠና ያሉት አመልካቾች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ አስደሳች ነው ። እስካሁን በከፊል ይሰሩ የነበሩ ጠና ያሉ ሰዎች ከጌዜ ወደ ጊዜ በሥራ ገበታ ላይ ከተገኙ ወይም ደግሞ ምንም ሥራ የሌላቸው ሰዎች በሙሉ የሥራ ሠአት የሚቀጠሩ ከሆነ በ 2025 ከታሰበው 3 ሚሊዮን ክፍት የሥራ ቦታ ገሚሱን ብቻ ነው መሸፈን የሚቻለው ። ጀርመን በአሁኑ ሰአት ከመቼውም በበለጠ በርካታ የውጭ ሠራተኛ ኃይል ነው እንደሚያስፈልጋት ይነገራል ።

የፌደራል ጀርመን የሰራተኛ ቀጣሬ መስሪያ ቤት በየአመቱ ከውጭ ሃገር 200 ሺህ ገደማ የሠለጠኑ ባለሞያዎች ወደ ጀርመን መግባታቸው አስፈላጊ ሆኖ ይታየዋል ።ይህ ግን በእስካሁን ሙከራ እንደታሰበው አልተሳክማ ። ለዚህ ይረዳል ተብሎ በሰፊው የታመነበት በተለይ በከፍተኛ ደረጃ ሞያቸው ተፈላጊ የሆነ የውጭ ዜጎች ጀርመን መሥራት የሚያስችላቸው ደንብ ካለፈው ሳምንት አንስቶ ሥራ ላይ ውሏል ። ይህ አማራጭ የውጭ ዜጎችን እንደሚስብ በሰፊው ታምኖበታል ። ይሁንና አሁንም ጀርመን ተፈላጊዎን የሰው ኃይል እንዳሰበችው ማግኘቷን እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም ። ምክንያቱም አንዳንድ የሥራ ሁኔታዎች አስተማማኝ አለመሆናቸው የውጭ ዜጎች ሃገራቸውን ለቀው እንዳይወጡ ሊያደርጉ ይችላሉ አኒሽ ካና ኒውዴልሂ ህንድ የሚገኘው ABC የተባለው አማካሪ ድርጅት ባልደረባ ነው ። የውጭ ዜጎች ለሥራ አገራቸውን ለቀው ከማይወጡበት ምክንያት አንዱ ይህ ነው ነው ይላል ሆኖም በርሱ አስተያየት ጀርመን በአዲሱ ህግ ተጠቃሚ የመሆኗ ሰፊ ተስፋ አለ ።

«ባለፉት አመታት በርካታ ህጎች ከአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት ውጬ የሆኑ ዜጎች አውሮፓ ውስጥ እንዲሰሩ የሚፈቅዱ አልነበሩም ። የህጉ መላላት ሲጀምር ሰዎች እንደገና መጓዝ ይጀምራሉ ። ሰዎች ወደ ውጭ ሲሄዱ ሥራዮን አጣ ይሆን የሚል ፍርሃት አላቸው ። በዚህ ረገድ ግን ጀርመን በሰፊው ተጠቃሚ አገር ትሆናለች ብዮ አስባለሁ ። ምክንያቱም ጀርመን ውስጥ ሥራ አጥነት አነስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ኢኮኖሚዋም ጠንካራ ነው ። »

የውጭ ዜጎች ከጀርመን ይልቅ ወደ ሌሎች አገራት እንዲያተኩሩ የሚያደርጋቸው ሌላው ምክንያት ቋንቋ መሆኑን ነው ሆልገር ሼፈር የኮሎኙ የሥራ ቅጥር ጉዳዮች አጥኚ የሚያስረዱት

« በመሰረቱ ይህ ችግሩ የቋንቋ ገደብ ነው ። ከአንግሎ ሳክሰን ሃገራት ውጭ የሆኑ ጀርመንኛ ቋንቋ ይበልጥ ይከብዳቸዋል ። በከፊል ደግሞ ችግሩ ያለው ባለፉት ጊዜያት ሲሰራበት የነበረው አስቸጋሪው የጀርመን ወደ ጀርመን መኖር የሚፈልጉ ፈላስያንን የተመለከተው ህግ ነው ። ባለፉት አመታት ይህ ህግ ወደ ጀርመን ለመግባት ያለን ፍላጎት በመግታት ነው የሚታወሰው ። ከአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት ውጭ የሆኑ በሙያ የሰለጠኑ ዜጎች የስራና የመኖያ ፈቃድ ለማግኘት በጣም ነበር የሚቸገሩት ። ቢፈቀድም እንኳን በአመዛኙ በጊዜ ገደብ የተወሰነ ነው ። ለብዙዎች እንግዲህ ይህ አይነቱ መሰናክል መኖሩ የሚያማልለውን አማራጭ ከመሻት በስተቀር ወደ ጀርመን መምጣቱ ያን ያህል አያስደስታቸውም ነበር ። »

ለህንዳውያኑም አንዱ መሰናክል ቋንቋ ነው ወጣት ህንዳውያን እንግሊዘኛ ተናጋሪ የሆኑ አገሮችን ይመርጣሉ ። ሌሎች ደግሞ በጀርመን ያለው ዘረኝነት እንደሚገፋቸው ነው የሚናገሩት ። አንዳንዶች ደግሞ የጀርመንን ቀዝቃዛ የአየር ፀባይ መቋቋም የሚችሉም አይመስላቸውም ። ምንም እንኳን በአሁኑ ሰአት የኤኮኖሚ እድገት ዝግመት ቢኖርም ህንዳውያኑ በተለይም በመካከለኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት የህብረተሰብ ክፍሎች በሃገራቸው የወደፊት ኢኮኖሚ እደገት ትልቅ ተስፋ አላቸውና አይናቸውን ወደ ውጭ ከመጣል ይልቅ ሃገራቸው መቆየቱን መርጠዋል ። እናም ጀርመን በሯን ክፍት በማድረጓ በተፈላጊዎቹ የሥራ መስኮች ተገቢው ስለጠና ያላቸው ህንዳውያን በሙሉ ጀርመን ይመጣሉ ማለት እንዳይደለ ነው ታዛቢዎች የሚያስረዱት ። በአንፃሩ ደግሞ ህንዳውያኑም በመሉ ጀርመን መሄድ አይፈልጉም ማለትም አይደለም ። በጀርመን የቴክኖሎጂ እድገት የተሳቡ ጀርመን ከሌሎች አገሮች በተሻለ ደረጃ ላይ ትገኛለች ብለው የሚያምኑ ፣ ያሉበት ሆነው ጀርመንኛ በመማር ራሳቸውን በማዘጋጀት ላይ ናቸው ። ያም ሆኖ ጀርመን ተፈላጊ የውጭ ዜጋ ሠራተኞችን ለመሳብ ከእስካሁኑ በላይ ብዙ ጥረቶችን ማድረግ እንደሚገባት መረዳት ይቻላል ።

ሂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 07.08.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/15lQx
 • ቀን 07.08.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/15lQx