1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስኢትዮጵያ

በየ ድረ-ገጹ ብቅ የሚሉት ኩኪስ አገልግሎታቸው ምንድነው?

ረቡዕ፣ መስከረም 16 2016

ድረ-ገጾችን በጎበኘን ቁጥር ብቅ እያሉ ኩኪዎችን ለመጠቀም ይስማማሉ? የሚል ጥያቄ ማየት በዕለት ተዕለት የበይነ-መረብ አጠቃቀማችን ተደጋግሞ የሚያጋጥመን ጉዳይ ነው።አሁን አሁን ኩኪዎችን/ ለመጠቀም ካልፈቀድን በቀር የምንፈልገውን ድረ-ገፅ መጎብኘት፣ አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል።ለመሆኑ ኩኪዎች ምንድናቸው?ጥቅምና ጉዳታቸውስ?

https://p.dw.com/p/4WshY
በኩኪዎች ላይ ቅሬታ ማሰማት  ተጀምሯል
የአውሮፓ የመረጃ ጥበቃ ድርጅት በትላልቅ ድረ-ገጾች ላይ ባሉ የኩኪ ባነሮች ላይ ቅሬታዎችን እያነሳ ነው።ምስል Lino Mirgeler/dpa/picture alliance

አንዳንዶቹ ኩኪዎች ለመረጃ ስርቆት ያጋልጣሉ

ድረ-ገጾችን  በጎበኘን  ቁጥር  ብቅ እያሉ ኩኪዎችን ለመጠቀም ይስማማሉ? የሚል ጥያቄ  ማየት በዕለት ተዕለት የበይነ-መረብ አጠቃቀማችን ተደጋግሞ የሚያጋጥመን  ጉዳይ ነው።አሁን አሁን   ኩኪዎችን/cookies/ ለመጠቀም ካልፈቀድን በቀር የምንፈልገውን ድረ-ገፅ መጎብኘት፣ መረጃ ማግኘት እና  ግብይት መፈፀምን  የመሳሰሉ  የበይነመረብ ተግባራትን መከወን አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል።ለመሆኑ እነዚህ  ኩኪዎች ምንድን ናቸው? በሳይበር ደህንነት ሙያ የበርካታ አመታት ልምድ ያካበቱት አቶ ብሩክ ወርቁ  ትንንሽ የፅሁፍ መዝገቦች ይሏቸዋል።
የተጠቃሚዎች ኮምፒዩተር  እና ተንቀሳቃሽ ስልኮች ላይ ኩኪዎችችን የሚያስቀምጧቸው ድረ-ገፆች ናቸው።የሚሉት ባለሙያው፤ መረጃ ለማግኘት በምንጎበኛቸው ድረ ገጾች እና ድረ-ገፆችን ለመፈለግ በምንጠቀምባቸው  እንደ ጉግል ክሮም፣ ፋየር ፎክስ እና ኢንተርኔት ኤክስፕሎረር ባሉ  አሳሾች መካከል ያለው ግንኙነት  ኤች ቲ ፒፒ/HTTP/ በሚባለው ፕሮቶኮል /Hypertext Transfer Protocol/ የተዳኘ ነው።ነገር ግን ይህ የመግባቢያ ፕሮቶኮል የተጠቃሚዎችን መረጃ ይዞ የማያስቀር እና የማያስታውስ በመሆኑ ተጠቃሚው ወደ ተለያዩ ድረገጾች ድጋሜ ለመግባት በየ ጊዜው እንደ አዲስ የ«ሎግ ኢን» መረጃ እንዲሰጥ ይገደዳል።እንደ አቶ ብሩክ የኩኪ ቴክኖሎጅ  የተፈጠረውም  ይህንን መሰሉን ችግር ለማስቀረት ነው።

አቶ ብሩክ ወርቁ ለበርካታ ዓመታት በሙያው የሰሩ የሳይበር ደህንነት ባለሙያ
አቶ ብሩክ ወርቁ ለበርካታ ዓመታት በሙያው የሰሩ የሳይበር ደህንነት ባለሙያምስል Privat

በዚህ ሁኔታ ኩኪዎች፤  ድህረ ገጾች  ተጠቃሚዎቻቸውን ለይተው እንዲያውቁ እና የግል የመግቢያ መረጃዎቻቸውን እና ምርጫዎቻቸውን እንዲያስታውሱ ያስችሏቸዋል። ለምሳሌ ድረ-ገጾች ላይ የስፖርት ዜና ማንበብ ለሚያዘወትር ተጠቃሚ ከሌሎች  ዜናዎች በበለጠ የስፖርት ዜናዎችን በርከት አድረገው ይልኩለታል።ከዚህ በተጨማሪ ተጠቃሚዎች ከዚህ ቀደም ለመግዛት የተመለከቷቸውን ዕቃዎች መሰረት በማድረግ የግዥ ፍላጎትን ለመከታተልም ድረ ገጾች ኩኪዎችን ይጠቀማሉ። ለምሳሌ ጫማ ፣ ልብስ ወይም ሌሎች ቁሳቁሶችን በበይነመረብ ለመግዛት አሰሳ ከተደረገ፤  ይህንን ፍላጎት  ይበልጥ ግላዊ በማድረግ  ተመሳሳይ ማስታወቂያዎችን ለተጠቃሚው ያዥጎደጉዳሉ።ይህም ተጠቃሚዎች ሊወዷቸው የሚችሏቸውን እቃዎች ለመጠቆም እና ለመግዛት የፈለጓቸውን እቃዎች የመግዣ ሳጥኖች  ውስጥ እንዲያቆዩ ያስችላል።እየጨመረ የመጣው የሳይበር ጥቃት በኢትዮጵያ
ከዚህ በተጨማሪ አንድን ገጽ ስንት ጊዜ እንደጎበኙ ወይም በአንድ ገጽ ላይ ምን ያህል ጊዜ እንዳጠፉ፣  በድረ-ገጹ ላይ ምን እንደሠሩ፣ የት ሆነው ድረ-ገጹን እንደጎበኙ፣ ድረ- ገጹን ለመጎብኘት ምን ዓይነት የኤለክትሮኒክ መሳሪያ  እንደተጠቀሙ እና ሌሎች መሰል የበይነመረብ እንቅስቃሴዎች ላይ  መረጃዎችን ይሰበስባሉ።ይህ ደግሞ የግል መረጃ ጥበቃ ህግን የሚተላለፍ በመሆኑ ኩኪዎች ስምምነታችንን ይጠይቃሉ።ለመሆኑ በኩኪዎች ተስማማን ማለት ምን ማለት ነው?።አቶ ብሩክ ወርቁ እንደሚሉት በኩኪዎች መስማማት የተከማቸውን የግል መረጃ ውሰድ ብሎ እንደመስማማት ነው።
የተጠቃሚን የአሰሳ ታሪክ  ወይም የግዢ ፍላጎት  እና ሌሎች የበይነመረብ እንቅስቃሴዎች ላይ መረጃ በመሰብሰብ የጎበኘናቸው ድረ-ገጾች  እንዲያስታውሱን የሚያደርጉት ኩኪዎች፤ በዘመናዊው የበይነመረብ አጠቃቀም  የመረጃ መረብን  ለማሰስ አስፈላጊ መሳሪያ ተደርገው ይወሰዳሉ። የድረ ገፅ ባለቤቶችም  በኩኪዎች አማካኝነት ከተጠቃሚዎች የተሰበሰበውን መረጃ መሰረት በማድረግ  ተጠቃሚዎች የሚፈልጉትን ይዘት መርጦ ለማቅረብ እና የድረገፅ ጉብኝትን የበለጠ ግላዊ እና ምቹ  ለማድረግ ይጠቀሙበታል።ነገር ግን የግል መረጃ ውድ ሀብት በመሆኑ  ተጠቃሚው  ለመረጃ ምዝበራ ተጋላጭ እንዲሆን ሊያደርጉም ይችላሉ።ከዚህ አኳያ የግል መረጃ ባልተገባ ሁኔታ መሰብሰቡ፣ መከማቸቱ እና ጥቅም ላይ መዋሉ  የቴክኖሎጂ ባለሙያዎችን እና የተለያዩ አገራት ሕግ አውጪዎችን እያሳሰበ ነው። 

አንዳንዶቹ ኩኪዎች ለሳይበር ወምጀል ያጋልጣሉ
የመረጃ መንታፊዎች ከሚጠቀሙበት ዘዴ አንዱ በኩኪስ የሚሰበሰበውን መረጃ መሰረት በማድረግ ነውምስል Dominic Lipinski/PA/dpa/picture alliance

