በዑጋንዳ የዳኞች ስራ ማቆም | የጋዜጦች አምድ | DW | 28.11.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

በዑጋንዳ የዳኞች ስራ ማቆም

የዑጋንዳ ዳኞችና ጠበቆች ታጣቂዎች በፍርድ ቤት ግቢ መገኘታቸዉን በመቃወም በዛሬዉ ዕለት የስራ ማቆም አድማ አደረጉ። በዑጋንዳዉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሚሰሩት እነዚህ የህግ ባለሙያዎች በእስር ላይ የሚገኙ የመንግስት ተቃዋሚዎች ፍርድ ቤት በቀረቡበት ወቅት መሳሪያ አንግበዉ ወደፍርድ ቤቱ ግቢ የገቡት ታጣቂዎች ድርጊት በአገሪቱ ያለዉን የፍትህ ነፃነት የሚጋፋ ሲሉ ኮንነዋል።

በነፃነት ሲንቀሳቀሱ የቆዩት የዑጋንዳ መገናኛ ብዙሃንና ህዝቡ ጥቁር መርዘኛ እባብ በሚል ቅፅል ነዉ የሚጠሯቸዉ በዑጋንዳዉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ችሎት ላይ የተገኙትን የመንግስት ታጣቂዎች።
ኮማንዶዎቹ በችሎቱ ቅጥር ግቢም ጥቁር ቲሸርት በመልበስ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ታጥቀዉ ነዉ ባለፈዉ ህዳር 6ቀን ከአንድ ሰዓት በላይ የታዩት። በሌላ ጊዜ በድጋሚ ደግሞ ካኪዉን የፖሊስ የደንብ ልብስ።
ድርጊታቸዉም መንግስት ያሰራቸዉ የተቃዋሚ ፖለቲከኞች የፍርድ ሂደት ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር በመሆኑ የህግ ባለሙያዎቹ አጥብቀዉ እንደሚቃወሙት ገልፀዋል።
ዳኞቹ እንደሚሉት ይህን መሰሉ ድርጊትና ሙከራ አረመኔና አምባገነን በነበሩት በቀድሞዉ ኢዲ አሚን ዘመን ታፍነዉ የተገደሉትን የከፍተኛ ዳኛ ቤን ኪዋኑካን መራር ገጠመኝ አስታዉሷቸዋል።
የዑጋንዳ የህግ ማህበሰብ ፕሬዝደንት ሞሰስ አድሪኮ ነፃና ዲሞክራሲ በሰፈነበት ህብረተሰብ ዉስጥ የታጠቁ ኃይላት ሊያስፈራሩም ሆነ በፍትህ ሂደት ጣልቃ ለመግባት መሞከራቸዉ ተቀባይነት የለዉም ነዉ ያሉት።
ጨምረዉም መንግስት ራሱን የመግዛትና የመቆጣጠር ልማድን ማዳበርና ህገመንግስቱን የማክበር ግዴታ እንዳለበት ጠቅሰዉ እንዲህ ያለዉን ህገወጥ ተግባር ማስወገድ ይኖርበታል ብለዋል።
በፍርድ ቤቱ ይካሄድ የነበረዉ ዕለታዊ ተግባርም የህግ ባለሙያዎቹ ጥቁር ካባቸዉን ለብሰዉ በረንዳዉ ላይ በተሰቡበት የተቃዉሞ ሂደት ተስተጓጉሏል።
ዴቪድ ምፓንጋ የተባሉት ዳኛም መንግስት ሊያዉቀዉ የሚገባዉ ይህን መሰሉ ድርጊት የአገሪቱን ገፅታ በዓለም ፊት የሚያበላሽ ከመሆኑም በላይ የህግ ኃይን ከሌላዉ ኃይል መነጠል እንደሚያስፈልግ ነዉ ብለዋል።
የፍትህ ሂደት ካልተከበረ የሚታዩትና የሚከሰቱ ልዩነቶች ሁሉ በወታደራዊ ኃይል ለመፈታት የግድ የሚሆኑበት አጋጣሚ እንደሚፈጠር በመጥቀስም የአገሪቱ መንግስት አካሄዱን እንዲያጤነዉ አስገንዝበዋል።
ሌላዋ ዳኛ ኢሚሊ አኮራም ተቃዋሚ የሙያ ባልደረቦቻቸዉ የተቀላቀሉት በበኩላቸዉ በድርጊቱ ተመሳሳይ የተቃዉሞ ድምፅ ለማሰማት እንደሆነ በመግለፅ ወደፊት በመጓዝ ላይ በምትገኘዉ ዑጋንዳ ይህን መሰል ተግባር መፈፀም አገሪቱን ከዲሞክራሲያዊ እርምጃዋ ወደኋላ ለመመለስ መሞከር መሆኑን አስረድተዋል።
የህግ ባለሙያዎቹ የወሰዱት የተቃዉሞ እርምጃ የአገሪቱ መንግስት የቤሲጄን ጉዳይ አስመልክቶ በሚካሄደዉ የፍትህ ሂደት ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል በሚል ተቃዉሞ እንዳይደረግ የጣለዉን እገዳ መጣስ አለመጣሱ ግን ግልፅ አይደለም።
በመጪዉ መጋቢት አጋማሽ በሚካሄደዉ ምርጫ የሙሴቪኒ ቀንደኛ ተፎካካሪ እንደሚሆኑ ሲጠበቁ የነበሩት ቤሲጄ በአገር መክዳት ወንጀልና በአስገድዶ መድፈር በተጨማሪም ከሽብርና ከህገወጥ ጦር መሳሪያ ወንጀሎች ጋር በተገናኘ ጉዳያቸዉ በከፍተኛዉ ፍርድ ቤት እየታየ ነዉ።
ባለፈዉ ዓርብ አመሳሹ ላይ በየአገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዋስ መብት ተስጥቷቸዉ የነበሩት ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ቤሲጄ ከጦሩ በተሰነዘረባቸዉ ተጨማሪ ክስ ወደወህኒ ተመልሰዉ ተልከዋል።
በዛሬዉ እለትም የዋስ መብትን ለማስከበር የሚሞላዉን ተገቢ ቅፅ ያጠናቅቁ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ ቢሆንም ምን ያህል የተሳካ ሆኖ ይለቀቁ እንደሁ ግን ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸዉ የህግ ባለሙያዎች ገና አላወቁም።
የመንግስት ልሳን ያልሆነዉ ዘሞኒተር የተሰኘዉ ጋዜጣ ከታጣቂዎቹ መካከል የሁለቱን በጥቁር ቲሸርትና በካኪዉ የፖሊስ የደንብ ልብስ እንዳሉ የሚያሳይ ፎቶ ዓርብ ዕለት በፊት ገፁ ላይ ይዞ ወጥቷል።
ይህም በአሁኑ ሰዓት የዑጋንዳ ዋና ከተማ የካምፓላና አካባቢዋ ኗሪዎች መነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ ሆኗል።
የተለየ አለባበስና መሳሪያ መጠቀማቸዉ እንደሚፈጸመዉ የግዳጅ አይነት እንደሚለያይ ለመግለፅ የሞከሩት የፖሊስ ቃልአቀባይ አሱማን ሙጌኒ በዑጋንዳም የጦር ኃይሉ አባላት የፖሊስን ተግባር በተጨማሪነት ሲያከናዉኑ የመጀመሪያ እንዳልሆነ ነዉ የተናገሩት።
የቤሲጄን ጉዳይ የያዙት የከፍተኛዉ ፍርድ ቤት ዳኛ ጄምስ ዖጎላ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ በፍርድ ቤቱ ላይ የተፈፀመ ወረራና ፍርድ ቤትን ያለአግባብ የደፈረ እርምጃ ነዉ ሲሉ ኮንነዉታል።
ሙሴቪኒ ተቃዋሚና ተፎካካሪያቸዉን በአገር መክዳት ወንጀል ወደወህኒ ከጣሉ በኋላ በልዩ ታጣቂዎቻቸዉ ፍርድ ቤቱን ማስደፈራቸዉ በዑጋንዳ መጪዉ ዘመን የተገላገሉትን የቀድሞ አምባገነን ስርዓት መልሶ እንዳያመጣዉ ታዛቢዎች ከወዲሁ ስጋታቸዉን እየገለፁ ነዉ።