1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በድሬደዋ አንድ ሕጻን በተባራሪ ጥይት ተመቶ መሞቱን ፖሊስ ገለጸ

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 22 2014

በድሬዳዋ ከተማ ትላንትናው ዕለት በጎንደር የተፈጸመውን ግድያ ለማውገዝ የተካሔደ የተቃውሞ ሰልፍ ወደ ኹከት በተቀየረበት ወቅት በተተኮሰ ተባራሪ ጥይት አንድ የአራት አመት ልጅ መገደሉን ፖሊስ አስታወቀ። የድሬዳዋ ፖሊስ መምሪያ በሰጠው መግለጫ 22 አባላቱ መጎዳታቸውን፣ ባንኮች እና ተሽከርካሪዎች የጥቃት ሰለባ መሆናቸውን ገልጿል።

https://p.dw.com/p/4Af4t
Äthiopien Dire Dawa | Gemechu Kacha, Polizei
ምስል Messay Teklu/DW

በድሬደዋ አንድ ሕጻን በተባራሪ ጥይት ተመቶ መሞቱን ፖሊስ ገለጸ

በድሬዳዋ ከተማ ትላንትናው ዕለት በጎንደር የተፈጸመውን ግድያ ለማውገዝ  የተካሔደ የተቃውሞ ሰልፍ ወደ ኹከት በተቀየረበት ወቅት በተተኮሰ ተባራሪ ጥይት አንድ የአራት አመት ልጅ መገደሉን ፖሊስ አስታወቀ። የድሬዳዋ ፖሊስ መምሪያ በሰጠው መግለጫ 22 አባላቱ መጎዳታቸውን፣ ባንኮች እና ተሽከርካሪዎች የጥቃት ሰለባ መሆናቸውን ገልጿል።

በድሬደዋ አንዳንድ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው የጎዳና ላይ ሁከትና ረብሻ አንድ የአራት አመት ታዳጊ በተባራሪ ጥይት መሞቱን እንዲሁም በሃያ ሁለት ፖሊስ አባላት ላይ ቀላልና ከባድ ጉዳት መድረሱን የድሬደዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ። ሰማንያ ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጿል።

Äthiopien Dire Dawa | Straßenszene
በድሬዳዋ ትናንት አርብ ከሰዓት በኋላ የተፈጥረውን ሁከት ተከትሎ ተዘግተው የነበሩ ባንኮች እና ሌሎች ተቋማት ዛሬ ስራ የጀመሩ ሲሆን በከተማው ያለው እንቅስቃሴም ወደ ቀድሞ ተመልሷል።ምስል Messay Teklu/DW

በድሬደዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት እና የለውጥ ስራዎች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮማንደር ገመቹ ካቻ ሁከቱን ለቆጣጠር በነበረው ሂደት አንድ የአራት አመት ህፃን በተባራሪ ጥይት ተመቶ መሞቱን እንዲሁም ሃያ ሁለት የፖሊስ አባላት ላይ ከባድ እና ቀላል ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል። መረጃው ለጊዜው ባይደራጅም በንብረትም ላይ ጉዳት ደርሷል ብለዋል።

ሰማንያ ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች ተይዘው ምርመራ እየተካሄደ እንደሚገኝ ኮማንደር ገመቹ አስረድተዋል። በቀጣይ የሚከበረው የኢድ አልፈጥር በዓል ሰላማዊ እንዲሆን ፖሊስ ወደ ስራ መግባቱን የጠቀሱት ኮማንደሩ "በየትኛውም አግባብ ሰልፍ አደራጅቶ ህገ-ወጥ እንቅስቃሴ በሚያደርግ ማንኛዉም አካል ላይ ፖሊስ እርምጃ ይወስዳል" ብለዋል።

Äthiopien Dire Dawa | Biruk Feleke, Regierungskommunikation
የድሬደዋ አስተዳደር የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ብሩክ ፈለቀምስል Messay Teklu/DW

"ድርጊቱ የትኛውንም እምነት የማይወክል ነው" ያሉት የድሬደዋ አስተዳደር የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ብሩክ ፈለቀ የአስተዳደሩ ፀጥታ ምክር ቤት "ምንም ዓይነት ሰልፍ እንዳይካሄድ ውሳኔ" ማሳለፉን ገልፀዋል።

ትናንት ከሰዓት በከተማዋ የተፈጥረውን ሁከት ተከትሎ ተዘግተው የነበሩ ባንኮች እና ሌሎች ተቋማት ዛሬ ስራ የጀመሩ ሲሆን በከተማው ያለው እንቅስቃሴም ወደ ቀድሞ ተመልሷል።

መሳይ ተክሉ

እሸቴ በቀለ