በየአመቱ እንደሚሆነዉ ሁሉ ከሲዊትዘርላንዷ ዉብ መናፈሻ | ኤኮኖሚ | DW | 26.01.2004
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

በየአመቱ እንደሚሆነዉ ሁሉ ከሲዊትዘርላንዷ ዉብ መናፈሻ

ከተማ ዳቮስ የተሰየመዉ ጉባኤ ያላቸዉ እንዳላቸዉ የሚቀጥሉበትን ብልሐት ከማጠናከር የተለየ-የአለም ንግድ ይሁን የምጣኔ ሐብት ክፍፍል የአብዛኛዉን የአለም ሕዝብ ኑሮ የሚያሻሻሉበትን ዘዴ ይቀይሳል ብሎ የሚገምት የለም።ሁለት ሺሕ ከሚሆኑት የዘንድሮ ጉባኤተኞች ከስልሳ ከመቶ የሚበልጡት ግን የተዛባዉ የንግድ ሥርዓት በተለይ አብዛኞቹ አዳጊ ሐገሮች የሚያመርቱት የግብርና ዉጤት ገበያ እንዲሻሻል መፈለጋቸዉ-ነዉ እንቆቅልሹ።Price Waterhose Coopers የተባለዉ አጥኝ ድርጅት ባሰባሰበዉ አስተያየት መሠረት ትላልቅ የንግድ ኩባንያ ተጠሪዎች፣ የገንዘብ ተቋማት ሐላፊዎችና የመንግስታት መሪዎች ወይም ተወካዮች የተካፈሉበት ጉባኤ ዘንድሮም እንደከዚሕ በፊቱ የግብርና ዉጤቶች ገበያን ለማሻሻል መተጋጀቱን የሚጠቁም ምልክት የለም።ከሁለት ሺሕ ጉበኤተኞች አንድ ሺሕ ሁለት መቶዎቹ የተስማሙበት ጉዳይ የተቀሩት ስምንት መቶዎቹ ባለመስማማታቸዉ ብቻ ገቢር አይሆንም መባሉ ግን የድሆች መብት ተቆርቋሪዎች እንደሚሉት አለም ብዙዎች ይኑሩባት እንጂ በጥቂቶች ፍላጎት መመራትዋን መስካሪ ነዉ።

እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር ሕዳር 2001 ዶሐ-ቀጠር ዉስጥ ተሰይሞ የነበረዉ የአለም ንግድ ድርጅት አባል ሐገራት የሚንስትሮች ሥብሰባ የአለም ንግድን ሥርአት የሚያሻሽል ዉሳኔ አሳልፎ ነበር።ባለፈዉ መስከረም ካንኩን-ሜክሲኮ ዉስጥ የተደረገዉ ተመሳሳይ ስብሰባ የዶሐዉን ስምምነት ገቢር ለማድረግ ቀርቶ-ተባለጡን የእርሻ ንግድ ለማሻሻል የሚተክር እርምጃ እንኳን ሳይወስድ-ነዉ የተበተነዉ።የካንቱኑ ስብሰባ ከስብሰባዉ በፊት እንደተፈራዉ ያለሥምምነት የተበተነዉ ሐብታሞቹ ሐገራት ለድሆቹ የእርሻ ዉጤቶች ገበያቸዉን እንዲከፍቱ በሌላ አባባል ሐብታሞቹ ሐገራት ለየእርሻ ምርታቸዉ የሚሰጡትን አለቅጥ የበዛ ድጎማ እንዲቀንሱ ድሆቹ ያቀረቡትን ሐሳብ አንቀበልም በማለታቸዉ ነበር።ያዉ የእርሻ ገበያ ጥያቄ አሁን ዳቮስ ላይ የተሰየመዉ የአለም ምጣኔ-ሐብት ጉባኤ አብይ ጉዳይ መሆኑ አጥኚዎች እንደመሰከሩት ሰወስተኛ አመቱን የያዘዉ የዶሐዉ ዉል ገቢር የሚሆንበት ሳይሆን የሚፈርስበት መንገድ መጠረጉን ጠቋሚ ነዉ።

ከእርሻ ዉጤት ገበያ ሌላ የዶላር መዉደቅ፣ ወይም የዩሮና የጃፓኑ ገንዘብ የን መጠንከር በአለም ንግድ ላይ ያሰደረዉና የሚያሳድረዉ ተፅዕኖ የዳቮስ ጉባኤተኞችን የሚያሳስብ ጉዳይ ሆኗል።የአለም ምጣኔ ሐብት የሚያንሰራራበት መንገድም ጉባኤተኞቹ እንደሰወስተኛ ጉዳይ አንስተዉታል።የእርሻ ምርት ገበያ ተባለጥ የፈጠረዉን ሥጋት ያሕል አብዛኛዉን ጉባኤተኛ ያስማማ ግን የለም።የዳቩሱ ጉባኤ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት ሰላሳ ሁለት አመታት እንደሚደረገዉ ሁሉ ዘንድሮም የንግድ ድርጅቶች፣ የገንዘብ ተቋማት፣ የመንግሥታት ተጠሪዎች ከጋራዉ ጉባኤ ጎን የየራሳቸዉን ዉይይትና ምክክር አድርገዋል።በየስፍራዉ በነበረዉ ዉይይት የእርሻ ዉጤት ንግድና ችግሩን ያሕል የተንፀባረ ግን የለም።አጥኚዉ ድርጅት እንዳስታወቀዉ የእርሻ ዉጤት ንግድን የተዛባ ሥርአት ለማስተካከል በዉጤቱም የዶሐዉን ዉል ከሞት ለማዳን ዋንኞቹ እንቅፋቶች ዩናይትድ ስቴትስና የአዉሮጳ ሕብረት ናቸዉ።የቀድሞዉ የሜክሲኮ ፕሬዝዳንት አርኔስቶ ዜዲሎ እንዳሉት ባለፈዉ መስከረም ሐገራቸዉ ያስተናገደችዉ የአለም ንግድ ድርጅት የሚንስትሮች ሥብሰባ ያለዉጤት የተበተነዉ ዩናይትድ ስቴትስና የአዉሮጳ ሕብረት ለስብሰባዉ ያቀረቡት የእርሻ ምርት ንግድ እቅድ ፍትሐዊ ሥላልነበር ነዉ።እነዚሕ ሐብታም ሐገራት አሁንም በያዙት አቋም የሚቀጥሉ መምሰላቸዉ ዜድሎ እንደሚያምኑት የዶሐዉን ስምምነት ጨርሶ ይገድለዋል።

ሐብታሞቹ ሐገራት ለግብርናና ከግብርና ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች በየአመቱ ሰወስት መቶ ሃያ ቢሊዮን ዶላር ይደጉማሉ።ድሖቹ ሐገራት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶ፣ የተፈጥሮ ጥበቃ ተማጋቾች ይሕ ድጎማ ቀንሶ የሐብታሞቹ ሐገራት የእርሻ ምርት ከዶሆቹ ሐገራት የእርሻ ምርት እኩል በአለም ገበያ ተወዳድሮ መሸጥ መለወጥ አለበት፣ አለያም ሐብታሞቹ ሐገራት በድሆቹ ምርት ላይ የጣሉት ቀረጥ መቀነስ አለባቸዉ ባዮች ናቸዉ።የጀርመኑ የኢኮኖሚ ሚንስትር ቮልፍ ጋንግ ክሌመንት አዉሮጶች ሥለ እርሻ ምርት ገበያ መፍትሔ መፈለግ አለባቸዉ ይላሉ።-መፍትሔዉ ግን የፖለቲኮች ዉሳኔ ነዉ።የዩናይትድ ስቴትሱ የአለም ንግድ ምክትል ሚንስትር ግራንድ አልዶናስም ሐገራቸዉ የእርሻ ምርት ገበያን ለማሻሻል ማሰቧን አስታዉቀዋል።የጀርመንና የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት ዳቮስ ያሉት የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች እንደሚያምኑት ጥሩ ነዉ።ግን የአዉሮጳ ሕብረትና ዩናይትድ ስቴትስ እንደ ተቋም ወይም ሐገር ባለሥልጣኖቻቸዉ ያሉትን ለማድረግ አለመዘጋጀታቸዉ ነዉ-አሳሳቢዉ።