በዓባይ ፕሮጀክት ላይ የግብጽ ኢትዮጵያ ልዩነት | ራድዮ | DW | 06.11.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ራድዮ

በዓባይ ፕሮጀክት ላይ የግብጽ ኢትዮጵያ ልዩነት

የስብሰባው ዓላማ በውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ጉዳይ ሃላፊ አቶ ፈቂህ ኣህመድ እንደሚሉት የፕሮጀክቱን ሂደት የሚከታተል የጋራ ኮሚቴ ለማቐቐም ነበር። በዚሁ መሰረትም ግብጽ ኢትዮጵያ እና ሱዳን የሶስትዮሽ ኮሚቴ ለማቋቋም የተስማሙ ቢሆንም በኮሚቴው አባላት ስብጥር ላይ ግን ግብጽና ኢትዮጵያ ሳይስማሙ ቀርቷል።

በአባይ ግድብ ፕሮጀክት ላይ ለመምከር ኢትዮጵያ ግብጽ እና ሱዳን ትላንት በካይሮ ባካሄዱት የሚኒስትሮች ስብሰባ በልዩነት መለያየታቸው ተሰማ።

የስብሰባው ዓላማ በካርቱም ምንጮች መሰረት የፕሮጀክቱን ሂደት የሚከታተል የሶስትዮሽ ኮሚቴ ለማቐቐም ሲሆን በኮሚቴው ስብጥር ላይ የኢትዮጵያና የግብጽ ሚኒስትሮች ሊስማሙ ኣልቻሉም።ኢትዮጵያ ኮሚቴው በሶስቱ ኣገሮች ባለሙያዎች ብቻ እንዲዋቀር ስትፈልግ ግብጽ ደግሞ ዓለም ዓቀፍ ቡድን እንዲሆን ትሻለች።

ይሁንና ሶስቱ ኣገሮች በኣንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተመልሰው ለመገናኘት መስማማታቸው ታውቋል።

በኢትዮጵያ በኩልም ቢሆን ሳይታሰብ ድንገት ይፋ ሆኖ ወዲያውኑ የተጀመረው እና ገና ከጅምሩ ደግሞ በተለይ ከግብጽ በኩል ማለት ይቻላል ተቃውሞ የገጠመው ታላቁ የዓባይ ግድብ ፕሮጀክት በመሪዎች ደረጃ ሳይቀር ብዙ ሲያነታርክ መቆየቱ ይታወቃል።

በተለይም ፕሬዝደንት ሙርሲ በስልጣን በነበሩበት ወቅት ውጥረቱ ወደ ጦርነት ሊያመራ ይችላል የሚል ስጋት ደቅኖ የነበረ ሲሆን የሙርሲን መወገድ ተከትሎ ግን ውጥረቱ ጋብ እንደማለት ብሎ ነበር። ይሁን እንጂ የሁለቱን ኣገሮች ኣቐም ኣቀራርቦ ከኣንድ ኣስተማማኝ መቐጫ የሚያደርስ ስምምነት ገና ባለመደረሱ ኣጋጣሚን ጠብቆ ልዩነት መንጸባረቁ ኣልቀረም። ትላንት በሱዳኗ መዲና በካርቱም ተካህዶ በነበረው የሶስትዮሽ የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይም የታየው ይኸው ነበር።

Blauer Nil Wasserfall Äthiopien

የስብሰባው ዓላማ በውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የድንበር እና ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፈቂህ ኣህመድ እንደሚሉት የፕሮጀክቱን ሂደት የሚከታተል የጋራ ኮሚቴ ለማቐቐም ነበር። በዚሁ መሰረትም ግብጽ ኢትዮጵያ እና ሱዳን የሶስትዮሽ ኮሚቴ ለማቐቐም የተስማሙ ቢሆንም አቶ ፈቂህ እንደሚሉት በኮሚቴው አባላት ስብጥር ላይ ግን ግብጽና ኢትዮጵያ ሳይስማሙ ቀርቷል።

ያም ሆኖ ሚኒስትሮቹ እ ኣ ኣ የፊታችን ታህሳስ 8 ቀን እዚያው ካርቱም ላይ ተመልሰው ለመገናኘት የተስማሙ ሲሆን የግብጽ ስጋት ኣሁንም በካይሮ ምንጮች መሰረት የአባይ ግድብ የናይልን የውኃ መጠን ይቀንስብኛል የሚል ነው። አቶ ፈቂህ ግን ይህ ግብጽን ሊያሰጋት ኣይገባም ባይ ናቸው። ምክኒያቱም አቶ ፈቂህ እንደሚሉት የግብጹ ታላቁ የኣስዋን ግድብ ለግብጽ ፍጆታ ለሶስት ዓመት የሚበቃ የውኃ ክምችት ስላለው የህዳሴ ግድብ እስኪሞላ ድረስ ግብጽ ከኣስዋን የመጠባበቂያ ክምችት መጠቀም ትችላለች። ለዚያውም ኢትዮጵያ ለግድቡ በየዓመቱ የምታስቀረው የውኃ መጠን በጣም አነስተኛ መሆኑንም ኃላፊው ጠቂሟል።

ካለፈው ግንቦት ወር ኣንስቶ ኢትዮጵያ የአባይን ወንዝ አቅጣጫውን ቀይራ በሌላ በኩል እንዲፈስ ማድረጘ ይታወቃል። የዚህ ፕሮጀክት ግንባታ ሲጠናቀቅ በኣፍሪካ ትልቄ የኃይል ማመንጫ ግድብ እንደሚሆን እየተነገረለት ያለው የህዳሴ ግድብ እ ዘ ኣ በ2017 ሲጠናቀቅ 6000 MW የኤሌኬትሪክ ኃይል የማመንጨት ኣቅም ይኖረዋል ተብሎ ይገመታል። በኣሁኑ ጊዜ ግንባታው 26 በመቶ ተጠናቐልም ተብሏል።

በናይል ወንዝ ላይ ታሪካዊ የሆነ ልዩ የባለቤትነት መብት ኣለኝ የምትለው ግብጽ መከራከሪያዋም እ ዘ ኣ በ 1929 እና 1959 የተፈረሙት ዓ/ዓቀፍ ውሎች ናቸው። በእነዚህ ውሎች መሰረት ግብጽ 87 በመቶ የሚሆነውን የናይልን ውኃ ጠቅልላ በመውሰድ የአንበሳ ድርሻ ሲኖራት በናይል ተፋሰስ ላይ የሚሰሩ ማናቸውንም ፕሮጀክቶች ኣስመልክቶ ደግሞ ውሉ ለግብጽ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብትም ያጎናጽፋታል።

ጃፈር ዓሊ