በደቡብ አፍሪቃ በአፍሪቃውያን ላይ የተፈጸመው ግፍ መንስኤ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 23.04.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

በደቡብ አፍሪቃ በአፍሪቃውያን ላይ የተፈጸመው ግፍ መንስኤ

በ 1950ኛዎና 1960ዎቹ ዓመታት ፤ የነበሩ የኢትዮጵያ ተማሪዎችና አስተማሪዎች፤ የኪነ ጥበብ ሰዎችና ጋዜጠኞች ፤ እንዲሁም የመንግሥት ባለሥልጣናትና ዲፕሎማቶች ፤ በነበራቸው አፍሪቃ አቀፍ አመለካከት (ፓን አፍሪካኒዝም) የአፍሪቃው ክፍለ ዓለም ከቅኝ አገዛዝ ፈጽሞ እንዲላቀቅ ጽኑ ፍላጎታቸው መሆኑ በተለያዩ መስኮች ይገለጥ ነበረ።

ታዋቂው ጸሐፌ -ተውኔት የዜማና ግጥም ደራሲ ተስፋየ አበበ ፣
«ቅኝ አገዛዝ ይጥፋ ይላል የጥቁር ድምጽ» (ለርእሱ ትክክለኛነት እርግጠኛ አይደለሁም ፣) በዚያ ታደለ በቀለና በኃይሉ እሸቴ በአንጎራጎሩት ዘፈን፤
«ቶሎ ይውጡ ነጻ ከዚያ ከኮሎኒ
አንጎላ ሞዛምቢክ የፖርቱጊስ ጊኒ»
ሮዴሺያና ደቡብ አፍሪቃም ተቃርቧል ጊዜአቸው በማለት፤ ከትውልድ ሀገር ባሻገር፣ የአፍሪቃ አቀፍ ፍቅርንና ተቆርቋሪነትን ያሳይ የነበረው ፣ የዚያ ዘመን ኢትዮጵያዊ ዜጋ ለቀጣዩ ትውልድ ያን ለአፍሪቃ ነጻነትና ሕብረት እንዲሁም የጋራ ብልጽግና አስፈላጊነት ፈር ማስያዙ አልቀረም። ቅኝ አገዛዝና የጥቂት ነጮች የዘር አድሎአዊ አገዛዝ (አፓርታይድ ) እንዲወገድ ፤ ኢትዮጵያ ትልቅ ድርሻ ማበርከቷ የሚካድ አይደለም። የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ያሁኑ የአፍሪቃ ሕብረት ማዕከል ፣ አዲስ አበባ ላይ እንዲሆን የተመረጠበትን ምክንያትም የ ክፍለ ዓለሙን ታሪክ የሚያውቁ አፍሪቃውያን ሁሉ የሚገነዘቡት ነው። የኢትዮጵያ ፤ ዲፕሎማሲያዊና ወታደራዊ ድጋፍ ፤ ደቡብ አፍሪቃ ግንባር ላይ የሚገኙ አጎራባች ሃገራት መስዋእትነት እንዲሁም ፣ የሌሎች፤ የነጻነት ፤ ፍትሕና ርትእ ወዳዶች ድጋፍ ታክሎበት፤ ከአያሌ ዘመናት ትግል በኋላ፣ እ ጎ አ በየካቲት 1990 ትልቁ የትግል

