በዚምባብዌ ዉስጥ የታሰሩ ኢትዮጵያዉያን  | አፍሪቃ | DW | 06.01.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

በዚምባብዌ በእስር ላይ የሚገኙ 34 ኢትዮጵያውያን ትርጁማን ይፈልጋሉ

በዚምባብዌ ዉስጥ የታሰሩ ኢትዮጵያዉያን 

ወደ ደቡብ አፍሪቃ  ለመግባት በጉዞ እያሉ የዚምባቡዌ ፀጥታ አስከባሪዎች ያሰሯቸዉ  34 ኢትዮጵያውያን ትናንት  ክስ ተመሰረተባቸው። አራት ሕጻናትን ጨምሮ ፍርድ ቤት ከቀረቡት ከ34ት ኢትዮጵያውያን መካከል እንግሊዘኛ መናገር የሚችለው አንዱ ብቻ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ትርጁማን እየፈለገ ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:28
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:28 ደቂቃ

በዚምባብዌ የታሰሩ 34 ኢትዮጵያውያን ትርጁማን ይፈልጋሉ

የዚምባብዌን የፍልሰት ሕግ ጥሰዋል የሚል ክስ የቀረበባቸው 34 ኢትዮጵያውያን ከሐራሬ 80 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ በምትኘው የማሮንዴራ ከተማ በትናንትናው ዕለት ከችሎት ቀርበዋል። ከማሮንዴራ ከተማ አቅራቢያ ከሚገኝ የእርሻ ማሳ ውስጥ ተደብቀው ከተያዙት 34 ስደተኞች መካከል አራቱ  የአስራ አንድ እና የአስራ ሁለት ዓመት ታዳጊ ወጣቶች ናቸዉ። ስደተኞቹ እስከ ጥር 21/2009 ዓ.ም. ድረስ ማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ፍርድ ቤቱ መወሰኑን ኒውስ ዴይ የተሰኘው የዚምባብዌ ጋዜጣ ዘግቧል። ወደ ደቡብ አፍሪቃ ለመጓዝ የሚነሱት ኢትዮጵያውያን ኬንያ፤ ታንዛኒያ፤ማላዊ እና ሞዛምቢክን በማቋረጥ ወደ ዚምባብዌ እንደሚገቡ በሐራሬ የዶቸ ቬለ ወኪል ሙስቫንሂሪ ፕሪቪሌጅ ይናገራል።  

«የተፈጠረው ምንድነው ወደ ድንበር ሲቃረቡ ወደ ደቡብ አፍሪቃ ድንበር የሚመሯቸው ሁለት የዚምባብዌ የሰዎች አሸጋጋሪዎች ተቀብለዋቸዋል። ሐራሬ ከመድረሳቸው በፊት አሸጋጋሪዎቹ በማሮንዴራ ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ ማሳ ውስጥ ስደተኞቹን ትተዋቸው ምግብ ፍለጋ በሔዱበት ጥቆማ የደረሰው ፖሊስ ኢትዮጵያውያኑን በቁጥጥር ሥር አውሏቸዋል።» 

ኒውስ ዴይ  ጋዜጣ ታኅሳስ 7 ቀን ኢትዮጵያውያኑን ሙቶኮ ከተሰኘችው አነስተኛ ከተማ ወደ ማሮንዴራ ያጓዟቸው ክሌቶ ኒያንዶሮ እና ጊፍት ቤሬ የተባሉ የዚምባብዌ ዜጎች መሆናቸውን የፍርድ ቤት ሰነዶች ጠቅሶ ዘግቧል። የሰዎች አሸጋጋሪዎቹ ኢትዮጵያውያኑን ከደቡብ አፍሪቃ ድንበር አቅራቢያ ከምትገኘው የባይትብሪጅ ከተማ ድረስ ሊወስዷቸው እንደነበር ጋዜጣው ጨምሮ ዘግቧል። ፕሪቪሌጅ የዚምባብዌ ፍርድ ቤት ለተከሳሾቹ ትርጁማን ከኢትዮጵያ ኤምባሲ እየፈለገ መሆኑን ተናግሯል።

«ከ34 ኢትዮጵያውያን መካከል እንግሊዘኛ መናገር የሚችለው አንድ ብቻ ነበር። ቀሪዎቹ እንግሊዘኛ መናገር አይችሉም። ፍርድ ቤቱ ትናንት ጉዳዩን በቀጠሮ ለመመልከት የወሰነው በዚህ ምክንያት ነው። ጃንዋሪ 19 ተመልሰው ከፍርድ ቤት ይቀርባሉ። እስከዚያው ድረስ ግን በእስር ላይ ይቆያሉ። ተከሳሾቹ ተመልሰው ከፍርድ ቤት ሲቀርቡ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ትርጁማን እንዲያገኙ ለማድረግ እየጣረ ነው።»

የተሻለ ኑሮ እና የሥራ እድል ፍለጋ ወደ ደቡብ አፍሪቃ ለመጓዝ የበርካታ አገራት ድንበርን ሲያቋርጡ ለእስር የተዳረጉ ኢትዮጵያውያን እነዚህ ብቻ አይደሉም። ባለፈው ሚያዝያ በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ተሻግራችኋል የተባሉ 40 ኢትዮጵያውያን በኬንያ በቁጥጥር ሥር ውለዋል። ዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት (IOM) በጎርጎሮሳዊው 2009 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው በዓይነቱ ለየት ያለ ጥናት ከ17,000 እስከ  20,000 የሚደረሱ የምሥራቅ አፍሪቃ አገራት ዜጎች በየዓመቱ ወደ ደቡብ አፍሪቃ ይጓዛሉ ሲል አትቷል። ጥናቱ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን እና ሶማሊያውያን መሆናቸውን አልሸሸገም። ጋዜጠኛ ፕሪቪሌጅ እንደሚለው ከተጓዦቹ መካከል መዳረሻቸው የስደተኞች መጠለያ የሆነ ይገኝበታል።
«አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ወደ ደቡብ አፍሪቃ ለማቅናት በኬንያ፤ታንዛኒያ፤ማላዊ እና ሞዛምቢክ እና ዚምባብዌን የሚያቋርጠውን የስደት መስመር ይመርጣሉ። ዚምባብዌ ከደረሱ በኋላ በሌሊት ድንበር የሚያቋርጡ የጭነት ተሽከርካሪዎችን ይመርጣሉ።» የሚለው ሙስቫንሂሪ ፕሪቪሌጅ ብዙውን ጊዜ ስደተኞቹ ከመጠለያ ጣቢያ በመውጣት ወደ ደቡብ አፍሪቃ ለመሻገር እንደሚሞክሩም ተናግሯል። 


እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ 

Audios and videos on the topic