በደቡብ አፍሪቃ የውጭ አገር ዜጎች ላይ የደረሰው ጥቃት | አፍሪቃ | DW | 13.04.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

በደቡብ አፍሪቃ የውጭ አገር ዜጎች ላይ የደረሰው ጥቃት

በደቡብ አፍሪቃ የውጭ አገር ሰዎች ላይ የሚደርሰው ተቃውሞና ጥቃት ተባብሶ ቀጥሏል። ባለፈው ሳምንት አርብ በተኙበት በእሳት ከተቃጠሉ ሁለት ኢትዮጵያውያን መካከል አንደኛው መሞቱን ዜና ምንጭ ሮይተርስ ዘግቧል።

በደቡብ አፍሪቃ የውጭ አገር ሰራተኞች ላይ በተነሳ ተቃውሞ በተኙበት እሳት ተወርውሮባቸው ከተቃጠሉት ሁለት ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ መሞቱን ሬውተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።ሁለቱ ወንድማማቾች በእሳት የተቃጠሉት ባለፈው አርብ በደርባን ከተማ ኡልማዚ በተባለ አካባቢ በሱቅ ሳሉ ነበር። ኒውስ 24 የተሰኘው ጋዜጣ ያነጋገራቸው ኢትዮጵያዊ በእሳት ከተቃጠሉት መካከል የአንዱ ህይወት ማለፉን ከሆስፒታል ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል። ከፍተኛ ቃጠሎ የደረሰበት ሁለተኛው ኢትዮጵያዊ በሆስፒታል በማገገም ላይ ነው ተብሏል። በርካቶች የመኖሪያ ቤቶቻቸውን ጥለው ሸሽተዋል። እስካሁን ድረስ የአገሪቱ መንግስት 28 ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውሏል

በውጭ አገር ዜጎች ላይ የተነሳውን ተቃውሞና የተፈጸሙ ጥቃቶች የሚያሳዩ አሰቃቂ ምስሎች በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ ታይተዋል። በጥቃቱ የዚምባብዌና ሶማሊያ ዜግነት ያላቸው ነዋሪዎችና ሰራተኞች ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ተሰምቷል። ዚህ ኢዝ አፍሪካ የተሰኘ ድረ-ገጽ በተቃዋሚዎች የተፈጸሙ ዘረፋዎችንና ድብደባዎችን እንዲሁም በቁማቸው ነዳጅ ተርከፍክፎባቸው የሚቃጠሉ ሰዎችን የሚያሳዩ ቪዲዮችን ይፋ አድርጓል። ይህን መሰል ጥቃት በደቡብ አፍሪቃ አዲስ ባይሆንም ጉድዊል ዝዌሊቲኒ የተባሉ የዙሉ ንጉስ «ከአገራችን ስደተኞች መውጣት አለባቸው የሚለውን መልዕክት ለህዝብ ካስተላለፉ በኋላ በጥቂት ቀናቶች ውስጥ ህዝቡ አላስፈላጊ እርምጃ በመውሰድ ንብረቱን በመዝረፍና በማቃጠል እንዲሁም በመደብደብ ላይ ናቸው።»በማለት የተቃውሞና ጥቃቱን ጅማሮ አቶ ታምሩ አበበ ይናገራሉ።

Fremdenhass in Südafrika, Flüchtlinge

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት አጥብቀው በኮነኑት ተቃውሞና ጥቃት ከ 250 በላይ የውጭ አገር ሰዎችና ሰራተኞች ኢላማ ሆነዋል ተብሏል። የአገሪቱ ፖሊስ በተለይ በደርባን ከተማ ኢስፒንጎ በተባለ አካባቢ ለተፈጸመው ጥቃት ምላሽ ለመስጠት ዘገምተኛ ሆኗል ሲሉ የደቡብ አፍሪቃ ጋዜጦች ተችተዋል። አቶ ታምሩ አበበ «ከአራት ቀን በፊት ኢትዮጵያውያኖች ከሌሎች ስደተኞች ጋር በመሆን ሰላማዊ ሰልፍ በሚደረግበት ጊዜ ፖሊስ አስቁሟቸው ቀለል ያሉ ጉዳቶች ደርሰዋል» በማለት አፍሪቃውያን ስደተኞች ጥቃቱን ለመቃወም ቢሞክሩም እንዳልተሳካላቸው ተናግረዋል።

ደቡብ አፍሪቃ በአለም ከፍተኛ የስራ አጥነት ችግር ከሚታይባቸው አገሮች መካከል አንዷ ነች። እድሚያቸው ከ35 አመት በታች ከሆኑ ደቡብ አፍሪቃውያን መካከል 70 በመቶው ስራ አጥ እንደሆኑ ይነገራል። ባለፈው አመት ከአጠቃላይ ደቡብ አፍሪቃውያን 24.3 በመቶው ስራ አጥ የነበሩ ሲሆን ችግሩ እየተባባሰ ሊሄድ እንደሚችል የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በአብዛኛው ወጣት ደቡብ አፍሪቃውያን የተሳተፉበት በውጭ አገር ሰዎች ላይ የተጀመረው ተቃውሞና ጥቃት ዋነኛ መነሾ ይህ የስራ አጥነት እና የስራ ቅርምት ነው ተብሏል።

እሸቴ በቀለ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic