በዩክሬይን የሩስያና የምዕራቡ ዓለም ፍጥጫ | ዓለም | DW | 14.04.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

በዩክሬይን የሩስያና የምዕራቡ ዓለም ፍጥጫ

ዩክሬይን፤ ዛሬም የዓለም ልዕለኃያላኑን እንዳፋጠጠች ነው። በክሬሚያ የነገሰው ውጥረት ልሣነ-ምድሪቱን በሕዝበ-ውሳኔ ለሩስያ ግብር ዳርጎ ወደ ምሥራቃዊ የሀገሪቱ ክፍል ተዛምቷል። መፍቀሬ-ሩስያውያን በምሥራቅ ዩክሬይን በርካታ የመንግሥት ተቋማትን እንደተቆጣጠሩ ነው።

ሩስያ እዛው ምሥራቅ ዩክሬይን ውስጥ የሚኖሩ የሩሲያ ቋንቋ ተናጋሪዎችን ለመጠበቅ በሚል የጦር ክምችቷን ከምን ጊዜውም በላይ አግዝፋለች።በምድርም በዓየርም እጅግ ዘመናዊው የሩስያ ጦር በአካባቢው እስከ 40 ሺህ ደርሶ ይርመሰመስ ጀምሯል። በዋናነት በጀርመን የሚዘወረው የአውሮጳ ኅብረትም ሆነ ዩናይትድ ስቴትስ የሚያደርጉት መላው ጠፍቷቸዋል። መከረኛ ጋዝና ነዳጅ በዩክሬይን ዕጣ-ፈንታ ይጫወት ይዟል።

ዩክሬናውያን በወኔ ተሞልተው የነፃነት ዓርማቸው አድርገው ወደ ሚመለከቱት የሜይደን አደባባይ እንዲያ ሠርክ ሲተሙ የጠበቁት ሌላ ነበር። ያልጠበቁት ዱብዕዳ ወረደባቸው እንጂ። ወርሃ ኅዳር አጋማሽ ላይ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ቪክቶር ያኒኮቪች የአውሮጳ ኅብረት የትብብር ውልን አልፈርምም ማለታቸው ነበር የተቃውሞው መነሻ።

ወደ የእርስ በእርስ ግጭት የተቀየረው የተቃውሞ ሠልፍ በዩክሬይን ከወራት በፊት

ወደ የእርስ በእርስ ግጭት የተቀየረው የተቃውሞ ሠልፍ በዩክሬይን ከወራት በፊት

በእዚሁ ታሪከኛ የነፃነት አደባባይ፤ ከዘጠኝ ዓመታትም በፊት፤ በወርሃ ኅዳር ለብርቱካናማው አብዮት ድጋፋቸውን ለመስጠት ከሁለት መቶ ሺህ በላይ ዩክሬናውያን ተመው ዓለምን አስደምመው ነበር። የዩክሬይኑ የነፃነት አደባባይ ዲሞክራሲ መንገዳገድ ሲጀምር ዩክሬኖችን ለተቃውሞ የመሳብ አንዳች ኃይል አለው። አሁን ደመኛቸው አድርገው ከሀገር ሊያባርሩዋቸ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ቪክቶር ያኑኮቪችን በድምፃቸው መርጠው ከሥልጣን መንበሩ ላይ አደላድለዋቸውም ነበር፤ ዩክሬናውያን።

ዩክሬናውያን ተቃውሞዋቸውን በቪክቶር ያኒኮቪች መንግሥት ላይ ማፋፋም ሲጀምሩ ከሩስያ ይልቅ ከአውሮጳ ጋር የሚያቆራኛቸው የትብብር ውል በተፅዕኖ ይፈረማል የሚል ተስፋ ሰንቀው ነበር። የዛሬ አምስት ወር ግድም መሆኑ ነው። ዩክሬናውያኑም ሆኑ የምዕራቡ ዓለም፤ በተለይ ደግሞ የአውሮጳውያኑ ፍላጎት የዩክሬን መንግሥት የትብብር ሠነዱን ፈርሞ ፊቱን ወደ አውሮጳ እንዲያዞር ነበር።

ሩስያ በከርሠ-ምድር ሀብት እጅግ የበለፀገችው ዩክሬይን ውስጥ የሚካሄደውን እንቅስቃሴ ሌትም ሆነ ቀን በማይከደኑት አይኖቿ ነው የምትከታተለው። ሩስያ በዩክሬን ላይ የምታሳድረውን ምጣኔ-ሀብታዊ ተጽዕኖ በቀላሉ ማጣት አትፈልግም። እናም ተፅዕኖዋን አስጠብቃ ለመቆየት የተለያዩ አማራጮችን ስትጠቀም ሰንብታለች።

