በጀርመንኛ ቋንቋ ሥነ-ጽሑፍ ለኢትዮጵያዊዉ ሽልማት | ባህል | DW | 22.10.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

በጀርመንኛ ቋንቋ ሥነ-ጽሑፍ ለኢትዮጵያዊዉ ሽልማት

በጀርመን የታወቁ ደራሲ እና የቱቢንገን ዩንቨርስቲ የክብር ሴናተር ዶ/ር ልዑል አስፋዉ ወሰን አስራተ «ያኮብ ግሪም ፕራይስ » የተሰኘዉን በጀርመን ቋንቋ ከፍተኛዉን ከሥነ-ጽሑፍ ሽልማት አገኙ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 17:16
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
17:16 ደቂቃ

በጀርመንኛ ቋንቋ ሥነ-ጽሑፍ ለኢትዮጵያዊዉ ሽልማት

Jacob-Grimm-Preis Deutsche Sprache Schriftsteller Asfa-Wossen Asserate

በአዳራሹ የተገኙት እድምተኞች በከፊል


በጀርመንኛ ቋንቋ መጠርያዉ « Jacob-Grimm-Preis- Deutsche Sprache » በመባል የሚታወቀዉ በጀርመን ቋንቋ ከፍተኛዉ የሥነ-ጽሑፍ ሽልማት ዘንድሮ ለልዑል አስፋዉ ወሰን አስራተ ተሰጥቶአል። በጀርመን በ19 ኛዉ ክፍለ ዘመን የመጀመርያዉን የአንድ ዕውቀት ዘርፍ የመረጃ ክምችት መዝገብን ማለት ኢንሳይክሎፒዲያን የፃፉና ለጀርመን ቋንቋ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማድረጋቸዉ የሚነገርላቸዉ የጀርመናዉያኑን ወንድማማቾች የቪልሄልምና የያኮብ ግሪምን ሥያሜ የያዘዉ 30 ሺህ ይሮ የገንዘብ ስጦታን ያካተተዉ ይህ ከፍተኛ ሽልማት ዘንድሮ ለአስራ አስራ አምስተኛ ጊዜ የተሰጠ ሲሆን ሽልማቱን አንድ አፍሪቃዊ ሲያገኝ የዘንድሮዉ ተሸላሚ በፍራንክፉርት ነዋሪ የሆኑት ኢትዮጵያዊዉ ልዑል አስፋዉ ወሰን አስራተ የመጀመርያዉ መሆናቸዉ ነዉ።

የካስል ከተማ ከንቲባን ጨምሮ ከፍተኛ የጀርመን ባለሥልጣናት ምሑራን እንዲሁም በግምት ወደ አንድ ሺህ የሚሆኑ እድምተኞች የተገኙበት የሽልማት አሰጣጥ ሥነ-ስርዓት የተካሄደዉ ኮንግረስ ፓላስ በመባል በሚታወቀዉ በካስል ከተማ እንብርት ላይ በሚገኘዉ ጥንታዊ በተ-መንግሥት ሠፊ አዳራሽ ዉስጥ ነበር።
በየዓመቱ ለሚሰጠዉ ለዚህ ከፍተኛ ሽልማት እንዲበቃ የሚመርጠዉና የሚመክረዉ የዳኞች ስብስብ ተጠሪ ፕሮፊሰር ዶክተር ሄልሙት ግሉክ በሽልማት አሰጣጥ ሥነ-ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ዶክተር ለልዑል አስፋዉ ወሰን አስራተ ልዩ ስለሆነዉ ሥነ-ጽሑፍ ችሎታና የትረካ ክህሎታቸዉ አወድሰዋቸዋል።

Jacob-Grimm-Preis Deutsche Sprache Schriftsteller Asfa-Wossen Asserate

ዶ/ር ልዑል አስፋዉ ወሰን አስራተ በካስል ከተማ ከንቲባ በመራት የወርቅ መዝገብ ላይ የክብር ፊርማቸዉን ሲያኖሩ


« የአስራተ ሥነ-ጽሑፎች በከፍተኛ ደረጃ የቋንቋ አገላለፅ ሥርዓትን የጠበቀ፤ መስዕብ ያለዉና ቁም ነገር አዘል ነዉ። ሥነ-ጽሑፎቹ ሚስጥራዊ አልያም ምፀታዊነትም የሚታይበት የማይሰለች ትረካን የተሞላ በመሆኑ ጀርመንኛ የአፍ መፍቻ ቋንቋዉ ላልሆነ ደራሲ የሚያስደንቅ ነዉ።»


የግሪም ወንድማማቾች በሚል መጠርያም የሚታወቀዉ ይህ ከፍተኛ የጀርመን ቋንቋና ሥነ-ፅሑፍ ሽልማት ከዚህ ቀደም በተለያዩ ዘርፎች ጀርመን ቋንቋ ከፍተኛ አስተዋፅዖን ያደረጉ ጀርመናዉያን ተሸላሚ ነበሩ። ከነዚህ መካከል ታዋቂዉ ጀርመናዉያ ከያኒ ኡዶ ሊድን በርግ፤እንዲሁም ታዋቂዉ ጀርመናዊ ደራሲ፤ የኪነ-ጥበብ ሰዉ ዲተር ኑር ይገኙበታል። የቀድሞዋ የፍራንክፉርት ከተማ ከንቲባ ፔትራ ሮት በሽልማት አሰጣጥ ሥነ-ስርዓት ላይ ተገኝተዉ ባደረጉት ንግግር ልዑል አስፋዉ ወሰን አስራተን ለረጅም ዓመታት በፍራንክ ፈርት ከተማ መዘጋጃ ቤት እንዲሁም በተለያዩ ዘርፎች በከተማዋ በሚያደርጉት ጥሩ ሥራ ረዘም ላለ ጊዜ አዉቃቸዋለሁ ሲሉ ነበር ስለሚተገብሩትና ስለተሰጣቸዉ ሽልማት በማወደስ ንግግራቸዉን የጀመሩት፤


«ከዶክተር አስፋዉ ወሰን አስራተ ጋር የምንተዋወቀዉ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ነዉ። የምንተዋወቀዉ ለረጅም ጊዜያት የኃላፊነት ሥራ ላይ በነበርኩበት በፍርናክፈርት ከተማ መዘጋጃ ቤት፤ ለፍራንክፈርት ከተማና በአጠቃላይ ለማኅበረሰቡ በሚደረገዉ ምግባረ ሰናይ ሥራዎች ላይ ነዉ። በተለይም በከተማዋ በባህል ነክ ነገሮች ላይ በሚሰራዉ ሥራ ፤ በግዛቱ ዉስጥ ባለዉ ሄስሽ ራድዮ ፤ በፍራክንፈርት በሚታወቀዉ የመፀሐፍ አዉደ ርዕይ ላይ እንተዋወቃለን ። እናም አስፋወሰን በከተማችን በፍራንክፈርት ከፍተኛ ቦታ የሚሰጣቸዉ የከተማዋ ነዋሪ ናቸዉ። በአሁኑ ሰዓት ደግሞ ይበልጥ በሥነ-ጽሑፋቸዉ ማኅበረሰብን የሚያገናኙ የሚያስተዋዉቁና የሚያሳዉቁ ሆነዉ እናገኛቸዋለን።»

Jacob-Grimm-Preis Deutsche Sprache Schriftsteller Asfa-Wossen Asserate

የቀድሞዋ የፍራንክፉርት ከተማ ከንቲባ ፔትራ ሮት


ዶ/ር ልጅ አስፋዉ ወሰን በመቀጠል በጀርመንኛ ባደረጉት ንግግር ሽልማቱን በክብር እንደሚቀበሉ ተናግረዋል። በመቀጠልም የ20 ዓመት እድሜ ሳሉ በጎርጎረሳዊዉ 1968 ዓ,ም ወደ ጀርመን ሀገር እንደመጡ በመተረክ ፤ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህታቸዉን አዲስ አበባ በሚገኘዉ የጀርመን ትምህርት ቤት ተከታትለዉ፤ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቅያ ፈተናን ተፈትነዉ ነዉ ወደ ጀርመን ሀገር ነዉ የመጡት፤ በኃላም በጀርመን እና በብሪታንያ ኬምብሪጅ ዩንቨርስቲ፤ በታሪክ፤ በሕግ እና በኤኮኖሚ ሞያ፤ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን አጠናቀዋል። ልዑል አስፋዉ ወሰን ከሽልማቱ ሥነ-ስርዓት በኋላ በሰጡን ቃለ ምልልስ ደስታዉ እና ክብሩ የሳቸዉ ብቻ እንዳልሆነ ሽልማቱን በሀገራቸዉ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዉያን ስም እንደሚቀበሉ ነዉ የገለፁልን።


የጀርመን ቋንቋ ጥናት ማኅበር በምህፃሩ «VDS » አባል እንደሆኑ የነገሩንና ይህን ሽልማት አሰጣጥ ሥነ-ስርዓት ለመከታተል ወደ ካስል ከተማ የመጡት የሃኖቨር ከተማ ነዋሪዉ ኡልማ፤ ልዑል አስፋዉ ወሰን አስራተን ሲሸለሙ በማየታቸዉ መደሰታቸዉን ገልፀዋል። « አስፋወሰን የደም ግባት ያላቸዉ ከፍተኛ ምሁር ሆነዉ አግኝቻቸዋለሁ። እዚህ ተገኝቼ እሳቸዉን በማየቴና የዝግጅቱ ተካፋይ በመሆኔ እድለኛ ነኝ»


በዚያዉ በካስል ከተማ ሲኖሩ ከሰላሳ ዓመት በላይ የሆናቸዉ ወሮ አልማዝ አሉላ፤ የሽልማት አሰጣጥ ሥነ ስርዓቱን ከጀርመናዊ ባለቤታቸዉ ጋር ተከታትለዋል። በሥነ-ስርዓቱ ላይ ስለ ኢትዮጵያ ስለ ልዑል አስፋዉ ወሰን ሲነገር ጀርመናዉን በጭብጨባ ደስታቸዉ ሲገልፁ በማየታቸዉ መደሰታቸዉን ገልፀዋል።


በወጣትነት እድሚያቸዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ያወቋት ጀርመናዊት መምህራቸዉ ቋንቋን እና ባህልን ስላስተዋወቀቻቸዉ ወደ ጀርመን በመጡ ግዜ በተለይ በመጀመርያዎቹ ቀናት እንብዛም እንዳልተደናገራቸዉ፤ ዶክተር ልጅ አስፋወሰን ለፊስቲቫሉ ታዳሚዎች ገልፀዋል። ቢሆንም በጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን እዚሁ ጀርመን ከመጡ በኋላ ጀርመንኛ ቋንቋን አቀላጥፈዉ መናገር የሚችሉ እንዳሉ ሳይገልፁ አላለፉም። ኢትዮጵያዉያን በቋንቋ ችሎታ እንደማይታሙ ነዉ የተናገሩት።
ቢሆንም የጀርመንን ቋንቋ የአኗኗር ባህልን ሳያቁ ከሚመጡ ከአፍሪቃዉያን ወንድም እና እህቶቼ ጋር ስተያይ፤ የእኔ ሁኔታ የተመቻቸ ነበር፤ ያሉት ልዑል አስፋዉ ወሰን አስራተ በሽልማት አሰጣጥ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የጀርመንን ባለሥልጣናት በጀርመን በጥገኝነት ለሚኖሩ የዉጭ ዜጎች በመጀመርያ ደረጃ የቋንቋ ትምህርትን በነፃ እንዲሰጣቸዉ ሲሉ ጠይቀዋል።


በጀርመን የጀርመንኛ ቋንቋ ሰዋስዉ ጥናት በዩንቨርስቲ ደረጃ የተሰጠዉ የአማርና ቋንቋ ስዋስዉ በጀርመን ዩንቨርስቲዎች መሰጠት ከጀመረ በኋላ ነዉ ሲሉ ታዳሚዉን ያስደመሙት ልዑል አስፋወሰን ጀርመን የአማርኛ ሰዋስዉ ጥናት ቤት ነዉ ብለዉ ሲናገሩ በአዳራሹ ንግግራቸዉን የሚያደምጠዉ ታዳሚ በከፍተኛ ጭብጨባ ደስታዉንና ምስጋናዉን እንዲገልጽ አድርገዉታል።


ከዶ/ር ልዑል አስፋዉ ወሰን አስራተ ንግግርና ሽልማት አሰጣጥ ሥነ-ስርዓት በኋላ በካስል ከተማ ከንቲባ በመራት የወርቅ መዝገብ ላይ የክብር ፊርማቸዉን አኑረዋል። በመጠናቀቅያ ሥነ-ስርዓቱም ላይ አዳራሹ በሰልፍ ይጠብቋቸዉ ለነበሩ በርካታ ታዳሚዎች በጀርመንኛ ቋንቋ በፃፍዋቸዉ መፃሕፍት ላይ የምሥጋናና የክብር ፊርማቸዉን አኑረዋል።


ዶ/ር ልዑል አስፋዉ ወሰን አስራተ ባለፈዉ የጎርጎረሳዉያኑ ዓመት 2014 የመጨረሻዉ የአፍሪቃ ንጉስ » በሚል ለአንባብያን ያቀረቡት መጻሐፍ ከሳምንታት በፊት በእንጊሊዘኛ ተተርጉሞ በተለያዩ የአዉሮጳ ሃገራት በገበያ ቀርቦአል። በጀርመን ካስል ከተማ በጀርመን ቋንቋ ከፍተኛዉን ከሥነ-ጽሑፍ ሽልማት ስለ ተቀበሉት ኢትዮጵያዊዉ የተሰናዳዉን ሙሉ ቅንብርን የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ!


አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic