1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጀርመን በቀኝ ጽንፈኞች ላይ የተጠናከረው ተቃውሞ

ማክሰኞ፣ ጥር 14 2016

ህዝብ በገፍ አደባባይ ወጥቶ መቃወም የጀመረው«ኮሬክቲቭ» የተባለው በምርመራ ጋዜጠኝነት ላይ የተሰማራው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ባለፈው ኅዳር ፖስትዳም በተባለው ከተማ ተቃዋሚው አማራጭ ለጀርመን የተባለው ፓርቲ ከሌሎች ቀኝ ጽንፈኞች ጋር የውጭ ዝርያ ያላቸውን ሰዎች እንዴት ከጀርመን እንደሚያባርሩ በድብቅ የተነጋገሩበትን እቅድ ካጋለጠ በኋላ ነው።

https://p.dw.com/p/4bbKO
Deutschland Kundgebung „Zammreißen! - Bayern gegen Rechts“ in München
ምስል Matthias Balk/dpa/picture alliance

በጀርመን በቀኝ ጽንፈኞች ላይ የተጠናከረው ተቃውሞ

በጀርመን በቀኝ ጽንፈኞች ላይ የተጠናከረው ተቃውሞ 

 

ጀርመናውያን ሰሞኑን በሚያካሂዷቸው የተቃውሞ ሰልፎች ከወትሮው በተለየ በቀኝ ጽንፈኞች ላይ ቁጣቸውን  በመግለጽ ላይ ናቸው። ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ከአርብ እስከ እሁድ ትላላቅ የሚባሉትን ከተሞች በርሊን ሙኒክና ኮሎኝን ጨምሮ ቢያንስ አንድ መቶ በሚሆኑ አካባቢዎች «አማራጭ ለጀርመን» የተባለውን ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲንና መሰሎቹን በመቃወም እስከ 1.4 ሚሊዮን የተገመተ አደባባይ ወጥቷል።በርሊን የቀኝ ጽንፈኞች ተቃውሞና የሃገሪቱ መሪዎች ቁጣ 

 ይህን ያህል ቁጥር ያለው ህዝብ በገፍ አደባባይ ወጥቶ መቃወም የጀመረው «ኮሬክቲቭ» የተባለው በምርመራ ጋዜጠኝነት ላይ የተሰማራው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ባለፈው ኅዳር ፖስትዳም በተባለው ከተማ በጀርመን ምክር ቤት ውስጥ መቀመጫ ያለው ተቃዋሚው አማራጭ ለጀርመን የተባለው ፓርቲ ከሌሎች ቀኝ ጽንፈኞች ጋር የውጭ ዝርያ ያላቸውን ሰዎች እንዴት ከጀርመን እንደሚያባርሩ በድብቅ የተነጋገሩበትን እቅድ ካጋለጠ በኋላ ነው። ጀርመን የተማሩትና የሚሰሩት የፖለቲካ ሳይንስና የሕግ ምሁር ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ ለዶቼቬለ እንደተናገሩት ቀኝ ጽንፈኞቹ በድብቅ በተነጋገሩበት ሰነድ መሠረት ከጀርመን ለማባረር የያቀዱት መሰረታቸው የውጭ የሆነ የጀርመን ነዋሪዎችና ዜጎች ቁጥር በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ነው.።እነዚህ ቡድኖች እቅዱን ተግባራዊ የሚያደርጉበትን መንገድም ጭምር በሰነዱ አካተዋል።

በሙኒክ  ቀኝ ጽንፈኞችን የተቃወመ ሰልፍ
በሙኒክ ቀኝ ጽንፈኞችን የተቃወመ ሰልፍ ምስል Johannes Simon/Getty Images

ህዝቡ ቁጣውን በገለጸባቸው ሰልፎች የተሰጡ አስተያየቶች  

 

በዚህ የቀኝ ጽንፈኞች እቅድ የተቆጣው ህዝብ በየሚገኝባቸው ከተማዎች ጊዜ ሳያጠፋ ነበር ግልብጥ ብሎ በመውጣት በአደባባይ ሰልፍ ተቃውሞውን ማሰማት የጀመረው። በምዕራብ ጀርመንዋ በኮሎኝ ከተማ በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የተገኙት ሽቴፋን ካልሽ ቀኝ ጽንፈኞች ገደቡን ጥሰው ማለፍ የጀመሩት አሁን አይደለም ይላሉ። «በኔ አመለካከት መስመሩ ከተጣሰ ብዙ ጊዜ ሆኖታል። ሆኖም በተለይ ፖለቲካው ፣በጉዳዩ ላይ ሁሌም በጣም ዝም እንዳለ ነው። አሁን ደግሞ ሁሉም ነገር አንድ ላይ በፍጥነት እየመጣ ነው። «ኮሬክቲቭ» የተባለው የምርመራ ጋዜጠኝነት የሚያካሂደው ድርጅት ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት ነገሮች በተሳሳተ አቅጣጫ እየሄዱ መሆኑ ግልጽ ነው። ኬምኒትስ ቀኝ ጽንፈኞች እና ተቃዋሚዎቻቸው 

ስለዚህ ሁሉም አሁን አደባባይ መውጣት አለበት።ይህ ደግሞ እስከዛሬ በንቃት ተቃውሞአቸውን ለሚያሰሙት ሳይሆን እስካሁን ዝምታን ለመረጡት ነው።» እሁድ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተገኙበት በበርሊኑ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የተካፈሉት የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አማካሪ ጀራልድ አንገረር ሰልፍ የወጡት ጊዜው አሁን ነው ብለው ስላሰቡ መሆኑን ተናግረዋል። «ሁሉንም ነገር ስከታተል ነበርና ቀኝ ጽንፈኞችን ተቃውሞ አደባባይ መውጫ፣ ፊቴንም፣መኖሬንም በአደባባይ ማሳያው ጊዜው አሁን ነው ብዬ ስላሰብኩ ነው።» 

የበርሊኑ የተቃውሞ ሰልፍ
የበርሊኑ የተቃውሞ ሰልፍ ምስል Thomas Imo/photothek/picture alliance


ሊዲያ ሽቴፈን ሀገን የተባሉት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሞያ ጉዳዩን ንቆ ይተው የነበረው ህዝብ አደባባይ መውጣቱን አድንቀዋል። «ነገሮች ወዴት እንደሚሄዱ የምናይ ይሆናል። ግን  በስተመጨረሻ አንድ ነገር መደረጉ ፣ዝምታን መርጦ የቆየው ብዙሀኑ እንደቀድሞው ዝም ብሎ አለመቅረቱ ጥሩ ነው»  እንደሽቴፈንሀገን ሁሉ ሌላዋ ሰልፈኛ ኡተ ራውትንበርግም የጽንፈኞች እንቅስቃሴ እስካሁን ችላ ተብሎ መቆየቱን ያምናሉ።« እንደሚመስለኝ ወደ ቀኝ ማዘንበሉ ጎልቶ በሚታይ ሁኔታ በሀገሪቱ እየተስፋፋ ነው። እኔ እንደምለው እዚህ ያለነው የተቀረነው እኛ ፣ጉዳዩ የትም አይደርስም ፤ እነዚያ ጥቂቶቹ የሚያስቡት ትክክል አይደለም ብለን ነበር። ሆኖም የነርሱ አመለካከት ከሚታሰበው በላይ ተዛምቷል።»የዞሊንገኑ የቀኝ ጽንፈኞች ጥቃት 30ኛ ዓመት

ቀኝ ጽንፈኞችን የተቃወመ ሰልፍ በኮትቡስ ብራንድንቡርግ
ቀኝ ጽንፈኞችን የተቃወመ ሰልፍ በኮትቡስ ብራንድንቡርግ ምስል Frank Hammerschmidt/dpa/picture alliance

ከሰልፎቹ ምን ይጠበቃል?

አቶ ሀብተአብ ኢያሱ ጀርመን ሲኖሩ ከ30 ዓመት በላይ ሆኗቸዋል ።ከፍተኛ ትምሕርታቸውን የተከታተሉትም የሚሰሩትም እዚሁ ጀርመን ነው።  ህዝቡ ዓይንህ ላፈር ያለውን «አማራጭ ለጀርመን» ፓርቲ በዴሞክራሲ ስም ተደብቆ የሚንቀሳቀስ ፓርቲ ነው የሚሉት። ከ10 ዓመት በፊት የተመሰረተው የአማራጭ ለጀርመን ፓርቲ ደጋፊዎች ቁጥር እየጨመረ በመሄዱ ፓርቲው በአጭር ጊዜ ውስጥ የፌደራሉን ምክርቤት ጨምሮ በተለያዩ የጀርመን ግዛቶች መቀመጫዎች አሉት። አቶ ሀብተአብ እንደሚሉት ግን የአሁኑ ተቃውሞ ከዚህ ቀደምና አሁንም ፓርቲውን አሳንሰው ለሚያዩት የተለያዩ መልዕክቶችን ያስተላለፈ ነው። ከመካከላቸው ከዚህ ቀደም የፓርቲውን እንቅስቃሴዎች ችላ ይሉ የነበሩ ሰዎችን ማንቃት ይገኝንበታል። ምርጫ የማይሄደው ህዝብ ምርጫ እንዲወጣ ይገፋፋል  ብለው ይጠብቃሉ።

ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