ከዚህ አኳያ አቶ ብሩክ  ኩኪዎችን መጠቀም ጥቅምም ጉዳትም አለው ይላሉ።ከጥቅም አንፃር ስንመለከት ኩኪሶችን መጠቀም የድረ ገጽ ባለቤቶች ተጠቃሚዎች ምን ዓይነት መረጃ እንደሚፈልጉ በመገንዘብ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ ያግዛል። ኩኪዎች ድረ ገጾች እንዲያስታውሱን በማድረግም የበይነ መረብ ግብይትን ለማሳለጥ እንዲሁም በተጠቃሚዎች ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ማስታወቂያ ለማቅረብ ይጠቅማሉ።የበዓላት ወቅት የሳይበር ጥቃቶች እና ጥንቃቄዎቻቸው
የተጠቃሚውን ኮምፒዩተር ፍጥነት እንዲቀንስ ማድረግ እንዲሁም የመረጃ ደህንነትን አደጋ ላይ መጣል ም ዋነኛው ጉዳት ነው።የበይነመረብ ኩኪዎች በተለያዩ  ምድቦች የሚከፈሉ ሲሆን፤ አንዳንዶቹ ኩኪዎች ከሌሎቹ የበለጠ አስጊ ሊሆኑ ይችላሉ።
የመጀመሪያ ወገን ኩኪዎች /First party cookies/ ከኩኪስ አይነቶች  አንዱ ሲሆን፤ ተጠቃሚ ከሚጎበኛቸው ድረ-ገፅ ባለቤቶች  በቀጥታ የሚመጡ ናቸው። ታዋቂ ድረ-ገጾችን ወይም በመረጃ ዝርፊያ እና  በሳይበር ጥቃት ስማቸው የማይነሳ ድረ-ገጾችን እስካሰሱ ድረስ ደህንነታቸው የተጠበቀ ነው።
ሁለተኛው የኩኪስ አይነት የሶስተኛ ወገን ኩኪዎች/ Third party cookies/  የሚባሉ ሲሆን የበለጠ አሳሳቢ ናቸው።ምክንያቱም  እነሱ የሚመጡት ተጠቃሚዎች ከሚጎበኙት ገፅ ሳይሆን ከሌላ ድህረ ገፆች  በአብዛኛው በዚያ ገጽ ላይ ከሚታዩ ማስታወቂያዎች ጋር የተገናኙ ናቸው።

ኩኪዎች ለመረጃ መንታፊዎች ሊያጋልጡን ይችላሉ
የሳይበር ወንጀለኞች በተለይ ዙምቢ ኩኪዎችን ሆን ብለው ሊጠቀሙባቸው ይችላሉ።ምስል allOver-MEV/IMAGO

ሌላው እና ሶስተኛው የኩኪስ አይነት ዞምቢ ኩኪዎች/Zombie Cookies/ የሚባሉት ናቸው። እነዚህ በቋሚነት በተጠቃሚዎች ኮምፒውተሮች ላይ የሚጫኑ የሶስተኛ ወገን ቋሚ የኩኪ አይነት ናቸው።እነዚህ ኩኪዎች ብዙም የተለመዱ ባይሆንም፤ ከኮምፒዩተር ላይ ከተሰረዙ በኋላ እንኳ እንደገና መታየት የሚችሉ በመሆናቸው፤ ለማስወገድ እጅግ በጣም አስቸጋሪዎች  ናቸው። ዞምቢ ኩኪዎች ልክ እንደሌሎች የሶስተኛ ወገን ኩኪዎች፣  ልዩ የግለሰቦችን የአሰሳ ታሪክ ለመከታተል ኩባንያዎች ሊጠቀበት ይችላሉ። ድረ-ገጾች የተወሰኑ ተጠቃሚዎችን ለማገድ ዞምቢዎችን ሊጠቀሙ ይችላሉ። በአንዳንድ አጋጣሚዎች ግን እነዚህ አይነት ኩኪዎች በጠላፊዎች ሊፈጠሩ እና የተጠቃሚዎችን ኮምፒዩተር  በቫይረስ ለመበከል ሁሉ ይችላሉ።
ከዚህ አንፃር ተጠቃሚዎች ተገቢ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ ባለሙያው ይመክራሉ።የመጀመሪያው ጥንቃቄ በስልካችን «ሴቲንግ» ውስጥ «ፕራይቬሲ»ወደሚለው ክፍል በመግባት ፈቃድ መከልከል የሚቻል ሲሆን፣ኩኪዎችን ከምንጠቀምበት ኮምፒዩተር ላይ ማጥፋት ደግሞ  ሁለተኛው መፍትሄ ነው።  ከመስማማታችን በፊት አማራጮችን በደንብ ማንበብ ደግሞ የተሻለው መፍትሄ ነው። 

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።


ፀሀይ ጫኔ
ዮሀንስ ገብረእግዚአብሄር