በዚምባቡዌ የሚካሄደዉ አወዛጋቢ ምርጫና የሮበርት ሙጋቤ መግለጫ | የጋዜጦች አምድ | DW | 31.03.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

በዚምባቡዌ የሚካሄደዉ አወዛጋቢ ምርጫና የሮበርት ሙጋቤ መግለጫ

ዓለም በትኩረት ሲከታተለዉ የሰነበተዉ የዚምባቡዌ ብሄራዊ ምርጫ በዛሬዉ እለት ከንጋቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ በመካሄድ ላይ ነዉ። የተለያዩ ዓለም ዓቀፍ የመገናኛ ብዙሃንም ሰፊ ሽፋን ሰጥተዉታል።

የዚምባቡዌ ተቃዋሚ ፓርቲ MDC ደጋፊ የዚምባቡዌን ምርጫ አስመልክቶ በተካሄደዉ የመኪና ዉድድር ላይ

የዚምባቡዌ ተቃዋሚ ፓርቲ MDC ደጋፊ የዚምባቡዌን ምርጫ አስመልክቶ በተካሄደዉ የመኪና ዉድድር ላይ

መራጮች ከመቼዉ ጊዜ በተለየ በየምርጫ ጣቢያዉ በነፃነት እየመረጡ መሆኑ ተገልጿል። ወታደሮችም ሆኑ ፓሊሶች በምርጫ ጣቢያዎች አካባቢ አልተሰማሩም የሚለዉ የወኪሎቻቸዉ ዘገባ ቢኖርም ጥርጣሬዉ አልተለወጠም።
ለተነሱበት ዓላማ ቁርጠኝነታቸዉን በይፋ ያሳዩት የ81 ዓመቱ ዓዛዉንት ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤም ጡረታ የሚወጡበት ጊዜ ካልደረሰ በቀር ስልጣኑን የሚለቁ አይመስሉም። የምርጫዉ ዉጤት ከ48 ሰዓታት በኋላ ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
ምርጫዉ ነፃና ፍትሃዊ ለመሆኑ ምን ማረጋገጫ ይሰጣሉ? በሚል ለቀረበላቸዉ ጥያቄ ሙጋቤ ሲመልሱ ምርጫዉ ነፃና ፍትሃዊ ነዉ ወታደር በየምርጫ ጣቢያዉ አይኖርም፤ ህዝቡም የፈለገዉን መምረጥ ይችላል። ግን ለመሆኑ የትኛዉ አገር ነዉ ላካሄደዉ ምርጫ ነፃና ፍትሃዊነት ማረጋገጫ የሰጠን? መልሰዉ ጋዜጠኛዉን አፋጠጡት።
ክቡር ፕሬዝዳንት በዚህ አጋጣሚ ለአሜሪካ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ? ለአሜሪካ በተለየ የማስተላልፈዉ መልዕክት የለኝም ለመላዉ ዓለም መግለፅ የምፈልገዉ አገሬ በብሌየር ላይ ድልን እንደምትቀዳጅ እርግጠኛ መሆኔን ነዉ።
ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ በትናንትናዉ እለት ከዉጪም ሆነ ከአገር ዉስጥ ጋዜጠኞች ለቀረበላቸዉ ጥያቄ በሙሉ ልብ ነበር ምላሽ የሰጡት።
ጋዜጠኞቹ ቀጠሉ ክቡር ፕሬዝዳንት በአሁኑ ጊዜ ዓለም አንድ እየሆነች የእርስዎ አገር ለምን እንድትነጠል ፈለጉ? ሙጋቤ የምፀት ፈገግታ አሳዩ በፍፁም አልተነጠልንም ከዓለም መነጠል ከብሌየር ጋር አለመተባበር ከሆነ ትርጉሙ ሌላ ይሆናል።
እኛ የአፍሪካ ህብረት፤ የሳዲክ የኔፓድ አባል ነን በርካታ ወዳጆችና ደጋፊዎች አሉን። በአዉሮፓም ቢሆን ፈረንሳይና ጣሊያን፤ በእስያም ቻይናና ህንድ ሌሎችም ወዳጆቻችንን መጥቀስ ይቻላል። ስለየትኛዉ መገለል እንደምታወራ አልገባኝም? ኮስተር አሉ።
