በጀርመን ታዋቂ የሆነችዉ የመረሃ ቤቴዋ ዓለም ከተማ | ባህል | DW | 30.07.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

በጀርመን ታዋቂ የሆነችዉ የመረሃ ቤቴዋ ዓለም ከተማ

በደቡባዊ ጀርመን ባቫርያ ግዛት የሚገኝ አንድ የራድዮ ጣብያ ኢትዮጵያ መረሃ ቤቴ አዉራጃ በምትገኘዋ ዓለም ከተማ በጀርመን ፋተርሽቴትን በምትባል ከተማ የሚኖሩ ነዋሪዎች ማኅበር መስርተዉ ስላቋቋሟቸዉ ሁለት የሕጻናት መዋያዎችና እያበረከቱ ስላሉት አስተዋፅዎ ሰፊ ዝግጅትን አስደምጦአል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 15:15

በጀርመን ታዋቂ የሆነችዉ የመረሃ ቤቴዋ ዓለም ከተማ

ይህን ተከትሎ ስለኢትዮጵያዉያን አኗኗር፤ ቋንቋዎች ባህልና ሙዚቃም በሰፊዉ ተነግሮአል። በደቡባዊ ባቫርያ ግዛት ፋተርሽቴትን ከተማ ከጀርመን ኢትዮጵያ ቆንስላ ተወካዮች በከተማዉ ተገኝተዉ የዓለም ከተማ ነዋሪን የሚራዳዉን ማኅበር ጎብኝተዋል። በዚህ ዝግጅታችን የኢትዮጵያዋን የዓለም ከተማንና የጀርመናንዋን ከተማ ፋትርሽቴትን ትስስርን እንቃኛለን።

Deutschland Alem Katema Partnerschaftsverein Vaterstetten

በከተማ ፋተርሽቴትን በተካሄደ ድግስ ላይ ዓለም ከተማን በማስተዋወቅ ላይ


ዓለም ከተማ ከባቫርያዋ ፋተርሽቴትን ከተማ ጋር በእህት ከተማነት ግንኙነትን ከመሠረተች በኋላ እዉቅናን እድገትን እያሳየች ነዉ። ሁለቱ ከተሞች ከ 20 ዓመታት በላይ በዘለቀዉ የወዳጅነት ግንኙነትና የባህል ልዉዉጥ ዓለም ከተማ በጀርመን ታዋቂነትን እያገኘችም መጥታለች። ባለፈዉ ሰሞን መቀመጫዉን ደቡብ ጀርመን ያደረገዉ ባየርሽ ሩንድ ፉንክ የተሰኘዉ ራድዮ በዓለም ከተማ የመጠጥ ዉኃ ቧንቧን በመትከል፤ ሁለት የሕጻናት መዋያ በመገንባት ቤተ-መጻሕፍቶችን በማቋቋሙ የሚታወቀዉን የዓለም ከተማ ፋተርሽቴትን ማኅበር ዋና ተጠሪን እያደረጉት ስላለዉ አስተዋፅዖ አንቶን ሽቴፈን አነጋግሮ ነበር። ስለኢትዮጵያ ባህል ቋንቋ ስለዓለም ከተማና ማኅበሩ እዚህ ጀርመን በሚሰበስበዉ የርዳታ ገንዘብ በከተማዋ ስለሰራቸዉ ነገሮች ማብራርያ ሰጥተዋል።


በመረሃ ቤቴ አዉራጃ በምትገኘዋ በዓለም ከተማ ርዳታዉን በመለገስ ላይ ያለዉ ከስድስት መቶ በላይ ሰዎች የተሰባሰቡበት ማኅበር በከተማዋ በተለይም ሕፃናትና ወጣትን ለመርዳት ቆርጦ ከተነሳ 21ኛ ዓመቱን አስቆጥሮአል። በዓለም ከተማ ያቋቋመቸዉ ሁለት የሕፃናት መዋያዎችም የተሰየሙት ማኅበርተኞቹ በሚኖሩባቸዉ አነስተኛ የጀርመን ከተሞች ከተሞች ስያሜ ነዉ፤ ፋተርሽቴትንና ባልድሃም። ይህ ታድያ ለባቫየርሽ ሩንድ ፉንክ ራድዮ ጋዜጠኛ ትልቅ ጥያቄን ነበር ያጫረለት። ለማኅበሩ ዋና ተጠሪ ለአንቶን ሽቴፈን ባቀረበዉም የመጀመርያ ጥያቄ፤ ለመሆኑ ኢትዮጵያዉያኑ ይህን ስያሜ ለመልመድና አስተካክሎ ለመጥራት አላዳገታቸዉም? የማኅበሩ ተጠሪ የአንቶን ሽቴፈን መልስ በጭራሽ ሲሉ ነበር መልስ የሰጡት።

«የጀርመንና ቋንቋ ቅላጼዉ ከአማርኛ ቋንቋ ጋር ዝምድና አለዉ በዚህም ምክንያት አልከበዳቸዉም።» ነበር ያሉት።

Deutschland Alem Katema Partnerschaftsverein Vaterstetten

የሁንቦልት ተማሪዎች ለዓለም ከተማ የርዳታ ገንዘብ የማሰባሰብ ዘመቻ


ዓለም ከተማ ዉስጥ ፋተርሽቴትንና ባልድሃም ብላችሁ በሰየማችኋቸዉ ሕፃናት መዋያ ዉስጥ ያሉት ሕፃናት የሚወዱት የሚያዘወትሩት የጨዋታ አይነትስ ምንድን ነዉ? ጀርመናዊዉ ጋዜጠኛ በመቀጠል ያቀረበዉ ጥያቄ ነበር።
«እንደሚመስለኝ እግር ኳስ ነዉ። በዓለም ከተማ ዉስጥ ብቻ ሶስት የእግር ኳስ ማኅበር ይገኛል። በዚህም ምክንያት በሕጻናት መዋያዉ ዉስጥ እግር ኳስ ጨዋታ ይዘወተራል።»
በአቋቋማችሁት የሕጻናት መዋያ መንግሥት ትምህርት እንዲሰጥ በመፈለጉም ቤት-መጻሕፍትም ማቋቋመችሁ ተነግሮአል። ለቤተ-መጻሕፍቱስ ምን ስያሜ ሰጣችሁት?


አንቶን ስቴፈን መልሳቸዉን የጀመሩት ፈገግ በማለት ነበር። «በርግጥ የሁለቱን ሕጻናት መዋያ ማኅበርተኞቻችን የሚኖሩበትን አካባቢ ስያሜ በመስጠት ማለትም ፋተርሽቴትን እንዲሁም ባልድሃም ብለን ሰይመናል፤ ሌላዉ ጥያቄዎ ለቤተ- መጻሕፍቱስ ምን ሥያሜን ሰጣችሁት ነዉ። በርግጥ ለማኅበራችን ከፍተኛ ገንዘብን በለገሱ የሚታወቀዉን ኮሌጅ ለማመስገን በመፈለጋችን በዚሁ ኮሌጅ ስም ለመሰየም ወስነናል። ይህ ኮሌጅ ሁንቦልት ኮሌጅ ይባላል። ለማኅበራችን ከፍተኛ ገንዘብ ነዉ የሚለግሰዉ። በዚህም ዓለም ከተማ ዉስጥ ያቋቋምነዉ ሁምቦልት ቤተ -መጻሕፍት ብለነዋል።
በመረሃቤቴ አዉራጃ የምትገኘዋ ከተማ ስያሜ ፍችም ሰፊ ነዉ። በርግጥ ስንት ነዋሪዎች ቢገኙባት ነዉ? ዓለም ከተማ የተባለችዉ!
«ሶስተኛ መዋዕለ ሕጻናት ለመክፈት በማቀድ ባለፈዉ ጥቅምት ወር የመሠረት ድንጋይ ለመጣል ወደ ኢትዮጵያዋ ዓለም ከተማ ተጉዘን ነበር። አንድ አነስተኛ የዓዉደ-ርዕይ ቦታንም አቋቁመናል። በዚያን ወቅት ስለከተማዋ የመጠጥ ዉኃ አቅርቦት ተነጋግረናል። ከመካከላችንም ከተማዋ ዉስጥ ወደሚገኘዉ የፊናንስ ቢሮም የደወሉ ነበሩ። በዓለም ከተማ 24,100 አካባቢ ነዋሪ እንዳለ ነዉ መረጃን ያገኘነዉ።»

Deutschland Alem Katema Partnerschaftsverein Vaterstetten

በፍራንክፈርት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጀነራል ምህረትዓብ ሙሉጌታ ፋተርሽቴትን ሲጎበኙለዚሁ ማኅበር ገንዘብ የሚለግሱ የአካባቢዉ ነዋሪዎች፤ ተማሪዎች ራድዮ ጣብያዉ ድረስ መጥተዉ ለማኅበሩ ተጠሪ ስለኢትዮጵያ ባሕል፤ አልባሳት፤ አመጋገብ እና ቋንቋ ሰፊ ቃለ-ምልልስ ያደረጉበት የራድዮ ፕሮግራም በጀርመንና አካባቢዉ ላይ ለሚገኙ የጀርመንኛ ቋንቋ አድማጮች ተሰራጭቶአል።


በቅርቡ ፍራንክፈት በሚገኘዉ የኢትዮጵያ ቆንስላ አዲስ ተሾመዉ የመጡት ቆንስላ ጀነራል ምህረትዓብ ሙሉጌታ ከሌሎች ሁለት የቆንስላ ጽ/ቤቱ ሠራተኞች ጋር ባቫርያ ግዛት ወደሚገኘዉ ፋተርሽቴትን ተጉዘዉ ከማኅበሩ ዋና ተጠሪና ከሌሎች የማኅበሩ አባላት ጋር ተገናኝተዋል። በከተማዋ ማዘጋጃ ቤት ወርቅማ የክብር መዝገብ ላይም የክብር ፊርማቸዉንም አኑረዋል። ቆንስላ ጀነራል ምህረትዓብ ሙሉጌታ ማኅበሩ በዓለም ከተማ ያቋቋማቸዉን አነስተኛ ተቋማትና ሌሎች ነገሮች በመጥቀስም አድንቀዋል። ማኅበርተኞቹ ከሚተገብሩት ቋሚ ሥራ በተጨማሪ በሙሉ ትጋት ከዓለም ከተማ ጋር ያለዉን ግንኙነትና ትብብር ለማጠንከር እየሰሩ መሆኑን ማየታቸዉን ነዉ የተናገሩት። ማኅበሩ በዚሁ ከተማ በተለያዩ ወቅቶች ፊስቲቫሎችን በማዘጋጀት የኢትዮጵያን አልባሳት ባህልና አመጋገብ በሰፊዉ እያሳዩ መሆናቸዉን መገንዘባቸዉን ቆንስላ ጀነራል ምህረትዓብ ጠቅሰዋል።

Deutschland Alem Katema Partnerschaftsverein Vaterstetten

በፍራንክፈርት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጀነራል ምህረትዓብ ሙሉጌታ ፋተርሽቴትን ሲጎበኙ

የጀርመንዋ ከተማ የፋተርሽቴትን ነዋሪዎች ወደ ኢትዮጵያ ሲሄዱ ዓለም ከተማን ጎብኝተዉ እንዲመጡ ቅስቀሳ እያደረጉ መሆኑን በተለያየ ጊዜ በሚዲያና በጋዜጦች ላይ የሚፃፍ መሆኑንም ገልጸዋል። የዓለም ከተማና ፋተርሽቴትን የእትማማች ወዳጅነት ይበልጥ በማጠንከር መሥርያ ቤታቸዉ ከሌሎች የጀርመንና የኢትዮጵያ ከተሞች ጋር የጥምረት የትብብር ሥራ እንዲካሄድ ጥረት እንደሚያደርጉም ቆንስላ ጀነራል ምህረተዓብ ሙሉጌታ ተናግረዋል።
በፋተርሽቴትን በሚገኘዉ ማኅበር የኮሚቴ አባል ወ/ሮ ራሄል መኮንን በዚህ ድርጅቱን ለማገዝ እንቅስቃሴን ከጀመሩ ወደ ሰባት ዓመት እንደሆናቸዉ ይገልፃሉ። ጀርመናዉያኑ የትርፍ ጊዜን ስራ እየሰሩ ዓለም ከተማን እንደሚረዱም ሳይገልፁ አላለፉም።


ዉጤታማ ግንኙነት ሥለነበር ተደስቻለሁ ያሉን በደቡባዊ ጀርመን የፋተርሽቴትን ዓለም ከተማ የእህትማማች ከተሞች ማኅበር ዋና ተጠሪ አንቶን ሽቴፈን የቆንስላ ጀነራል ምህረትዓብ ሙሉጌታ በከተማቸዉ የተገኙት ከሁለት ኢትዮጵያዉያን ባልደረቦቻቸዉ ጋር እንደነበር ተናግረዋል።

20 Jahre Partnerstadt zwischen Alem Katema und Vaterstetten

የሁንቦልት ተማሪዎች በስፖርታዊ እንቅስቃሴ ለዓለም ከተማ የርዳታ ገንዘብ የማሰባሰብ ዘመቻ


በፋተርሽቴትን ዉስጥ ዓለም ከተማን ለማስተዋወቅ የተሰሩትን ነገሮች ካስጎበኝዋቸዉ በኋላም ለሁለት ሰዓታት ያህል በአንድ ጠረቤዛ ዙርያ በአንድ ማዕድ መቀመጣቸዉንና በእህትማማቾቹ ከተሞች መካከል ከሁለቱም ወገኖች ስላለዉና ወደፊት ሊሠሩ ስለታቀዱ ሥራዎች መወያየታቸዉን ገልፀዉልናል። ማኅበሩ ሰፊ መረሃ-ግብርን ለመጠርጋትን ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይን ለማፍሰስ አቅም እንደሌለዉም ጠቁመዋል።
ከአዲስ አበባ 185 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘዉ የመረሃ ቤቴ አዉራጃዋ ዓለም ከተማ፤ በደቡባዊ ጀርመን በባቫርያ ግዛት ከምትገኘዉ ፋተርሽቴትን ከተማ ጋር ከ 20 ዓመታት በላይ በዘለቀዉ ወዳጅነት በርካታ ርዳታን እያበረከቱ ያሉትን በማመስገን ሙሉዉን መሰናዶ የድምፅ ማድመጫዉን ማዕቀፍ በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ
ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic