በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የፖለቲካ ሳይንስ ተንታኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ | DW | 04.11.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የፖለቲካ ሳይንስ ተንታኞች አስተያየት

በኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ክራይስስ ተንታኝ ዊልያም ዴቪሰን የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና የትግራይ ክልላዊ መስተዳድር የገቡበትን ውጥረት በሚመለከት ለዶይቸ ቬለ እንደሚሉት ከሆነ፤ ሁለቱ አካላት አሁኑኑ ተኩስ አቁም ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:41

በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የፖለቲካ ሳይንስ ተንታኞች አስተያየት

በትግራይ ክልላዊ አስተዳደር እና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በሚመሩት የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት መካከል የነበረው የቃላት ጦርነት አብቅቶ ከትናንት ሌሊት አንስቶ ውጊያ ውስጥ መገባቱን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ አብይ አህመድ የተሰጠው መግለጫ ያመላክታል። ይህ ከመከሰቱ አስቀድሞ የውጭ ኃይል ጣልቃ እንዲገባበት ሲያሳስቡ ከነበሩ የፖለቲካ ተንታኞች መካከል በኢትዮጵያ የኢንተርናሽናል ክራይስስ ተንታኝ ዊልያም ዴቪሰን አንዱ ናቸው። አሁን በትግራይ ክልላዊ አስተዳደር እና በፌደራል መንግሥት መካከል የተፈጠረው የከረረ ግጭት ሀገሪቱ ወሳኝ ጊዜ ላይ ባለችበት ወቅት ነው ይላሉ።  « ይህ የሆነው ሀገሪቱ በተከፋፈለችበት ወቅት ነው።  በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ግጭቶች ተከስተዋል። በተደጋጋሚ የጎሳ ግጭቶች ነበሩ፤ የምርጫው መዘግየት እንዲሁም የተቃዋሚ መሪዎች መታሰር፤ ከዚህም ሌላ ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ የፖለቲካ ችግሮች አሉ ይሁንና የትግራይ ክልል ላይ አሁን በግልፅ የተጀመረው ግጭት ዋንኛው ነው።» 
ይህም ሀገሪቷን ወደ ያልተረጋጋ ሁኔታ ሊከታት ይችላል የሚሉት ዴቬሰን ግጭቱን ያባባሰው የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ብቻውን ያካሄደው ምርጫ ሊሆን እንደሚችል በምሳሌነት ይጠቅሳሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወሰዱት ርምጃስ አግባብ ነበር? « ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ለግጭቱ በምክንያትነት ያቀረቡት ህውሐት ትግራይ በሚገኘው የመከላከያ ካምፕ ላይ ጥቃት አድርሷል የሚል ነው።  የፌደራል መንግሥቱ የሚለው ይህንን ነው። ከትግራይ በኩል ደግሞ ሌላ አይነት ታሪክ ይሰማ ይሆናል።»
ዴቪሰን እንደሚሉት ከሆነ መፍትሔው ግጭቱ እንዳይባባስ ማድረግ ነው።  ይህም ሁለቱ አካላት ተኩስ አቁም ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ከዚህም ሌላ እንደ ዴቪሰን የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ግፊት ማድረግ ይኖርበታል። 
ሌላው በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ዶይቸ ቬለ ያነጋገራቸው  የፖለቲካ ተንታኝ ፕሮፌሰር ሼል ትሮንፎል ናቸው። የግጭት እና ሰላም ጥናት ተመራማሪና በዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የሚሰራው የኦስሎ አናሊስቲካ መሥሪያ ቤት ዳሬክተር የሆኑት ትሮንፎን እንደሚሉት ይህ  ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ኃይላቸውን ለማሳየት የወሰዱት ርምጃ  ሳይሆን ጉዳዩ ውስብስብ ነው።
«ርምጃው ኃይልን ከማሳየት ያለፈ እና ውስብስብ ነው። አብይ አህመድ ከሚመሩት የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት አኳያ ካየነው አስፈላጊ ነበር። » የፌደራል መከላከያ ሠራዊቱን ታማኝነት ጥያቄ ውስጥ የሚከቱት የኖርዌይ ተንታኝ ኢትዮጵያ ውስጥ በፌደራል መንግሥት እና በትግራይ ክልል መካከል ካለው ግጭት ባሻገር ሰርጎ ገብ እንቅስቃሴዎች በምዕራብ ወለጋ እና በመላው በሀገሪቷ መንግስትን ፈታኝ የሆኑ ብዙ ነገሮች አሉ ይላሉ።  «የትግራዩ ግጭት የሰሜን ዕዝን እና ንብረቶቹን ለመቆጣጠር የሚደረግ ነው። የስልክ እና የኢንተርኔት ግንኙነት ከመቋረጡ በፊት ከህወሓት የተሰጠው መግለጫ የሰሜን ዕዝ ወታደሮች እና አዛዦች ዐቢይን ለመዋጋት ወደ እነሱ መክዳታቸውን ገልጿል። ይሁንና ይኸ ትክክል መሆኑ አልተረጋገጠም»
 ስለሆነም የአብይ አህመድ ትልቁ ፈተና የመከላከያ ሠራዊቱን ተዓማኒ አድርጎ ማቆየቱ ይሆናል ይላሉ ትሮንፎል። 


የኢፌድሪ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ጠዋት በትግራይ ክልል ላይ ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁም አስፈላጊ ነበር ሲሉ ትሮንፎል ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል። የፖለቲካ ተንታኙም ከትግራይ ክልል ጋር የነበረው የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት ግንኙነት በመቋረጡ በክልሉ ስላለው ነገር ከሌላ አካል መረጃ ማግኘት መቸገራቸውን ተናግረዋል። አሁን ያላቸው መረጃ ሁለቱ አካላት ውጊያ ላይ እንዳሉ ቢሆንም የተባባሰ ጦርነት ውስጥ ሳይገቡ አሁንም ለማስቆም ይቻላል ይላሉ ትሮንፎል። 
ልደት አበበ

እሸቴ በቀለ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች