በድሬዳዋው ግጭት ሰባት ሰዎች መሞታቸው ተገለፀ | ኢትዮጵያ | DW | 26.10.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

በድሬዳዋው ግጭት ሰባት ሰዎች መሞታቸው ተገለፀ

ከረቡዕ እስከ አርብ በድሬዳዋ በነበረ ግጭት እና ኹከት ስድስት ሰዎች በጥይት አንድ ሰው በስለት መገደላቸውን፤ ብዙ ሰዎች መቁሰላቸውን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ። የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን የሟቾች ቁጥር 67 መድረሱን ይፋ አድርጓል።

በድሬደዋ በሰሞኑ ኹከትና ብጥብጥ ሰባት ሰዎች መሞታቸውን የከተማው አስተዳደር የመንግስት ጉዳዮች ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ። ከረቡዕ እስከ አርብ ለሶስት ቀናት የዘለቀውን እና ጎማ በማቃጠል እና መንገድ በመዝጋት የተጀመረውን ኹከት ለመቆጣጠር የመከላከያ ሰራዊት አባላትን ጨምሮ የጸጥታ አስከባሪዎች ተሰማርተዋል።

የድሬደዋ አስተዳደር መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ እስቅያስ ታፈሰ «በፖሊስ በተጣራው እና ፖሊስ በሰጠን መረጃ መሰረት ሰባት ሰው ሞቷል» ሲሉ በዛሬው ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል። አቶ እስቂያስ እንዳሉት ስድስቱ በጥይት አንድ ሰው ደግሞ በስለት ተወግተው ሕይወታቸው አልፏል። ኃላፊው በከተማዋ በተፈጠረው ኹከት ብዙ ሰዎች «ቀላል እና ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው» አክለው ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል ከፍያለው ተፈራ በክልሉ በተቀሰቀሱ ግጭቶች የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 67 መድረሱን ባለፈው አርብ ማምሻውን ለሬውተርስ ተናግረዋል። ኃላፊው እንዳሉት ከሟቾቹ መካከል አስራ ሶስቱ በጸጥታ ኃይሎች የተገደሉ ሲሆን የቀሩት በተለያዩ ከተሞች በተቀሰቀሱ ግጭቶች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

አቶ እስቅያስ በሰጡት መግለጫ በድሬዳዋው ኹከት «ሃያ አምስት ቤቶች ላይ ዘረፋ ተፈፅሟል፤ አራት ቤቶች ተቃጥለዋል። ስድስት ተሽከርካሪዎች ላይ ጉዳት ደርሷል» ብለዋል።

በድሬዳዋ «ግጭቱ እንዲባባስ የሚፈልጉ ኃይሎች በከተማው ሕዝብ ላይ ከፍተኛ አደጋ ሊፈጥር የሚችል እንቅስቃሴ ሲደረግ እንደነበረ፤ በብሔር መሰረት በማድረግ ትንኮሳ እና ግጭት ለመፍጠር ጥረቶች» መደረጋቸውን አቶ እስቅያስ አስረድተዋል።

ኃላፊው «ቤተ እምነቶች ላይ ጉዳት ለማድረስ እና በዚያ ሰበብ የሐይማኖት ግጭት እንዲፈጠር ጥረት የማድረግ እንቅስቃሴዎች የነበሩበት ሁኔታ አለ» ብለዋል።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል ከፍያለው ተፈራ ተመሳሳይ ድርጊት ግጭት በነበረባቸው ከተሞች መታየቱን ለሬውተርስ ተናግረዋል። አብያተ-ክርስቲያናትን እና መስጂዶችን የማቃጠል ሙከራም ነበር ያሉት የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነር «ተቃውሞዎቹን ወደ የብሔር እና የሐይማኖት ግጭት ለመቀየር ድብቅ አጀንዳ ነበር» ሲሉ ተናግረዋል።

የድሬደዋ አስተዳደር መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ እስቅያስ ታፈሰ በአንዳንድ አካባቢዎች እስከ ትናንት አርብ የዘለቀው ኹከት እና ብጥብጥ በሁሉም የከተማው አካባቢዎች እንዲስፋፋ ብሔር ተኮር ጥቃቶች መፈፀማቸውን ገልፀው በዘረፋው «ከሌላ አካባቢ የመጡና በቡድን የተደራጁ ሰዎች» ተሳትፈዋል ብለዋል። ኃላፊው በወቅቱ የኃይማኖት ግጭት እንዲፈጠር ጥረት ተደርጓል ሲሉም አክለዋል። ኃላፊው እንዳሉት በግጭቱ እጃቸው አለበት ተብለው የተጠረጠሩ 110 ግለሰቦች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ ተጀምሯል።

መሳይ ተክሉ

እሸቴ በቀለ

ልደት አበበ