በጀርመን የመስቀል ዳመራ በዓል | ባህል | DW | 03.10.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

በጀርመን የመስቀል ዳመራ በዓል

በጀርመን በፍራንክፈርት እና አካባቢዋ የሚኖሩ ኢትዮጽያዉያን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች የመስቀል በዓልን፣ በደማቅ ሁኔታ አክብረዋል። ሁለት ሽህ ያህል ኢትዮጽያዉያን እንዲሁም በርካታ ጀርመናዉያን እድምተኞች የተገኙበት የደመራ ችቦ ከመቀጣጠሉ በፊት የፍራንክፈርት ከተማ ከንቲባ ተጠሪ በአሉን ለማክበር ለተሰበሰቡት ኢትዮጽያዉያን እና ጀርመናዉያን ንግግር አድርገዋል ለኢትዮጽያም የመልካም ምኞት መግለጫቸዉን አስተላልፈዋል

ዳመራ

ዳመራ

መዘምራን በተለይ ህጻናት መዘምራን ልዩ በሆነ ዜማቸዉ በአሉን የደመቀ አድርገዉት ቆይተዋል።
ቢያንስ ሶስት ሜትር ያህል ቁመት የነበረዉ የደመራ ችቦ እንደ ባህሉ አናቱ ላይ በአደይ አበባ የተጎነጎነ መስቀል ተሰክቶበታል። ዙርያዉን መለያችን በሆነዉ በአንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራም ታስሮአል። በአደባባዩ መዕዘንም የጀርመን እና የኢትዮጽያ ባንዲራ ይዉለበለባል። ህጻናት አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ህብረ ቀለም የተሰራ የሹራብ አይነት ኮፍያ አድርገዉ እጀ ጠባባቸዉን ለብሰዉ ደመራዉን እያዩ ይደነቃሉ ገሚሾቹም ዙርያዉን ይሮጣሉ። መቼም ልጅና ፊት አይበርደዉም ሆኖ ነዉ እንጂ የአየሩ ጸባይ እጀ ጠባብ ብቻ የሚያስለብስ አልነበረም። በአዋቂዎቹ በኩል ማጋነን ባይሆንብን ሴቱ ሙሉ በሙሉ የአበሻ ቀሚሱን ለብሶአል እንደዉ ለብርዱ መከላከያ ከላይ ካፖርት ደረበብ ወይም ጋቢ ብጤ ጣል ያደረገ በርካታ ቢሆንም። ወንዱም ቢሆን ሙሉ በሙሉ እጀ ጠባብ ለብሶ በበአሉ ላይ ባይገኝም ለበአሉ ድምቀት ለኢትዮጽያዊነቱ መለያ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ህብረ ቀለም ያለበት ክራባት፣ ኮፍያ ወይም አንገት ላይ የሚደረግ የቁልፍ ማንጠልጠያ የያዘ ብዙ ነበር። የባህል መድረካችን በፍራንክፈርቱ የመስቀል ደመራ በአል ላይ ተገኝቶ ነበር።