በየመን የቀጠለው ተቃውሞ | ዓለም | DW | 03.03.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

በየመን የቀጠለው ተቃውሞ

ካለፉት በርካታ ሳምንታት ወዲህ በየመን በአስር ሺህ የሚቆጠር ህዝብ በሀገሪቱ ፕሬዚደንት አሉኢ አብዱላ ሳሌህ አንጻር ተቃውሞውን እንደቀጠለ ይገኛል።

default

ትናንት በደቡብ የመን የኤደን ከተማ በፕሬዚደንት ሳሌህ ደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎች፡ እንዲሁም በተቃዋሚዎችና በጸጥታ ኃይላት መከከል በተፈጠረ ግጭት አራት ሰዎች ተገድለዋል። የሀኪም ቤት ሰራተኞች እንዳስታወቁት፡ ሌሎች አራትም በጠና ቆስለዋል። ስለየመን ጊዚያዊ ሁኔታ አርያም ተክሌ የሚከተለውን ዘገባ አጠናቅራለች።

Jemen Demonstration Proteste gegen die Regierung in Sanaa


በየመን ፕሬዚደንት አሊ አብዱላ ሳሌህ አንጻር በተጀመረው  ተቃውም መሪነቱን የያዙት ወጣቶች ፕሬዚደንቱ ስልጣናቸውን አሁኑኑ እንዲለቁ እየጠየቁ ነው። ይህንኑ የህዝብ ዓመጽ አሁን ትልቆቹ የየመን ተቃውሞ ቡድኖች እና በህብረተሰቡ ውስጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያላቸው በርካታ የጎሳ አባላት ተቀላቅለውታል። ፕሬዚደንት ሳሌህ ከትናንት በስቲያ በሰንዓ ዩኒቨርሲቲ ባሰሙት ንግግር ላይ የሀገራቸውን ተቃውሞ የቀሰቀሱት የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ ናቸው እስከማለት ርቀው መሄዳቸው የሚገኙበትን አዳጋች ሁኔታ እንደሚያሳይ አቡ ዳቢ የሚገኘው የጀርመናውያኑ የአኮንራድ አድናወር የፖለቲካ ተቋም ኃላፊ ቶማስ ቤሪንገር ገልጸዋል።
« ከተቃውሞው በስተጀርባ የዩኤስ አሜሪካ እጅ አለበት ማለታቸው የማይረባ አነጋገር ነው። እንደሚታወቀው ዩኤስ አሜሪካ የፕሬዚደንት ሳሌህ ትልቋ ደጋፊ ናት። አሜሪካውያኑ ሳሌህን የየመንን አንድነት ጠብቀው ማቆየት የሚችሉ ብቸኛው መሪ አድርገው ነው የሚመለከቱዋቸው። እና ሳሌህ አሁን እንዲህ ዓይነቱን ወቀሳ መሰንዘራቸው ሀገሪቱ የምትገኝበት አዳጋች ሁኔታ ያሳያል። »
የየመኑ ፕሬዚደንት ለዚሁ አነጋገራቸው አሁን ዩኤስ አሜሪካን ይቅርታ መጠየቃቸው ተሰምቶዋል።  ብዙዎች የተለያዩት ወገኖች የጀመሩት ተቃውሞ በሀገሪቱ ፈጣኑን ለውጥ ያስገኛል ብለው ይገምታሉ። የኮንራድ አድናወር የፖለቲካ ማዕከል ኃላፊ ቶማስ ቤሪንገር ግን ይህንን ይጠራጠሩታል።
« ለውጥ ለማስገኘት በቂ ነው ብሎ ለመናገር አዳጋች ነው። ምክንያቱም ተቃውሞውን የሚያካሂዱት የተለያየ ዓላማ ያላቸው ወገኖች ናቸውና። »
በበርሊን የሚገኙት የፖለቲካ ተንታኝ ሀማዲ ኤል አውኒ በየመን ተቃውሞ የተሳተፉት ወገኖች የተለያየ ዓላማ አላቸው መባሉን ቢደግፉም፡ ሁሉም አንድ የሚጋሩት ሀሳብ መኖሩን ገልጸዋል።
«   የየመን ዓብዮትን የጀመሩት የሰንዓ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ፡ በደቡብ የመን የሚገኙት የቀድሞ ሶሻሊስቶች እና   በተራራማው አካባቢ የሚኖሩ የጎሳ አባላትናቸው። እነዚህ ሶስት የተለያዩ ቡድኖች የሚጋሩት አንድ ሀሳብ አለ። ይኸውም ከአሊ አብዱላ ሳሌህ እና ከፈላጭ ቆራጭ አገዛዛቸው ለመላቀቅ እና በሀገሪቱ ፍትሃዊ የምጣኔ ሀብት እንዲኖር መፈለጋቸው ነው። »

ይህ በዚህ እንዳለ፡ እስከ ሁለት ቀናት በፊት ድረስ ፕሬዚደንት ሳሌህ ከስልጣን ካልወረዱ በስተቀር ተቃውሞአቸውን እንደማያበቁ ሲናገሩ የነበሩት አንዳንድ የተቃዋሚ ወገኖች በሀገሪቱ ሰላማዊ የስልጣን ዝውውር ሊገኝ የሚችልበትን ዕቅድ ለፕሬዚደንቱ  አቅርበዋል።
ዕቅዱ የህገ መንግስት ለውጥ   እንዲደረግ፡ አዲስ የምርጫ ህግ እንዲወጣ፡ በመንግስቱ እና በጦር ኃይሉ የሚገኙ የፕሬዚደንቱ ዘመዶች እንዲነሱ እና የህዝቡ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብቱ እንዲከበር ይጠይቃል።

አርያም ተክሌ
ሂሩት መለሰ