በዛምቢያ የታሠሩት 137 ኢትዮጵያውያን | አፍሪቃ | DW | 01.01.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

በዛምቢያ የታሠሩት 137 ኢትዮጵያውያን

137 ኢትዮጵያውያን ዛምቢያ ዉስጥ መታሠራቸው ተሰማ። ወደ ደቡብ አፍሪካ በሕገ-ወጥ መንገድ በመጓዝ ላይ ሳሉ ከታሠሩት መካከል አስራ ሁለቱ የ15 ዓመታት እሥራት ተበይኖባቸዋል። መረጃዉን ወደ ዶቼ ቬለ በመደወል ያደረሱት ከታሣሪዎቹ አንዱ፤ ከታሠሩ ዓመታት እንዳለፏቸዉ አመልክተዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:09
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:09 ደቂቃ

በዛምቢያ የታሠሩት 137 ኢትዮጵያውያን

ከኢትዮጵያ ወደ ደቡብ አፍሪካ በጉዞ ላይ የነበሩ 137 ኢትዮጵያውያን በዛምቢያ መታሰራቸው ተሰምቷል። ከአንድ መቶ ሰላሳ ሰባቱ መካከል አስራ ሁለቱ በዛምቢያ የ15 አመታት እስር ተበይኖባቸዋል። «ያለፉትን አራት አመታት በእስር ቤት አሳልፊያለሁ።» የሚሉት ስማቸውን ያልነገሩን ኢትዮጵያዊ «እየሞትን ነው» በማለት የድረሱልን ጥሪ ያሰማሉ።«እኛ አስራ ሁለት ኢትዮጵያውያን የተፈረደብን አስራ አምስት ነው። አራት አመት እስር ቤት ተቀምጠናል። የኢትዮጵያ መንግስት ያደረገልን ምንም ነገር የለም።» ይላሉ ግለሰቡ።

አቶ ኪዳኔ አርዓያ በዛምቢያ ለ አስራ አንድ አመታት ኖረዋል። በአንድ የግለሰብ ሱቅ ውስጥ በአስተዳደር ሥራ ይተዳደራሉ። ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በእስር ላይ የሚገኙትን የሚጎበኙትና ጉዳያቸውን የሚከታተሉት አቶ ኪዳኔ ከአስራ ሁለቱ መካከል አንዷ እንስት መሆኗን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ኢትዮጵያውያኑ በሕገ-ወጥ መንገድ በዛምቢያ በመገኘታቸው ለእስር መዳረጋቸውን ያረጋገጡት አቶ ኪዳኔ «ከአገራችን ተስማምተን መጥተናል» የሚል ቅጽ በመፈረማቸው የፍርድ ውሳኔው ሳይከብድባቸው እንዳልቀረ ተናግረዋል። ኢትዮጵያውኑ ቀደም ሲሉ በዛምቢያ ዋና ከተማ ሉሳካ በሚገኝ እስር ቤት የነበሩ ቢሆንም በቅርብ ጊዜ ከፍተኛ የጸጥታ ጥበቃ ወደ ሚደረግለት የካዎቦይ ማረሚያ ቤት ተዘዋውረዋል።

በአፍሪቃ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት አስመዝግበዋል ከሚባሉት አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ብትሆንም ዜጎቿ ግን የተሻለ የስራ እና የኑሮ ሁኔታ ፍለጋ አገራቸውን ጥለው ይሰደዳሉ። ኢትዮጵያውያኑ በህጋዊም ይሁን ህገ-ወጥ መንገድ ለመግባት ከሚሞክሩባቸው አገራት መካከል ደቡብ አፍሪቃ አንደኛዋ ናት። ስደተኞቹ ከኢትዮጵያ ተነስተው ደቡብ አፍሪቃ በሚያደርጉት ጉዞ የበርካታ አገራትን ድንበር ያቋርጣሉ። በሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች የሚቀናበረው ጉዞ በርካታ ፈተናዎች የሚታለፍበት ነው። በርካታ ኢትዮጵያውያን ለእስር፣እንግልትና ሞት ይዳረጋሉ።

እንደ አቶ ኪዳኔ ከሆነ አስራ አምስት አመታት እስር ከተፈረደባቸው በተጨማሪ ሌሎች 125 ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግለት የዛምቢያ ካዎቦይ እስር ቤት ይገኛሉ። ኢትዮጵያውያኑ በሕገ-ወጥ መንገድ በዛምቢያ በመገኘታቸው ፍርዳቸውን በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ አቶ ኪዳኔ አርዓያ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በዛምቢያ ኤምባሲ የላትም። የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በዚምባብዌ የኢትዮጵያ ኤምባሲን ለማግኘት ያደረግንው ጥረትም አልተሳካም። በዙምባብዌ የኢትዮጵያ አምባሳደር ጉዳዩን ያውቁታል የሚሉት ኪዳኔ አርዓያ አመርቂ እርምጃ አልተወሰደም ሲሉ ይተቻሉ።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic