በድሬዳዋ ግጭት ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎች ተጎዱ | ኢትዮጵያ | DW | 24.01.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

በድሬዳዋ ግጭት ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎች ተጎዱ

ድሬዳዋ ዛሬ በተቃውሞ ስትናጥ ውላለች። በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች የጥይት ተኩስ ድምጽ ሲሰማ ውሏል። እስካሁን ድረስ በሰዎች ላይ ስለደረሰው ጉዳት በግልፅ የታወቀ ነገር ባይኖርም የቆሰሉ ሰዎች መኖራቸውን DW ለመረዳት ችሏል። 

በድሬዳዋ ግጭት ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎች ተጎዱ

በዛሬው ተቃውሞ በድሬዳዋ የሚገኘው የ05 ቀበሌ መቃጠሉን፤ ተሽከርካሪዎች መሰባበራቸውን እና ዝርፊያ መበራከቱን ዘጋቢያችን ገልጿል። "እኔ በተገኘሁባቸው አካባቢዎች የድል ጮራ ሪፈራል ሆስፒታል አምቡላንሶች በተደጋጋሚ ከተለያዩ ቦታዎች ድምፅ እያሰሙ የተጎዱ ሰዎች ሲያመላልሱ ተመልክቼያለሁ" ሲል በከተማዋ የሚገኘው የDW ዘጋቢ ተናግሯል።

በነዋሪዎች ዘንድ ሥጋት በፈጠረው ኹከት ከድሬዳዋ ወደ ሌሎች አካባቢዎች የሚያመሩ እና የከተማዋ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ተዘግተዋል፤ የትራንስፖርት አገልግሎትም ተቋርጧል። የDW ዘጋቢ ተቃዋሚዎች ድንጋይ በመደርደር እና ጎማ በማቃጠል መንገዶች ዘግተው ተመልክቷል። በተቃውሞ የተሳተፉ ወጣቶች "ጥያቄ አለን። ጥያቄያችንን ሊመልስ የሚችል አስተዳደር ከሌለ አያስፈልገንም" ሲሉ ተደምጠዋል። የጸጥታ አስከባሪዎች ተቃውሞውን ለመቆጣጠር አስለቃሽ ጭስ ቢተኩሱም በመላ ከተማዋ የተንሰራፋውን ኹከት መቆጣጠር የቻሉ አይመስልም። የDW የድሬዳዋ ዘጋቢ እንዳለው የጥይት ተኩስ ይሰማ ነበር። 

በድሬዳዋ ግጭት እና ኹከት የተቀሰቀሰው ጥር 13 ቀን 2011 ዓ.ም. የእግዚአብሔር አብ ታቦትን አስገብተው በሚመለሱ ምዕመናን ላይ ድንጋይ ከተወረወረ በኋላ ነበር። በድሬዳዋ ቀበሌ 09 ተፈጥሮ ለነበረው ግጭት እና ኹከት ተጠያቂ ናቸው ያላቸውን 84 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የገለጸው ፖሊስ ኹኔታው መረጋጋቱን ቢያስታውቅም ተቃውሞው ዛሬም እንደገና አገርሽቷል። 

ነዋሪዎች በከተማዋ ከሚፈጸሙ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ለመከላከል የራሳቸውን እርምጃ ወደ መውሰድ መሸጋገራቸው ለዛሬው ቀውስ መነሻ ነው ተብሏል። በድሬዳዋ ከቀናት በፊት ግጭት መቀስቀሱን ተከትሎ የከተማዋ አስተዳደር፣ የሐይማኖት አባቶች እና የአገር ሽማግሌዎች ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት ማድረግ መጀመራቸው ተነግሮ ነበር። የከተማዋ ከንቲባ እና የጸጥታ ኃላፊዎች በድሬዳዋ አዲስ ከተማ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከሚኖሩ ነዋሪዎች ጋር ለመነጋገር ለዛሬ ቀጠሮ ይዘዋል የሚል መረጃም ተሰራጭቶ ነበር። ውይይቱ በታቀደለት ጊዜ ሳይካሔድ በመቅረቱ የአዲስ ከተማ አካባቢ ነዋሪዎች በተቃውሞ መንገዶች ዘግተዋል። 

ከDW የድሬዳዋ ዘጋቢ መሳይ ተክሉ ጋር የተደረገውን ቃለምልልስ ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ።

መሳይ ተክሉ

እሸቴ በቀለ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች