በጀርመን በውጭ ዜጎች ግድያ የተከሰሰው ቡድን የፍርድ ሂደት | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 10.07.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

በጀርመን በውጭ ዜጎች ግድያ የተከሰሰው ቡድን የፍርድ ሂደት

ፖሊስ ሰዎቹ ከአደንዛዥ እጽ ዝውውር  ወይም ከቡድን ወንጀል ጋር በተያያዘ ነው የተገደሉት ይል ነበር። ይህ የፖሊስ አስተያየት እንደ ጠበቃ ፎን ዴር ቤርንስ ከተቋማዊ ዘርኝነት ጋር የሚስተካከል ነው በተለይ ከግድያዎቹ ጋር በተያያዘ የጀርመን የሀገር ውስጥ ደህንነት ሚና እስከ ምን ድረስ እንደነበረ ግልጽ ለማድረግ የፖለቲካ ፍላጎት አለማሳየቱ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:03

የኤን ኤስ ዩ የፍርድ ሂደት እና የሚጠበቀው ብይን

ጀርመን ውስጥ በህቡዕ ይንቀሳቀስ በነበረው ብሔራዊ ሶሻሊስት በተባለው ቡድን አባል ላይ በደቡባዊ ጀርመንዋ ሙኒክ ከተማ ውስጥ ነገ ይሰጣል ተብሎ የሚጠበቀው ብይን በመላ ጀርመን ትኩረት ስቧል።  ቡድኑ ለዓመታት ጀርመን ውስጥ በውጭ ዜጎች ላይ በተፈጸሙ ግድያዎች ይጠረጠራል። የዛሬው አውሮጳ እና ጀርመን ዝግጅታችን በፍርዱ ሂደት በሚጠበቀው ብይን እና አስተምህሮቱ ላይ ያተኩራል። ከአምስት ዓመታት በላይ በወሰደ የፍርድ ሂደት በመቶዎች የሚቆጠሩ ምስክሮች ቃል ተደምጧል። ረዘም ላለ ጊዜ የተወሳሰበ ሙግት ተካሂዷል። የሟች ቤተሰቦች ለፍርድ ቤት ቃላቸውን ሲሰጡ እንባቸውን እይረጩ ሲናገሩ ታይተዋል። ይህ ለ430 ቀናት የተከናወነ የፍርድ ሂደት በሙኒክ ከተማ ነገ መቋጫ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል። በነገው እለት አይኖች ሁሉ በተጠርጣሪ ቤአተ ቼፐ እና በዳኛ ማንፍሬድ ጎትዘ ላይ ያነጣጥራሉ። ቤአተ ቼፐ ራሱን «በህቡዕ የሚንቀሳቀሰው ብሔራዊ ሶሻሊስት» በምህጻሩ NSU ብሎ በሚጠራው ቡድን አባልነት ትጠረጠራለች። ቡድኑ ከ10 ዓመታት በፊት በተለያዩ የጀርመን ከተሞች በ9 የውጭ ዜጎች እና በአንዲት ፖሊስ ላይ ተፈጽመዋል በተባሉ ግድያዎች ይጠረጠራል። እርስዋ ግን አባል አይደለሁም ስትል አስተባብላለች። ቼፐ ከሁለቱ የቡድኑ መሥራቾች እና ጓደኞቿ ኡቨ ሙንድሎስ እና ኡቨ ቦንሃርድት ጋር ስቪካው በተባለው ከተማ ለበርካታ ዓመታት በሌላ ስም በተከራዩት ቤት ውስጥ አብራ ትኖር ነበር። ሙንድሎስ እና ቦንሃርድት በህዳር 2011 መጀመሪያ ላይ ጉዳዩ ሲደረስበት የራሳቸውን ህይወት አጥፍተዋል። ሰዎቹ ሞተው የተገኙት እንደ ቤትም