ዓርማ ኔልሰን ማንዴላ ከእሥራት ተለቀቁ ። የአፓርትይዱ ሥርዓትም ተሽሮ ደቡብ አፍሪቃ ፤ እ ጎ አ በ 1994 ዓ ም፤ የመጀመሪያውን አገር አቀፍ ነጻና ፍትኀዊ ምርጫ አካሂዳ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት መመሥረቷ የሚታወስ ነው። ጥያቄው፣ ያሁኑ የደቡብ አፍሪቃ ትውልድ እስከምን ድረስ ያስታውሰዋል? አፍሪቃዊ የወንድማማችነት ስሜቱስ እስከምን ድረስ ነው? ለምን ድን ነው ባለፈው ሰሞን፣ በታላላቅ ከተሞች መዳረሻዎች የሚኖሩ ደቡብ አፍሪቃውያን ፤ በሌሎች አፍሪቃውያን ተወላጆች ላይ የግፍ ተግባር የፈጸሙት ? የሚለው ነው። በደቡብ አፍሪቃ የጎስቋላ ሠፈሮችን ይዞታ በየጊዜው የሚያጠናው South African Cities‘ Network የተሰኘው Think Tank ቡድን አባል ዶክተር ጌሺ ካሩሪ-ሰቢና፣ እንዲህ ይላሉ።
«እንደሚመስለኝ ብዙ የተወሳሰቡ ጉዳዮችም ሆኑ ምክንያቶች አሉ። አንዱ ድንቁርና ነው ። ማንኛውም ሕብረተሰብ አልፎ-አልፎ በተወሰነ ደረጃ ድንቁርና ያጋጥመዋል። በአመዛኙ ግን የተወሰኑ የሕብረተሰብ አባላት የሀገር ሃብት ፣ የሚያጋብሱበት ሁኔታ ነው የሚታየው።እናም ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በዛ ያሉ የታላላቅ ከተሞች መዳረሻዎች ፤ ድህነት ያጠቃቸው ናቸው። ሁከት የሚፈጠረውና የኃይል ርምጃ የሚወሰደውም በአነዚሁ አካባቢዎች ነው። በተጠቀሱት የከተሞች

መዳረሻዎች፤ (ታውንሺፕስ)ደግሞ ከደeህነት ለመውጣት የሚፍጨረጨሩ የሃገሪቱ ዜጎችና ከሞላ ጎደል ድሆች የውጭ ተወላጆችም ይኖራሉ። ውድድሩ ማሕበረሰባዊ ፍትጊያን ሊያስከትል ይችላል። እርግጥ እንደተከሠተው፣ ወደ ኃይል ርምጃ መረማመድ አይገባውም ነበር።»
ባለፈው ሰሞን ፤ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ስለተፈመው፤ አረመኔአዊ የጭካኔ ተግባር ፤ አፍሪቃውያን ተወላጆች በቆንጨራ በመከትከት በአንገታቸው ላይ ጎማ አስጠልቆ በእሳት ማንጨርጨር፤ ድብደባና የመሳሰለው ስለደረሰበት ሁኔታ ፤ በዓለም ዙሪያ ብዙ ተብሏል። መሪዎቹ ፤ ፕሬዚዳንት ጆኮብ ዙማም ያሉትን መነሻ በማድረግ ዶ/ር ካሩሪ ሰቢና ተከታዩን ብለዋል።
«ፕሬዚዳንቱ ፤ ይህ የአፓርትይድ የዘረኛው ሥርዓት ውርስ ነው ይላሉ። ይህ ትክክል መሆኑን እኔ--እንጃ! ግን አንድ መከራከሪያ ነጥብ ነው። የኃይል ርምጃን የመፍትኄ ማስገኛ ይሆን ዘንድ ጥረት የሚደረግበት ሁኔታየደቡብ አፍሪቃውያን ልማዳዊ ቅርስ መስሎ ቀጥሏል። አገሪቱ ፣ በእርግጥ ከድህነት ፤ ችግርና ከአኩልነት ጥያቄ ጋር እንደተፋጠጠች ናት። እዚህ ላይ ከአፓርታይድ በኋላ፣ የፈለጉትን ለማግኘት ፤ ኑሮአቸው እንዲሻሻል የጠበቁ ፣ አንዱ ምኞታቸውና ፍላጎታቸው አልሆነላቸውም። ስለዚህ ቀላሉ ነገር በምሥኪኖች ላይ ማላከክ ነው። ያሳዝናል! የኅይል ርምጃ የሚወሰደው በመሰል -አፍሪቃውያን ወገኖች ላይ ነው። ሌሎች የውጭ ዜጎች፤ በዚያ አገር ይኖራሉ። በኤኮኖሚ ይበልጥ ተጠቃሚዎች የሆኑ! እናም፤ የ«አፍሮፎቢያ» ምልክት አለበት፤ ሆኖም በሰፊው ሊታይ የሚገባው የድህነት መንሠራፋትና ፍትኀዊ እኩልነት አለመኖር ናቸው።»

ተክሌ የኋላ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic