በኮንጎ የተባባሰዉ ግጭት | አፍሪቃ | DW | 04.11.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

በኮንጎ የተባባሰዉ ግጭት

የኮንጎ ጦርና አማፂው M 23 ውጊያ ተባብሶ መቀጠሉ ተነገረ። በዴሞክራቲክ ኮንጎ የሚንቀሳቀሱት አማፅያን፤ ከኮንጎ መንግስት ጋር የተቋረጠዉን ድርድር ለመቀጠል፤ ትናንት የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጠይቀዉ ነበር።

ይህ የሆነዉ በተመድ ጦር የሚታገዙት የኮንጎ መንግስት ወታደሮች አማፅያኑን ለማባረር የጀመሩበትን ዉጊያ መግፋታቸዉ ከተገለፀ ከቀናት በኋላ መሆኑ ነዉ። ባለፈዉ ሳምንት የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ወታደራዊ ኃይል በM-23 አማጽያን ላይ የከፈተዉ ጥቃት ትልቅ ስኬት ማሳየቱን መግለፁ ይታወሳል፤
የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ወታደራዊ ኃይል በምስራቅ ኮንጎ የሚንቀሳቀሱት የመጨረሻዎቹን የM23 አማፅያን ለማደን በያዘዉ ዘመቻ ገፍቷል። ከባድ ተኩስ መሰማቱ በአካባቢዉ ላይ ያሉ ነዋሪዎች ይናገራሉ። የኮንጎ ወታደራዊ ኃይል እና የM23 አማፅያን በምስራቃዊ ኮንጎ ለደረሰዉ ከፍተኛ ጥፋትና ምስቅልቅል አንዳቸዉ ሌላኛቸዉን ይከሳሉ። በቡናጋና፣ ሙቡዚያና ሩንዮኒ ወደተባሉ በብዛት የሚገኙባቸዉ አካባቢዎች ላይ ባለፈዉ ረቡዕ ከፍተኛ ጥቃት ከተጣለ በኋላ አማጽያኑ ወደ ዩጋንዳ ድንበር ማፈግፈጋቸዉ ተነግሮአል። በተፈጠረዉ ከፍተኛ ዉጥረት አካባቢዉን ለቀዉ ከሸሹት ነዋሪዎች አንዱ፤«ቦታዉን ለቀን ሸሽተናል። የመጣነዉ ከተራራዉ አካባቢ ነዉ። ለልጆቻችን የሚበላም ሆነ የሚለበር ነገር የለንም። ልጆቻችን በረሃብ ያልቃሉ።»
በዴሞክራቲክ ኮንጎ የሚንቀሳቀሱት አማፅያን፤ ከኮንጎ መንግስት ጋር የተቋረጠዉን ድርድር ለመቀጠል፤ ትናንት የተኩስ አቁም እንዲደረግ መጠየቃቸዉ የሃሰት እርምጃ ነዉ ሲል የኮንጎ መንግስት ዉድቅ አድርጓል። ዩጋንዳ ዋና ከተማ ካንፓላ ላይ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክና በM-23 አማጽያን መካከል ዕርቅ እንዲወርድ በሚካሄደዉ ሽምግልና ከሚሳተፉት የአማፅያኑ ወገን የሆኑት ቤትራንድ ቢስማዋ በጠላትነት የመተያየቱ እርምጃ በአስቸኳይ እንዲቆም እንዲያደርግ የዩጋንዳን መንግስት


ጠይቀዋል። ካንፓላ በተደጋጋሚ ሁለቱ የኮንጎ ተቀናቃኝ ኃይሎች የሰላም ድርድር የተካሄደበት ቦታ ቢሆንም መቋጫ ባጣዉ ጦርነትና ግጭት፤ የተጀመረዉ የዕርቅ ድርድር እስከ ዛሬ ፈር አለመያዙ እየታየ ነዉ። በሌላ በኩል ግን በሰሜናዊ ኪቩ አዉራጃ የመረጃ ሚንስትር ማሪየ ሻምሲ ከአማጽያኑ ጎን የተሰለፉ ዜጎችን ወደቤታቸዉ እንዲመለሱ ጠይቀዋል።
«አማጽያኑን የተቀላቀሉትን ወንድሞቻችንን ወደቤታቸዉ ተመልሰዉ እንዲመጡ እጠይቃለሁ። ተታለዉ ሄደዉ ነበር ግን አሁን ወደቤታቸዉ ተመልሰዉ መግባት ይችላሉ። ከዚህ በተጨማሪ እየተጠቋቆምን ይሄ የ M23 አማጺ አባል ነበርም አንባባል። እርስ በርስ እንዋደድ፤ ሁላችንም የኮንጎ ተወላጆች ነን፤ ሀገራችንን እንገንባ።»
የተባበሩት መንግሥታትና የተለያዩ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች፤ M-23 አማጽያን በሲቭሉ ህዝብ ላይ የጭካኔ ተግባር ፈጽመዋል አስግድዶ መድፈርና የመሳሰለውን አካሂደዋል፤ በ 10 ሺ የሚቆጠር ህዝብም ከቀየው እንዲፈናቀል ሰበብ ሆነዋል ሲሉ በተደጋጋሚ ወቅሰዋል።

አዜብ ታደሰ

ሸዋዪ ለገሰ

Audios and videos on the topic