እንደ የአዉሮፓ ህብረት የመሳሰሉ ታዛቢዎች ምርጫዉ የቀልድና የማጭበርበር ነዉ የሚል አስተያየት አላቸው? ሙጋቤ የዚህን ጊዜ የተደሰቱ ነዉ የሚመስሉት ለእነሱ እንደዚያ ሊሆን ይችላል ለእኛ ግን የለመድነዉን ስርዓት የተከተለ ዉጤታማ የሚሆን የእዉነት ምርጫ ነዉ። ቁርጥ ያለ ምላሽ።
ከሶስት አመት በፊት ከተካሄደዉ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በኋላ በዚምባቡዌ ላይ ማዕቀብ የጣሉት ዩናይትድ ስቴትስና የአዉሮፓዉ ህብረት በዘንድሮዉ ምርጫ ታዛቢ እንዲልኩ አልተጠየቁም።
በዚያም ቢባል በዚህ ሙጋቤ ፓርቲያቸዉ በምርጫዉ ማሸነፉን እሳቸዉም በስልጣን መሰንበታቸዉን እርማችሁን አዉጡ በሚል መልኩ ነዉ ለወዳጅም ለጠላትም በይፋ የተናገሩት።
በዚምባቡዌ በሚካሄደዉ ምርጫ በምክር ቤቱ ላለዉ 150 መቀመጫ ሳይሆን ለ120ዉ ነዉ ፉክክሩ ምክንያቱም በህጋቸዉ መሰረት ቀሪዉ 30 መቀመጫ ፕሬዝዳንቱ በሚመርጡት ቡድን የሚያዝ ይሆናል።
ይህም ከያቅጣጫዉ ትችት ያስነሳባቸዉ ቢሆንም ፕሬዝዳንት ሙጋቤ ከዉሳኔያቸዉ ንቅንቅ አላሉም። ከአምስት አመት በፊት በተካሄደዉ ምርጫ 57ቱ መቀመጫ በዲሞክራሲያዊ ለዉጥ እንቅስቃሴ በእንግሊዝኛዉ ምህፃረቃል MDC በተሰኘዉ ተቃዋሚ ፓርቲ ሲያዝ 62ቱ መቀመጫ ደግሞ የሙጋቤ ገዢ ፓርቲ የዛኑፒኤፍ ነበር። ቀሪዉ ደግሞ በስርዓቱ መሰረት በዛኑፒኤፍ ደጋፊዎች።
ምንም እንኳን በአገሪቱ ሌሎች ሶስት ተቃዋሚ ፓርቲዎችና የግል ተወዳዳሪዎች ቢኖሩም ትንሽ ጠንከር ብሎ የሚፎካከረዉ ፓርቲ MDC ነዉ።
ይህ ፓርቲ ደግሞ በፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ አገላለፅ በዚምባቡዌ ነፃነት የማያምኑ የብሌየርና የደጋፊዎቻቸዉ አሻንጉሊት ነዉ።
ሙጋቤን በተለይ ከምዕራባዉያን ነጭ ወዳጆቻቸዉ ያቆራረጣቸዉ የመሬት ጉዳይ ዚምባቡዌና የእሳቸዉ ስም በተጠራበት ሁሉ የሚነሳ ጉዳይ ሆኗል።
ከምርጫዉ ጋር አያይዘዉ የመሬቱን ጉዳይ አነሱባቸዉ ሙጋቤ እንደተለመደዉ ቃላቸዉ አንድነበር መሬቱ የዚምባቡዌያዉያን ነዉ እንጂ የአዉሮፓዉያን አይደለም። የተደረገዉ የመሬት ድልድል ተገቢ ነበር ምክንያቱም መሬቱን ለባበቤቱ ነዉ የመለስነዉ ከእኛጋ መስራት የሚፈልጉ ከሆነ በእኛ ህግ ሳይንቁን መስራት ይችላሉ።
ከዚህ ምላሻቸዉ በመነሳትም አወዛጋቢዉ የዚምባቡዌ ምርጫና አወዛጋቢዉ የፕሬዝዳንት ሙጋቤ ንግግር የሚል ርዕስ ተሰጥቶት ነበር በመገናኛ ብዙሃን የቀረበዉ። በምርጫ ጣቢያዉ በጠዋት ከተገኙት የመጀመሪያ መራጮች መካከል አንዱ ነበሩ የተፎካካሪዉ ፓርቲ የMDC መሪ ሞርጋን ሳቫንጊሬ።
ለጋዜጠኞች እንደገለፁት ለዉጥ በዚምባቡዌ እየመጣ ነዉ ህዝቡ እንደሚነግራቸዉና እሳቸዉም እንዳዩት ድሉ የፓርቲያቸዉ የሚሆንበት ቀን ቀርቧል።
የመንግስት የሆነዉ የሃራሬ ሄራልድ ጋዜጣ ደግሞ ከሌሎች ዜጎች የተለየን አድርጎ የቀረፀንን መሪ ፓርቲያችንን የምንመርጥበት ጊዜ ደረሰ በሚል ድጋፉን ለዛኑፒኤፍና ለፀረ ቅኝ አገዛዝ ትግሉ ያደረገበትን ዘገባ አዉጥቷል።
ሁኔታዉ ሲታይ በወሰዷቸዉ እርምጃዎች በተለያዩ ጊዜያት የተጣለባቸዉ ማዕቀብና የቀድሞ ወዳጆቻቸዉ ፍት መንሳት ከአቋማቸዉ ያላናወጣቸዉ ፕሬዝዳንት ሙጋቤ የመጨረሻ ፍልሚያ ይመስላል።