ኢንዱስትሪ ምሥራቅ ዩክሬይን ውስጥ በከፊል

ኢንዱስትሪ ምሥራቅ ዩክሬይን ውስጥ በከፊል

ሩስያ የክሬሚያ ልሣነ-ምድርን በጠቀለለች ማግስት ዩክሬይንን በተለያየ መንገድ መቅጣት ተያይዛለች። ከሰሞኑ እንኳን ፕሬዚዳንቷ ቭላድሚር ፑቲን የዩክሬይን የጋዝ አቅርቦትን እንደሚያቋርጡ ዝተዋል። ዩናይትድ ስቴትስ ግን ዛቻውን በፅኑዕ ተቃውማለች። የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ቃል አቀባዪት ጄን ፕሳኪ የሩስያን ውሳኔ አውግዘዋል።

«ሩሲያ የኃይል አቅርቦትን ዩክሬን ላይ ጫና ለማሳደር በመሳሪያነት መጠቀሟን እናወግዛለን። ጋዙን የሚሸጡት ከገበያዉ ዋጋ በላይ መሆኑን መግለፁ ተገቢ ይመስለናል። እናም በእርግጥም ከአካባቢዉ አጋሮቻችን ጋ በመሆን ዩክሬንን በዚህ ወቅት ለመርዳት ርምጃዎችን ለመዉሰድ እየሠራን ነዉ።»

ዩክሬይን ምንም እንኳን እምቅ የጋዝ እና የነዳጅ ሀብትን ጨምሮ የተለያዩ የከርሠ-ምድር ክምችት የታደለች ብትሆንም የኃይል አቅርቦቷ ሙሉ ለሙሉ ከሩስያ በሚላክ ጋዝ ጥገኛ ነው። ሩስያ የጋዝ አቅርቦቱን የማቋርጠው ዩክሬይን ያልተከፈለ 2,2ቢሊዮን ዶላር ገደማ ብድር ስላለባት ነው ብላለች። ላለፉት አራት ዓመታት ወደ 35 ቢሊዮን ዶላር የምጣኔ ሀብት ድጎማ ሳደርግላት መቆየቴ ሳያንስ ብድሯን ሳትከፍል ከእንግዲህ የጋዝ አቅርቦት ማግኘት አትችልም ብላለች። ድርጊቱ አውሮጳውያንንም ሊጎዳ እንደሚችል ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በጋዝ አቅርቦቱ በአብዛኛው ጥገኛ ለሆኑ 18 የአውሮጳ ሃገራት በፃፉት የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ገልጸዋል። ሩስያ ለአውሮጳውያን የምትልከው ጋዝ የሚያልፈው የዩክሬይንን ድንበር አቋርጦ በተዘረጋው የጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧ ነው።

በዩክሬይን ምድር አሳብሮ ወደ አውሮጳ የሚያቀናው የሩስያ የጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧ በከፊል

በዩክሬይን ምድር አሳብሮ ወደ አውሮጳ የሚያቀናው የሩስያ የጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧ በከፊል

አውሮጳ ከዩክሬይን ጋር የትብብር ሠነድ ከተፈራረመች ግን በአብዛኛው በሩስያ ጥገኛ የሆነው የኃይል አቅርቦቷን በዩክሬይን በኩል ለማግኘት ያስችላታል። የትብብር ሠነዱ አውሮጳ ከኃይል አቅርቦት ማሻሻያ አንስቶ የተለያዩ የመሰረተ-አውታሮችን ያለችግር ዩክሬይን ውስጥ እንድታከናውን መንገድ የሚያመቻች ነው። በእዚያ ላይ 46 ሚሊዮን የሚጠጋው የዩክሬይን ነዋሪም እራሱን የቻለ የገበያ ምንጭ ነው።

አውሮጳ ዩክሬይንን ከሩስያ ተፅዕኖ ማላቀቅ ከቻለ ኅብረቱ በምሥራቅ በኩል ለሚያደርገው መስፋፋት ታላቅ ስኬት ተደርጎ ይወሰዳል። ይሄን በቅጡ ያጤነች የምትመስለው ሩስያ የጦር ኃይሏን በዩክሬይን ድንበር አቅራቢያ እያበራከተች የምጣኔ ሀብትን የጨዋታው አካል አድርጋለች። ሁኔታው ያሳሰባቸው አውሮጳውያን ሩስያ ላይ የተለያዩ የተለሳለሱ ርምጃዎችን እየወሰዱ ነው። አክሴል ፊሸር፤ በአውሮጳ ምክር ቤት የጀርመን ልዑክ፦

«ዛሬ የሩስያ ልዑካን በሌሉበት ዘለግ ያለ ውይይት ከአካሄድን በኋላ፤ የሩስያ ልዑካን በእዚህ ዓመት ድምፅ የመስጠት መብታቸው እንደተነሳ እና ከጥር ወርበኋላ ጉዳዩን አንስተን እንደ አዲስ የምንወያይበት መሆኑን ወስነናል።»

ሩስያ ልዑካኗን በአውሮጳ ኅብረት ምክር ቤት እየሰየመች በኅብረቱ ውይይት ላይ ስትሳተፍ መቆየቷ ይታወቃል። በእዚህ ተሳትፎ ሩስያውያኑ ድምፅ የመስጠት መብታቸውን ነው የተነጠቁት። ቀደም ሲል የሰሜንአትላንቲክጦርቃልኪዳን ድርጅት(ኔቶ)በበኩሉ አማራጮችን አቅርቧል። ዋና ፀሐፊው አንድረስ ራስሙስን ፎግሕ የዩክሬይንን ዉዝግብ ለማስወገድ ጦር ከማዝመት ይልቅ የሚመለከታቸዉ ወገኖች እንዲደራደሩ ጠይቀዋል። የሩስያ የውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ሠርጌይ ላቭሮቭም ድርድሩን እንደሚፈልጉ ሆኖም ግን የመንግሥቴ አቋም የሚሉትን ሀሳብ አሰምተዋል።

ሠርጌይ ላቭሮቭ በሩስያ ዱማ ተገኝተው ለምክር ቤት አባላት ንግግር ሲያደርጉ።

ሠርጌይ ላቭሮቭ በሩስያ ዱማ ተገኝተው ለምክር ቤት አባላት ንግግር ሲያደርጉ።

«በእርግጥም የዩክሬይን ቀውስን ማርገብ እንደሚቻል እናምናለን። ያን ለማሳካት ታዲያ ማዕቀብ የመጣል ርምጃን መግታት አለብን። ያለአንዳች ቅድመ-ሁናቴም በመላ ዩክሬይን ከሚገኙ የፖለቲካ ኃይላት ጋር ውይይት ሳይካሄድ በማንኛውም መንገድ የሜይዳን አደባባይ መንግሥትን ዕውቅና ለመስጠት ከመሞከር መቆጠብ አለብን። እናም ወሳኙ ጥያቄ ያለአንዳች ማግለል፣ የሁሉንም ዩክሬናውያን ሕጋዊ መብት እና ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ፤ ምንም ያልተቀባባ፣ እውነተኛ የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ ማድረግ ነው። በሕገ-መንግሥቱ በተደነገገው መሰረት የዩክሬይን ገለልተኝነት እንደተጠበቀ ለመፅናቱ ጥብቅ ማረጋገጫ እንደሚያስፈልግ ለማንም ግልፅ ነው።»

ሠርጌይ ላቭሮቭ «የዩክሬይን ገለተኝነት» የምትለውን ቃል አፅንዖት የሰጡባት ዩክሬይን ከአውሮጳ ኅብረት ጋር የተፈራረመችውን ከፊል የትብብር ሠነድ አስመልክተው ከወዲሁ ለማስጠንቀቅ ነው። በአውሮጳ ኅብረት በሚደገፈው የዩክሬይን የተቃዋሚ ኃይል ከስልጣናቸው የተነሱት የቀድሞው የዩክሬይን ፕሬዚዳንት ቪክቶር ያኑኮቪች ከዩክሬይን ተባረው ሩስያ ጥገኝነት ከመጠየቃቸው ከሁለት ዓመታት በፊት ለሩስያ የሚመች ውል ፈርመው ነበር። ያኒኮቪች የፈረሙት ሠነድ በምንም መልኩ ዩክሬይን ከሌሎች አካላት ጋር የጦር ውል እንዳታደርግ የሚል ነው። ይህቺን የመጫወቻ ካርድ ሩስያኖች አሁን ሊስቧት መፈለግ ብቻ አይደለም ጠበቅ አድርገውም ይዘዋል። ሩስያ ዩክሬይንን ጨምሮ የሶቪየት ኅብረት የቀድሞ አባል ሃገራት የኔቶም ሆነ የሌላ የጦር ኃይላት ስብስብ አባል እንዲሁኑ ፈጽሞ አለመፈለጓን አስረግጣ ተናግራለች።

ቪክቶር ያኑኮቪች በጠቅላይ ሚንሥትርነት ዘመናቸው በርሊን ከተማ ውስጥ ከአንጌላ ሜርክል ጋር

ቪክቶር ያኑኮቪች በጠቅላይ ሚንሥትርነት ዘመናቸው በርሊን ከተማ ውስጥ ከአንጌላ ሜርክል ጋር

አውሮጳውያን ዩክሬይንን በእጃቸው የማድረግ ህልማቸው ዕውን ይሆን ዘንድ ከዩክሬይን መዲና ኪዬቭ ጀርመን በርሊን ከተማ ድረስ የሚመላለስ አንድ ታዋቂ ሰውም አሰናድተው ነበር። የዓለማችን የከባድ ሚዛን ቡጢ ባለድሉን ቪታሊ ክሊችኮ። ቡጢኛው ኪዬቭ ላይ በዩክሬን አንደበት፤ ሁለተኛ ሀገሩ የሆነችው ጀርመን ሲደርስ ደግሞ በጀርመንኛ ቋንቋ ለተቃውሞው አመራር ሲሰጥ አይሰለቸውም ነበር። በሺህዎች የሚቆጠሩ ዩክሬናውያን የተቃውሞ ጥሪውን ተከትለው ዕለት በዕለት የሜይደን አደባባይ በማጨናነቅ ፕሬዚዳንቱን ከሀገር ማስኮብለል ተሳክቶላቸዋል። የክሬሚያ ልሣነ-ምድር ግዛታቸውን ግን ለሩስያ አስረክበዋል። አሁን የጀርመን መራሂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ይበልጥ ድርድር ማካሄዱ ላይ ያተኮሩ ይመስላል።

«ዩክሬን የምትካፈልበት ዓለም አቀፍ ድርድር መጀመር አጣዳፊ ነዉ። ድርድሩ የአዉሮጳ ኅብረት፤ዩናይትድ ስቴትስ፤ሩሲያና ዩክሬን የሚሳተፉበት መሆን አለበት። የዩክሬን ሕገ-መንግሥትን የማርቀቁ ሂደትን ማፋጣን አስፈላጊ ነዉ። እዚያ የሚደረገዉን ምርጫ አሳማኝ በሆነ-መንገድ ማዘጋጀት አስፈላጊ ነዉ። ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ በቀየሰዉ መርሐ-ግብር መሠረት ለዩክሬን ሊሰጥ ቃል የገባዉን ገንዘብ ባስቸኳይ መስጠቱም ከሁሉም በላይ በጣም አስፈላጊ ነዉ።»

ጆን ኬሪ ዩክሬይን ውስጥ የተገደሉ ሠልፈኞችን አስመልክተው የአበባ ጉንጉን ሲያኖሩ

ጆን ኬሪ ዩክሬይን ውስጥ የተገደሉ ሠልፈኞችን አስመልክተው የአበባ ጉንጉን ሲያኖሩ

ዩክሬይንን ጉዳይ ለአውሮጳ ኅብረት አንዳች ሙዳ ከአንበሣ መንጋጋ ለመፈልቀቅ የመሞከር አይነት ይመስላል። የአውሮጳ ኅብረትም ሆነ ዩናይትድ ስቴትስ ሩስያ የዩክሬይን ግዛት የነበረችው ክሬሚያን በመጠቅለሏ፣ ብሎም ወደ ምሥራቅ ጦሯን በማስፈሯ እስካሁን ድረስ የተለያዩ ማዕቀቦችን አሳርፈዋል።

መቼም ዩናይትድ ስቴትስ አይኗን በጨው አጥባ በዩክሬይን ጉዳይ ከሩስያ ጋር እስከ መጨረሻው የመፋጠጥ የሞራል ብቃት የሚኖራት ግን አይመስልም፤ ድፍረቱ እና አቅሙ ግን አላት። ያንን በእርግጥም እየተገበረችው ነው። ሩስያ በበኩሏ ግልፅ በሆነ ቋንቋ ማንም ጣልቃ እንዳይገባብኝ እያለች ነው።

ዩናይትድ ስቴትስ ከኢራቅ እስከ አፍጋኒስታን እንዳሻት ያለከልካይ ስትመላለስ ሩስያ ጣልቃ ባለመግባቷ አሜሪካ በሂደት ጥጓን መያዟ አይቀርም ብለው ሳይገምቱ አልቀርም የሩስያ ባለሥልጣናት። ያን የሚያንፀባርቅ ይመስላል የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከሰሞኑ የተናገሩት።

ምዕራባውያኑ ለአብነት ያህል ዩጎዝላቪያን እና ሊቢያን በቦንብ ሲቀጠቅጡ ከተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ይሁንታ ውጪ ነው ሲሉ ተችተዋል ፑቲን። እኛንም በተራችን ተዉን ይመስላል አነጋገራቸው። እናስ ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ የምዕራቡ ዓለም በተራው ሩስያኖቹን ይተዋቸው ይሆን?

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic