በደቡብ አፍሪቃ የቀጠለው የውጭ ዜጎች ጥቃት እና የሽብር ስጋት በሶማሊያ | አፍሪቃ | DW | 19.09.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

በደቡብ አፍሪቃ የቀጠለው የውጭ ዜጎች ጥቃት እና የሽብር ስጋት በሶማሊያ

ደቡብ አፍሪቃ  በስደተኞች ጥላቻ እና የኃይል ጥቃቶች ጋር ስትታገል ዓመታትን አስቆጥራለች። ባለፈው ዓመት መስከረም  በሺዎች የሚቆጠሩ ጥቁር ደቡብ አፍሪቃውያን ስደተኞችን በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ባደረጉ ወቅትም በሀገሪቱ ለሚታየው ሥራ አጥነትና ወንጀል  ስደተኞችን ተጠያቂ አድርገዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:28

ትኩረት በአፍሪካ መስከረም 09/2013 ዓ/ም

በደቡብ አፍሪቃ ተባብሶ የቀጠለው የውጭ ዜጎች ጥቃት እንዲሁም አልሸባብ ከመጭዉ የሶማሊያ ሀገራዊ ምርጫ በፊት የሽብር ጥቃቶችን ሊፈፅም ይችላል መባሉ።የዛሬው የትኩረት በአፍሪቃ ዝግጅት የሚዳስሳቸው ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው።

ደቡብ አፍሪቃ  በስደተኞች ጥላቻ እና የኃይል ጥቃቶች ጋር ስትታገል ዓመታትን አስቆጥራለች። ባለፈው ዓመት መስከረም  በሺዎች የሚቆጠሩ ጥቁር ደቡብ አፍሪቃውያን ስደተኞችን በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ባደረጉ ወቅትም በሀገሪቱ ለሚታየው ሥራ አጥነትና ወንጀል  ስደተኞችን ተጠያቂ አድርገዋል። በዚህ ተቃውሞ   ንብረትነታቸው የውጭ ዜጎች የሆኑ መደብሮች የተዘረፉ ሲሆን በሁከቱም የሰው ህይወት ጠፍቷል  የአካል ጉዳትም እንዲሁ።

ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ድርጅት «ሂውማን ራይትስ ዎች» በቅርቡ ባወጣዉ ዘገባ  በደቡብ አፍሪቃ የውጭ ዜጎች ጥቃት  እየጨመረ መምጣቱን አመልክቷል። በጥቃቶቹ በርካታ በሀገሪቱ የሚገኙ የውጭ ዜጎች ሰለባ ቢሆኑም ፤ጥቃት ያደረሱ ከባድ ወንጀለኞችን ከአጭር ጊዜ እስር በኋላ መልቀቅ ወይም በጭራሽ ክስ አለመመስረት እንዲሁም ለህጋዊ ስደተኞች የመታወቂያ ወረቀቶች መከልከልና  ያለበቂ ምክንያት በእስር ማንገላታትን  የመሳሰሉ አድሎአዊ አሰራሮች በደቡብ አፍሪቃ በውጭ ዜጎች ላይ ይፈፀማል ፡፡ 

በዚህም በርካታ የውጭ ዜጎችና ቤተሰቦቻቸው የደህንነት ስጋት አንዣቦባቸዋል።የዕለት ተዕለት ህይወታቸውንም በአግባቡ ማከናወን አይችሉም።ኮንጓዊቷ ዶኔት ኒጎኒፊም ያጋጠማት ይሄው ነው።ዶኔት በዚህ ወቅት ትምህርት ቤት መሄድ  የነበረባት ቢሆንም፤ በደህንነት ስጋት ከቤተሰቦቿ ጋር ቤት ውስጥ መቆየትን መርጣለች።

"በየቀኑ ወደ ትምህርት ቤት አልሄድም ፡፡ ትምህርቴ ላይም ማተኮር አልችልም። ህይወቴ ተመሰቃቅሏል። ምርጫ ቢኖረኝ  ኖሮ እዚህ አልኖርም።ይህንን ሀገር  ለዘላዓለም ለቅቄ እወጣ ነበር።»

ከ 9 ዓመታት በፊት ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በስደተኝነት ወደ ኬፕታውን የመጡት የዶኔት ወላጆች የተሻለ ሕይወት ተስፋ አድርገው ነበር። ዶኔት በትምህርቷ ጥሩ ውጤት ያላት ተማሪ ነች። ይህንን የተመለከቱ አስተማሪዎቿም የክፍል አለቃ አድርገው መርጠዋታል።በክፍል ጓደኞቿ  ዘንድ ግን ተቀባይነት አላገኘም።

«ምክንያቱም እነሱ  የሚፈልጉት ሌላ ተማሪ  የክፍል አለቃ እንዲሆን ነው። ደቡብ አፍሪቃዊ የሆነ ሌላ ሰው።ሁል ጊዜ አንቺ ደቡብ አፍሪቃዊ አይደለሽም።አንቺ የውጭ ዜጋ  ነሽ። እኛ የምንሰራውን ስራ ለመንጠቅ ወደ ሀገራችን መምጣት አትችይም።ሁል ጊዜ ይህንን ነው የሚሉኝ።

ከአንድ ዓመት በፊትም ከክፍል ጓደኞቿ  በደረሰባት ድብደባ ሆስፒታል ገብታ ነበር።

« ደበደቡኝ  የተወሰኑት ሆዴ ላይ ረጋገጡኝ። አንዲት ጓደኛዬ ልትረዳኝ ፈልጋ ነበር ፤ግን  ምንም ማድረግ አልቻለችም። ምክንያቱም ወለል ላይ ወድቄ መላው የክፍል ተማሪ እየደበደበኝ  ነበር። አስተማሪው እንኳ ምንም ማድረግ አልቻለም።ዝም ብዬ አለቀስኩ። ምክንያቱም ማንም ሊረዳኝ አልቻለም ነበር።»ብላለች እንባ እየተናነቃት።

ከጆሃንስበርግ የአፍሪካ ዲያስፖራ ፎረም አሚር ሸክ እንደሚሉት፤ እንደ ዶኔት ባሉ የውጭ ዜጎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት የተለመደ ነው። 

«በየዕለቱ እንዲህ አይነት ነገር  ያጋጥመናል። ከሶማሌ ማኅበረሰብ ብቻ በአማካኝ በየቀኑ አንድ ሰው እናጣለን።በተመሳሳይ ሁኔታም ባንግላዲሽ እና ኢትዮጵያውያንም ይገደላሉ። በቅርብ ጊዜ ውስጥ በቶኮዛ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ የውጭ ዜጎች መደብሮች ተዘርፈዋል ሰዎችም ተፈናቅለዋል።ይህ በየቀኑ ይከሰታል ።ነገር ግን በመገናኛ ብዙሃን የሚቀርቡት የጅምላ ጥቃቶች ብቻ ናቸው።»ብለዋል።

የከተማ ንግድ በውጭ ዜጎች ጥላቻ ለሚፈፀም ጥቃት ዋነኛ ምክንያት  መሆኑን የሚገልፁት ሶማሊያዊው አሚር ሸክ፤ የደቡብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ችግሮች ውጥረቱን የበለጠ ሊያባብሰው ይችላል ባይ ናቸው።ምክንያቱም በኮሮና ወረርሽኙ ሳቢያ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች በደቡብ አፍሪቃ ሥራቸውን አጥተዋልና።የሳቸው ድርጅት በሳምንት አንድ ጊዜ የምግብ ስርጭቶችን ያስተባብራል።«አድልኦ ስለተፈፀመብህና ስለተገለልክ አድሎ መፈፀም የለብህም።» በሚል መሪ ቃልም በችግር ላይ ላሉና እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ደቡብ አፍሪቃውያን የምግብ ልገሳ ያደርጋሉ።

ሸኪ እንደሚሉት በደቡብ አፍሪካ እየጨመረ የመጣውን ውጥረት ለማርገብ  የዘረኝነትን አስከፊነት በተመለከተ ሰዎችን ማስተማር አስፈላጊ ነው። 

በሌላ በኩል የደቡብ አፍሪቃ መንግስት በወረርሽኙ የተከሰተውን ኢኮኖሚያዊ ችግር ለማቃለል የ25 ቢሊዮን ዩሮ  የእርዳታ መርሀ-ግብር  አቋቁሟል። ነገር ግን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተገን ጠያቂዎች ፣ ስደተኞች እና ሰነድ አልባ ስደተኞችን ተጠቃሚ አይደሉም። ምንም እንኳ በሀገሪቱ የውጭ ዜጎች ጥላቻ ቢኖርም አንዳንድ ደቡብ አፍሪቃውያን በዚህ ጉዳይ መንግስታቸውን ይተቻሉ።

«እዚህ ስላልተወለዱ ብቻ የውጭ ዜጎችን መተው ፍትሃዊ አይደለም። እዚህ የመጡት ኢኮኖሚያችንን ለማገዝ ነው። ስለሆነም እርዳታ በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ልንረዳቸው ይገባል።»

ወደ ኬፕታወን ስንመለስ ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ  የመጣችው  ዶኔት ኒጎፊኒ የዘረኝነትና የመድሎ ሰለባ የሆኑ ሌሎች ህፃናትን ለመርዳት አንድ ቀን የህግ ባለሙያ የመሆን ህልም አላት፡፡ለጊዜው ግን እሷን የደበደቧት የክፍል ጓደኞቿ በፈፀሙት ድርጊት  አልተቀጡም።

 የሽብር ስጋት በሶማሊያ

ከአልቃይዳ ጋር  ግንኙነት እንዳለው የሚነገርለት የአልሻባብ ታጣቂ ቡድን በቅርቡ የሶማሊያ ብሔራዊ ጦርን ፣ በደቡባዊ ሶማሊያ የሚገኙ የመንግስት የጦር ሰፈሮችንና ሰላማዊ ሰዎችን  ዒላማ ያደረጉ በርካታ ጥቃቶችን  ፈፅሟል።በዚህ ጥቃት ወታደራዊ መኮንኖችን ጨምሮ  በርካታ ሰዎች ተገድለዋል፡፡አልሸባብ በዋናነት ከአሜሪካ ጦር የአየር ድብደባ እየደረሰበት ቢሆንም ፣ ታጣቂው ቡድኑ  በመንግስትና በዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት አጠናክሮ ቀጥሏል።ባለፈው አንድ ሳምንት ብቻ በመላው የአፍሪካ ቀንድ ወደ 14 የሚጠጉ በታጣቂ ቡድኑ የተፈፀሙ የሽብር ጥቃቶችም  ተመዝግበዋል ።

ጥቃቱ እየጨመረ የመጣው ደግሞ ሀገሪቱ በዚህ ዓመት መጨረሻ ምርጫ ለማካሄድ  በዝግጅት ላይ ባለችበት ወቅት ነው።ያ በመሆኑ አልሸባብ  ከመጭዉ የሶማሊያ ሀገራዊ ምርጫ በፊትም በርካታ የሽብር ጥቃቶችን ሊፈፅም ይችላል የሚል ስጋት አሳድሯል።

የቀድሞው የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ  እና በአሁኑ ወቅት ሂራል የተባለው የሞቃዲሾ የደኅንነት ጥናት ተቋም መስራችና ዋና ዳይሬክተር  የሆኑት ሁሴን ሸኪ አሊ ለተባባሰው የፀጥታ ችግርና ለአልሸባብ ጥቃት መባባስ ምክንያት ናቸው ከሚባሉት በርካታ ጉዳዮች ውስጥ ሶስቱን ይጠቅሳሉ።  

«የመጀመሪያው በአጋሮች ውጤታማ የሆኑ የአፀፋ ርምጃዎች  ካልተወሰዱ፤ ማለትም የሶማሊያ ፌዴራላዊ መንግሥት፣የክልል ግዛቶች፣በአፍሪካ ህብረት ኃይሎች ና በአሜሪካ አየር  ሀይል ድጋፍ ካላደረጉ ፣ በሁለተኛ ደረጃ  በአየር ሁኔታ በዝናብ ወቅት የጎርፍ  አደጋ  ተልዕኮውን የሚጎዳ ከሆነ ፣ሶስተኛው  ጦርነት ለማካሄድ  የሚስፈልጉ ቁሳቁሶች  በቂና የተመጣጠኑ ካልሆኑ፤ በቅርቡ አልሸባብ በመላ ሀገሪቱ ተልዕኮውን አጠናክሮ  ሊቀጥል ይችላል።»

በሌላ በኩል በቀጣይ በሚካሄደው የምርጫ መመሪያ ላይ በክልል አመራሮች እና በፌዴራል መንግስቱ መካከል  ተፈጥሮ የነበረው አለመግባት ለሀገሪቱ ሌላው ስጋት ሲሆን፤ ሁለቱ ወገኖች በሞቃዲሾ ለቀናት ባካሄዱት  ውይይት  ውዝግቡ መፍትሄ ያገኘ ይመስላል። 

መሪዎቹ ከ 2016 የምርጫ ሂደት ጋር ተመሳሳይ የሆነ ቀጥተኛ ያልሆነ ምርጫ ህዳር 1 ቀን ለመጀመር  ተስማምተዋል ። ከዚያ በኋላ 101 የምርጫ ልዑካን ፕሬዚዳንቱን የሚሰይሙ የፓርላማ አባላትን ይመርጣሉ።ይህ ስምምነት በሀገሪቱ ምርጫውን ተከትሎ የታዩ ስጋቶችን የሚቀርፍ ቢሆንም፤ በፀጥታ ተግዳሮቶች እና በፖለቲካ ፉክክር ሳቢያ ሂደቱ በጉዞው ላይ መሰናክሎች ያጋጥሙት ይሆናል የሚሉ አሉ።

በምርጫ ሂደት ላይ አለመግባባትን በተመለከተ የደህንነት ተንታኙ ሁሴን በመሪዎቹ መካከል ትብብር አለመኖር የበለጠ የፀጥታ ችግር ሊፈጥር ይችላል የሚል ስጋት አላቸው ፡፡

«ሀገሪቱ እርግጠኛ ባልሆነ የምርጫ ሰሌዳ ውስጥ እየገባች ነው።ምክንያቱም እስካሁን ስምምነት የለም።ይህም አልሸባብ  በህዝቡ ላይ የሚያደርሰው ስቃይና የደህንነት ስጋት የበለጠ እንዲጨምር ያደርጋል።»

ይሁን እንጅ ከፌዴራል መንግስት እና ከክልል መንግስታት የተውጣጡ አመራሮች በመጪው ምርጫ ላይ ሰሞኑን ስምምነት ሲያደርጉ፤ የሶማሊያ የፓርላማ አባላት በሂደቱ ውስጥ ለመሳተፍ በተወካዮች ደህንነት ላይ ስጋት ነበራቸው።ምክንያቱም ከዚህ ቀደም አልሸባብ የቀድሞ የምርጫ ልዑካንን  ዒላማ ያደረገ ጥቃት በመፈፀም በርካታ ሰዎች  በተለያዩ ከተሞች ገድሏልና።

የቀድሞው የሶማሊያ ብሔራዊ መረጃና ደህንነት ኤጀንሲ ጄኔራል አብዲራሂም ሙሐመድ ቱርየር  በበኩላቸው የአልሸባብ ታጣቂዎች የመንግስት ተቋማን በማውደም  የመንግሥት ባለሥልጣናትን ለማስፈራራትና በምርጫው  ተስፋ ለማስቆረጥ እየሰራ ነው ብለው ያምናሉ። 

የጨመረው የአልሸባብ ጥቃት የመንግስት ባለስልጣናትን ብቻ ሳይሆን በሀገሪቱ   በሚገኙ የአሜሪካ ወታደሮችና የአፍሪቃ ህብረት ተልኮ በሶማሊያ ሀይሎች ላይም ተፅዕኖ ማሳደሩ አልቀረም።

ያም ሆኖ  የአሜሪካ ጦር በአየር ላይ በሚሰነዘሩ ጥቃቶች ቁልፍ የአልሸባብ ታጣቂዎችን እና የጦር ሰፈሮችን በማጥቃት ላይ ይገኛል።በዚህ መሰሉ የአየር ጥቃት የአሜሪካ ጦር በጎርጎሪያኑ ነሐሴ 25 ቀን አብዱልቃድር ኮማንዶ የተባለ አንድ ከፍተኛ የአልሸባብ ታጣቂን ገደልኩ ማለቱ ይታወሳል። 

በአጠቃላይ የሽግግር ጊዜ የሽብር ቡድኑ የመንግስትን የአገልግሎት መስጫዎችን ለማውደም ከሚሞክሩባቸው የምርጫ ወቅቶች ውስጥ አንዱ በመሆኑ የስጋት ድባብ ቢነግስም፤ በአሁኑ ወቅት ከሰላሳ ዓመታት የእርስ በእርስ ጦርነት ፣ የባህር ላይ ወንብድና እንዲሁም  ከፅንፈኝነት  አስተሳሰቦች የማገገም የተስፋ ምልክት በሀገሪቱ መኖሩን ተንታኞች ይገልፃሉ።

 

ፀሀይ ጫኔ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic