በድህነት አንፃር የሚደረገው ትግልና የምግብ አቅርቦት አስተማማኝነት | ኤኮኖሚ | DW | 15.04.2004
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

በድህነት አንፃር የሚደረገው ትግልና የምግብ አቅርቦት አስተማማኝነት

ከቅርብ ጊዜ በፊት ስለ አስተማማኝ የምግብ አቅርቦት በካምፓላ/ኡጋንዳ አንድ ዓለምአቀፍ ጉባኤ በተካሄደበት ወቅት እንደተመለከተው፣ ድህነት በበዛበት በአፍሪቃው አህጉር ረሃብን ለመግታት የሚያስችለው አንዱ ቁልፍ ርምጃ፣ ከዘመናት በፊት ጀምረው ያንኑ አህጉር የሚያተራምሱት ውዝግቦች ውገዳ ነው።

አፍሪቃ ውስጥ እ ጎ አ እስከ ፪ሺ፳ ድረስ ረሃብ ለሚቀረፍበት ግብ የርምጃ ስልቶችን ለሚፈትሸው ዓለምአቀፍ ጉባኤ ንግግር ያሰሙት የቀድሞው የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚደንት ኔልስን ማንዴላ ባልተቤት እና የሕፃናት መብት ተሟጋች ግራካ ማሼል እንዳስገነዘቡት፣ በዚያው በአፍሪቃው አህጉር የምግቡ አቅርቦት አስተማማኝ እንዳይሆን የሚያደርገው፣ ፀረድህነቱንም ርምጃ የሚያሰናክለው፣ በተለይ የውዝግቦች አለመወገድ ነው።

ባሁኑ ጊዜ አፍሪቃ ውስጥ የምግብ እጥረት የሚደርስባቸው ሰዎች አሃዝ በ፪፻-ሚሊዮን ነው የሚገመተው፤ አንፃሩ ርምጃ ተፋጥኖ ካልተንቀሳቀሰ በስተቀር ይኸው አሃዝ ይብሱን የሚያሻቅብ እንደሚሆን ነው የሚታሰበው። የኡጋንዳ፣ የሴኔጋልና የናይጀሪያ ፕሬዚደንቶች ዮዌሪ ሙሴቬኒ፣ ዓብዱላይ ዋድ እና ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ፣ እንዲሁም ከ፴፭ ያህል የአፍሪቃ ሀገሮች የተውጣጡ ፭፻ ሚኒስትሮች፣ የልማት ጠበብትና ገበሬዎችም ለተሳተፉበት ዓለምአቀፍ ጉባኤ እንደተመለከተው፣
ኅብረተሰቡን የሚያተራምሱት ውዝግቦች እንዲወገዱ በመጀመሪያ ጥረቱ ካልተጠናከረ በስተቀር፣ የምግቡን አቅርቦት ለማሻሻል ማቀድ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። ወይዘሮ ማሼል እንዳስገነዘቡት፣ አፍሪቃ ውስጥ እስካሁን ለጦር-ትጥቅና ለውጊያ ሲከሰከስ የቆየው ብሔራዊ ጥሪት እየተቆጠበ፣ የምግብ አቅርቦት አስተማማኝ ወደሚሆንበት፥ እያንዳንዱ ሰው በቂ ምግብ ለማግኘት ወደሚችልበት የልማት መርሐግብር መቀልበስ በተገባውም ነበር።

ረሃብን ለማስወገድ በፖለቲካዊ የኃላፊነት ስሜት ቆርጦ መነሳት አስፈላጊ እንደሚሆን የሚያስገነዝበው የተባ መ የምግብና የእርሻ ድርጅት/ፋኦ፣ የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት ለማነቃቃትና የምግብን አቅርቦት አስተማኝ ለማድረግ የሚያስችለው የፊናንሱ ድጋፍ/ ማለት በመንግሥታዊና በግላዊ ደረጃ የሚንቀሳቀሰው ውዒሎተንዋይ እንዲሻሻል በጥብቅ ነው ያሳሰበው። በድርጅቱ ጥናት መሠረት፣ በአፍሪቃው አህጉር ሊለማ ከሚችለው መሬት ሰባት በመቶው ብቻ ነው በመስኖው መረብ አማካይነት የሚለማው፤ በዚህ አንፃር ደግሞ የእስያው ፵ በመቶ ነው፤ ቀጥሎም አፍሪቃ ውስጥ ካለው የውሃ ክምችት አራት በመቶው ብቻ ነው ለመስኖ ልማት የሚውለው--በንጽጽር ደግሞ የእስያው ፲፯ በመቶ ነው።

የአውሮጳው ኅብረት የልማትና የሰብዓዊ ጉዳዮች ተጠሪ ፖል ኒልሶን እንደሚሉት፣ በሌሎቹ አዳጊ ሀገሮች ውስጥ የምግብ እጥረት የሚደርስባቸው ችግረኞች አሃዝ ከጊዜ ወደጊዜ እየተቀነስ ነው የተገኘው፣ በሰሐራ ደቡቡ የአፍሪቃ ከፊል ግን የተለወጠ ነገር የለም። የአውሮጳው ኅብረት አፍሪቃ በምግብ አቅርቦት ራስአገዝ የምትሆንበትን ርዳታ ወደፊትም የሚቀጥልበት ቢሆንም፣ የኋላ ኋላ ልማት በራሳቸው በሚደረጁት ሀገራት ርምጃ ላይ የሚመረኮዝ እንደሚሆን ኒልሶን አስገንዝበው ነበር፤ አፍሪቃውያኑ መሪዎች ግን ምዕራባዊው ዓለም ራሱ የሚደነቅነውን የንግድ መሰናክል በማስወገድ፣ አፍሪቃውያኑ ገበሬዎች ይበልጥ እህል እንዲያመርቱ ማበረታታት እንደሚገባው በካምፓላው ጉባኤ ላይ በጥብቅ ነበር ያስገነዘቡት። “አስተማማኝ ገቢ ከሌለ፣ የምግቡም አቅርቦት አስተማማኝ ሊሆን አይችልም፤ ነፃ ገበያ እንዲኖር እየተለፈፈ፣ ንግድን መከለል ተገቢ አይደለም” ይላል የኡጋንዳው መሪ ዮዌሪ መሴቬኒ ለምዕራቡ ዓለም ያጎሉት ማስገንዘቢያ። የናይጀሪያ መሪ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ደግሞ፥ “ምዕራባውያን ለገበሬዎቻቸው ድጎማ በቀን አንድ ሚሊያርድ ዶላር በሚያፈስሱበት ጊዜ፣ አፍሪቃውያን በቀን ከአንድ ዶላር ባነሰ ወጭ እንዲኖሩ ይገደዳሉ፣ ለአንዲት የአውሮጳ ላም ግን በቀን ከሁለት ዶላር የሚበልጥ ድጎማ ይከፈላል--በዚህ አኳኋን የውድድር አቅም የሚነሳቸው አፍሪቃውያን የአውሮጳው ገበያ በኢርቱእ ዝግ ነው የሚሆንባቸው” የሚለውን ስሞታ ነበር ያጎሉት። በሌላም አጋገር እንግዲህ፣ አፍሪቃ ውስጥ የምግቡ አቅርቦት አስተማማኝ እንዲሆን የሚደረገው ጥረት የሚቃናበት አንዱ መንገድ፥ ምዕራቡ ለግብርናው ዘርፍ የሚያፈስሰውን ሚሊያርድ ድጎማ እያስወገደ፣ አፍሪቃውያኑ የገበያ ውድድር አቅም የሚያገኙበትን ዕድል እንዲከፍት ይጠየቃል ማለት ነው።


አፍሪቃ ውስጥ የምግብን አቅርቦት አስተማማኝ ለማድረግ የሚያስችለው ሌላው መስፈርት የሕዝብ ጤንነት ነው። የአምራች ኅብረተሰቡ ጤንነት ጉድለት የልማቱን ርምጃ ከንቱ እያደረገ ነው የሚያስቀረው። በዚህ ረገድ በተለይ የሚጠቀሰው፣ አፍሪቃ ውስጥ ቀሳፊው በሽታ ኤድስ ምሁራንን እና አምራቹን የሠራተኛ ኃይል እያጓደለ የኤኮኖሚው እንቅስቃሴ ኃይል እንዲያጣ የሚያደርግበት ከባድ ቀውስ ነው። ሆኖም፣ አሁን ይኸው የሕይወትና የኤኮኖሚ ጠንቅ ሊገታ የሚበቃበት ተሥፋ የተፈነጠቀ መስሎ ነው የሚታየው። ይኸውም፣ ኤድስን ማስታገሻው መድኃኒት በጣም በተቀነሰ ዋጋ ለድሆቹ ሀገሮች እንዲዳረስ የሚደረግበት ሁኔታ ነው። የዓለም ባንክ ባለፈው ሣምንት ዋሽንግተን ውስጥ በሰጠው መረጃ መሠረት፣ በቀድሞው ያሜሪካ ፕሬዚደንት ክሊንተን ስም የሚጠራው ፀረ-ኤድስ ድርጅት ከመድኃኒት አምራቾቹ ኩባንያዎች ጋር የደረሰው ስምምነት የሚደረጁት ሀገሮች እጅግ በተቀነሰ ዋጋ መድኃኒቱን ሊገዙና የኤድሱንም ምርመራ በቀላሉ ሊያካሂዱ ይችላሉ። በዚህ አኳኋን፣ በጠበብቱ ግምገማ መሠረት፣ እስከመጭው ዓመት ድረስ በድሆቹ ሀገሮች ውስጥ ፫ ሚሊዮን ኤድስ-ሕሙማንን አሟልቶ በሕክምና ለመንከባከብ እንዲቻል የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት የተለመው ግብ እውን የሚሆንበት ጊዜ የተቃረበ ሆኖ ነው የሚታየው።

በኤድስ አንፃር የሚደረገውን ትግል ከዋነኛ ተግባራቱ መካከል አንዱ በማድረግ የሚንቀሳቀሰው የቀድሞው ፕሬዚደንት ክሊንተን ድርጅት ማስታገሻው መድኃኒት በተቀነሰ ዋጋ እንዲቀርብ ለማድረግ ያስቻለው፣ ከአንድ የደቡብ አፍሪቃና ከአራት የሕንድ ሥራይ-አምራች ኩባንያዎች ጋር የደመደመው ስምምነት ነው። የዓለም ባንክ አሁን በሰጠው መረጃ መሠረት፣ አንዱን የኤድስ ሕሙም ለማከም በዓመት አሁን ፩፻፵ ዶላር ወይም ፩፻፲፯ ኦይሮ ብቻ ነው የሚፈጀው፥ ይህም ከተለመደው የዋጋ ደረጃ አንድ-ሦሥተኛው ነው።

በጣም እንዲቀነስ የተደረገው የኤድስ ማስታገሻ መድኃኒት ዋጋ እስካሁን በ፲፮ የአፍሪቃና የከራይብ ሀገሮች ነው የተሰራበት። ካሁን ወዲያ ግን በጠቅላላው ፩፻፳፪ ሀገሮች በዚያው በርካሹ ዋጋ ሊጠቀሙ እንዲችሉ ይደረጋል ነው የሚባለው። ግን፣ ይህንኑ የቅናሽ ዋጋ አገልግሎት የሚሹት መንግሥታት በመጀመሪያ የክፍያ ዋስትና እንዲሰጡ፣ የረዥም ጊዜ የመድኃኒት አቅርቦት ኮንትራት እንዲዋዋሉ፣ መድኃኒቱንም ለተጠቃሚዎቹ በትክክል የሚያሰራጩበትን ማረጋገጫ እንዲያቀርቡ ግዴታ አለባቸው። ለዚህ ሁሉ ርምጃ፣ የዓለም ባንክ፣ የተባ መ የሕፃናት መርጃ ድርጅት/ኡኒሴፍ፣ እና እንዱስትሪ-ኩባንያዎች፣ መንግሥታት፣ እንዲሁም ኤድስን፣ ሳምባነቀርሳን እና ወባን ለመከላከል የተነሳሱት ግብረሠናይ ድርጅቶች የሚጣመሩበት “ግሎባል ፈንድ” የተሰኘው አካል አነቃቂ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በሚደረጁት ሀገሮች ውስጥ ዛሬ ኤድስ ያለባቸው ሰዎች አሃዝ ስድስት ሚሊዮን እንደሚደርስ ነው የሚገመተው። ግን ከእነዚሁ መካከል አሁን ለጊዜው ፪፻ሺ ያህሉ ብቻ ናቸው በእንዱስትሪ-ሀገሮች ውስጥ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኤድስ ምክንያት የሚሞቱትን ሰዎች አሃዝ በጉልህ ለመቀነስ ያስቻለውን መድኃኒት የሚያገኙት። ካሁን ወዲያ ግን፣ በተቀነሰው ዋጋ ምክንያት የመድኃኒቱ ተጠቃሚዎች አሃዝ ተፋጥኖ የሚጨምር እንደሚሆን ነው ተሥፋ የሚደረገው።

ተዛማጅ ዘገባዎች