በሚገለገሉበት መኪና ውስጥ ነበር። ፖሊስ እንዳለው ሁለቱ ሰዎች የራሳቸውን ህይወት ያጠፉት መኪናውን ካቃጠሉ በኋላ ነበር። በዚያው ቀን በጥቂት ሰዓታት ውስጥ የስቪካዉ መኖሪያ ቤታቸው በእሳት ተያይዟል ፍንዳታም ደርሶበታል። ከዚያ በኋላም ቼፐ እጅዋን ለፖሊስ ሰጠች። ቤአተ ቤቱን በማቃጠል ትጠረጠራለች። ቼፐ ከሁለት ዓመት ተኩል በኋላ በጎርጎሮሳዊው 2015 ለመጀመሪያ ጊዜ ዝምታዋን ሰብራ በሰጠችው የጽሁፍ መግለጫ ምንም እንኳን ከአባላቱ ጋር አብራ ብትሆንም የቡድኑ አባል እንዳልነበረች እና ድርጊታቸውንም ትቃወም እንደነበረ ገልጻለች። የሟች ቤተሰቦችንም ይቅርታ ጠይቃለች። በዚሁ መግለጫዋ ጓደኞችዋ ሙንድሎስ እና ቦንሃርድት የፈጸሟቸውን ግድያዎች ማስቆም ባለመቻልዋ  ግን የሞራል ጥፋተኝነት እንደሚሰማት አስታውቃለች። ይሁንና በወቅቱ «የሼፐ ኑዛዜ»የተባለውን ይህን መግለጫ ከምር የወሰዱላት ጥቂቶች ናቸው። ብዙዎች በሰጧቸው አስተያየቶች ከሃላፊነት ለመሸሽ ያደረገችው ሙከራ አድርገው ነው የቆጠሩት።  ሼፐ እና ሌሎች አራት የቡድኑ ደጋፊዎች የተባሉ ሰዎች የፍርድ ሂደት በሙኒክ ከፍተኛ የአካባቢ ፍርድ ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረቡት ግንቦት 6፣2013 ነው። ቼፐ እድሜ ይፍታህ እንዲበየንባት የጠየቀው አቃቤ ህግ ቡድኑን እና አባላቱን በመደገፍ የተጠረጠሩት 4 ሰዎች ደግሞ ከሦስት እስከ 12 ዓመት እስራት እንዲፈረድባቸው ጠይቋል። ይሁን እና የሟች ቤተሰቦች ብይኑ ምንም ይሁን ምን በበኩላቸው የቡድኑን ወንጀሎች በሚያጣሩት የጀርመን ባለሥልጣናት ላይ የራሳቸውን ፍርድ ሰጥተዋል። ቤተሰቦች መንግሥት የገባልን ቃል ሙሉ በሙሉ አልተፈጸመም ብዙ ያልተመለሱ ጥያቄዎች አሉ ሲሉ ቅሬታቸውን እየገለጹ ነው። መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በየካቲት 23፣2012 ሟቾችን ለማሰብ በተካሄደ ስነ ስርዓት ይህን ቃል ገብተው ነበር።

«እንደ ጀርመን  ፌደራል  ሪፐብሊክ መራሄ መንግሥት ግድያዎቹን ለማጣራት እና ተባባሪዎቹን እና ከጀርባ ሆነው ሲደግፉ የነበሩትን ተጠያቂዎቹን  ለፍርድ ለማቅረብ የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን»

Infografik NSU Mordopfer BRA

ሜርክል ይህን ቢሉም ከምርመራው ጋር በተያያዘ መልስ የሚያሻቸው ግን እስካሁን መልስ ያላገገኙ በርካታ ጥያቄዎች እንዳሉ አንድ የሟች ቤተሰቦች ጠበቃ ያስረዳሉ። አንቶንያ ፎን ዴር ቤርንስ በጎርጎሮሳዊው 2006 ዶርትሙንድ በተባለው ከተማ ውስጥ የተገደለው ሜህሜት ኩባሲክ የተባለው ቱርካዊ ልጆች ጠበቃ ናቸው። በርሳቸው አስተያየት የሟች ልጆች አባታቸው በምን ምክንያት እንደተገደለ ፍጹም ላያውቁ ይችላሉ። የግድያው ሰለባ ቤተሰቦች ቼፐ ለምን ወላጆቻቸው ዘመዶቻቸው እንደተገደሉ ፍንጭ መስጠት ትችል ነበር። ይሁን እና እርስዋ ስለ ግድያው ያወቀችው ዘግይቶ መሆኑን ነው የገለጸችው ጠበቃ ፎን ዴር ቤርንስ ይህን በፍጹም አያምኑም። እርሳቸው እንደሚሉት እንደሚባለው የተቻለው ሁሉ እየተደረገ አይደለም።

«የህገ መንግሥት ጠባቂው አካል ሚና ግልጽ ሆኖ አልተኘም።ይህ የማድረግ ፖለቲካዊ ፈቃድ አልታየም።»

በጠበቆች በመብት ተሟጋቾች እና በሟች ዘመዶች እምነት በህቡዕ ይንቀሳቀስ የነበረው ብሔራዊ ሶሻሊስት ቡድን አሁን ሙኒክ ውስጥ የፍርድ ሂደታቸው ሲታይ ከቆየው በላይ በርካታ ረዳቶች አሉት። ለበርካታ ዓመታትም የጀርመን የሀገር ውስጥ ደህንነት መሥሪያ ቤት ቡድኑ እና ደጋፊዎቹ በሚያካሂዷቸው ዝግጅቶች ላይ የሚታደሙ በርካታ መረጃ ሰብሳቢዎችን መድቦ ነበር። ይሁን እና እነዚህ መሥሪያ ቤቱ አሰማርቷቸው የነበሩ መረጃ ሰብሳቢዎች ቃላቸውን ለመስጠት በይፋ ቀርበው የሰጡት ምስክርነት ውስን እንደነበረ ወይም ምንም ማለት እንዳይደለ ነው የሚነገረው። ከዚህ ሌላ የራሱ የመሥሪያ ቤቱ ወኪሎችም ተመሳሳዩን ማድረጋቸው ነው የሚገለጸው። አንዳንድ የፓርላማ አጣሪ ኮሚቴዎችም ስለ ቡድኑ ጥያቄዎችን ማንሳታቸው አልቀረም። ክሌመንስ ቢኒንገር የጀርመን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአንድ አጣሪ ኮሚቴ አባል ነበሩ። እርሳቸውም ሶስቱ ማለትም ቼፐ ቦንሀርድት እና ሙንድሎስ ብቻ የዚህ አሸባሪ ቡድን አባላት ናቸው ብለው አያምኑም።

«እውነት NSU ማለት  እነዚህ ሦስቱ ሰዎች ብቻ ናቸው? እንደገናም ከሦስቱ ሁለቱ ብቻቸውን አንድም ቦታ ምልክት ሳይተው ይህን ሁሉ ወንጀል ፈጸሙ። »

አሁን ከፓርላማ አባልነታቸው የተሰናበቱት የቀድሞ የፖሊስ መኮንን ቢኒንገር NSU ሰለባዎችን እና አካባቢዎችን  የሚመርጥበት መመዘኛ ምን ሊሆን እንደሚችልም ሁሌም የሚያነሱት ጥያቄ ነው። በድኑ ገድሏቸዋል የተባሉት 8 ቱርኮች አንድ ግሪካዊ እና አንዲት ፖሊስ ናቸው። 10ሩ ግድያዎች ከሰሜን ጀርመን በሮስቶክ እና በሀምቡርግ ከምዕራብ በዶርትሙንድ ከመሀል ጀርመን  በካስል እንዲሁም ከደቡባዊ ጀርመን በኑርንበርግ በሙኒክ እና ሃይልብሉም በተባሉት ከተሞች ነው ለ7 ዓመታት የተፈጸሙት። ያኔ ግን ፖሊስ ሰዎቹ ከአደንዛዥ እጽ ዝውውር  ወይም ከቡድን ወንጀል ጋር በተያያዘ ነው የተገደሉት ይል ነበር። ይህ የፖሊስ አስተያየት እንደ ጠበቃ ፎን ዴር ቤርንስ ከተቋማዊ ዘርኝነት ጋር የሚስተካከል ነው በተለይ  ቡድኑ በፈጸማቸው ግድያዎች ውስጥ የጀርመን የሀገር ውስጥ ደህንነት ሚና እስከ ምን ድረስ እንደነበረ ግልጽ ለማድረግ የፖለቲካ ፍላጎት አለማሳየቱ። እነዚህ ከግድያ የተረፉ እና የሟች ቤተሰቦች ግራ ያጋቡ ጉዳዮች መሆናቸውን ጠበቃዋ ያስረዳሉ። መራሂተ ም,ንግሥት አንጌላ ሜርክልም ከ6 ዓመት በፊት በገቡት ቃል ለሟች ቤተሰቦች ተስፋ ቢሰጡም መንግሥታቸው ሁሉንም ጉዳይ ግልጽ ለማድረግ ባለመቻሉ ከባድ መዘዞችን አስከትሏል። የዚያን ጊዜው የጀርመን የሀገር ውስጥ ደህንነት መሥሪያ ቤት ፕሬዝዳንት ሃይንዝ ፍሮም በዚሁ መዘዝ በጎርጎሮሳዊው2012 ከሥልጣናቸው በፈቃዳቸው መሰናበታቸው ይታወሳል። ፕሬዝዳንቱ ስራቸውን የለቀቁት የቡድኑ ህልውና ሲታወቅ ከNSU ጋር የተያያዙ ፋይሎች እንዲወድሙ ከተደረገ በኋላ ነበር። የቀሩት ቡድኑን የተመለከቱ ፋይሎች ደግሞ ተቆልፎባቸዋል። አንዳንዶቹ ደግሞ ምርመራው ከተጀመረ በኋላ ሳይቀር እንዲወድሙ ተድርጓል ነው የሚባለው። እነዚህን ሁሉ መዘዞችን ባስከተለው በህቡዑ ብሔራዊ ሶሻሊስቶች ቡድን አባልነት እና ድጋፍ ሰጭነት ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች የፍርድ ሂደት ላይ ነገ ብይን ይጠበቃል። አስሩንም ሰዎች በአንድ ሽጉጥ መግደላቸው የሚነገረው ሙንድሎስ እና ቦንህርድት  በህዳር 2011 ህይወታቸውን በገዛ እጃቸው ያጠፉት ከከሸፈባቸው የባንክ ዝርፊያ በኋላ ነበር። ከዚያ በኋላ ነው ትኩረቱ ወደ ባልደረባቸው ቤአተ ሼፐ የሆነው። የፌደራል አቃቤ ህግ ቼፐ በግድያዎቹ በሙሉ በመተባበር ጥፋተኛ እንድትባል ጠይቋል። ነፍሰ ገዳዮቹ ሁለቱ ጓደኞቿ ሆነው ቼፐ እንዴት ጥፋተኛ ልትባል ትችላለች አሁን የሚነሳ ዋናው ጥያቄ ሆኗል። በህይወት የምትገኘው ብቸኛዋ የቡድኑ አባል የ43 ዓመቷ ቼፐ ጥፋተኛ ከተባለች የሚጠብቃት የእድሜ ልክ እሥራት ነው። የቼፐም ሆነ የአራቱ የNSU ተባባሪዎች ፍርድ ነገ ይታወቃል ተብሎ ቢጠበቅም NSUን በሚመለከት የሚነሱት መልስ ያላገኙ ጥያቄዎች ግን ማነጋገራቸው መቀጠሉ አይቀርም።

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ 

Audios and videos on the topic