በኮንጎ  በ2 ቀናት ብቻ ከ500 በላይ ሰዎች ተገድለዋል ተባለ | አፍሪቃ | DW | 16.03.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

በኮንጎ  በ2 ቀናት ብቻ ከ500 በላይ ሰዎች ተገድለዋል ተባለ

በዲሞክራቲክ ሪተብሊክ ኮንጎ  ባለፈዉ ዓመት ታህሳስ ወር በተቀሰቀሰ የጎሳዎች ግጭት በ2 ቀናት ብቻ ከ500 በላይ ሰዎች መገደላቸዉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰሙኑን ገልጿል። ዕልቂቱን በሰዉ ልጆች የተፈፀመ ወንጀል ነዉም ብሎታል። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:28

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት  ሰሙኑን ባወጣዉ ዘገባ


የተባበሩት መንግስታት ድርጅት  ሰሙኑን ባወጣዉ ዘገባ እንዳመለከተዉ በዲሞክራቲክ ኮንጎ ምዕራባዊ አቅጣጫ አራት ቦታዎች ባለፈዉ ዓመት ከታህሳስ 16 እስከ 18 ባሉት ቀናት በጎሳ መሪዎች የታቀደ የርስበርስ ጥቃትና ዕልቂት መፈፀሙን አጣርቷል። ይህ ዕልቂት በሰዉ ልጆች ላይ የተፈፀመ ወንጀል ነዉ ሲልም ድርጅቱ ገልጿል። የድርጅቱ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሀላፊ ሚሸል ባችሌት እንደገለፁት ግጭቱ ከተቀሰቀሰባቸዉ አራት ቦታዎች ዉስጥ በሶስቱ ድርጅቱ ማጣራት አድርጓል።በዚህም በጥቃቱ ከ500 በላይ ሰዎች መገደላቸዉን አረጋግጧል። 
«በዩንምቢ ከተማ  ዉስጥ፣ ቦንጌንዴ እና እንኮሎ  መንደሮች  ቢያንስ 535 ወንዶች ፤ሴቶችና ህፃናት መገደላቸውን እና ሌሎች  111 ሰዎች ደግሞ መጎዳታቸውን ማረጋገጥ ችለናል።  ይህ አሃዝ ዝቅተኛ  ነዉ። የተወሰኑ አስከሬኖች ወደ ኮንጎ ወንዝ በመወርወራቸው የሟቾች ቁጥር ከዚህ በላይ ሊጨምር ይችላል ተብሎ ይታመናል። 
የድርጅቱ  የምርመራ ቡድን «ናባናዚ» በተባለዉ ቦታ ማጣራት ያላደረገ በመሆኑ የሟቾችና የጠፉ ሰዎች ቁጥር ሊያሻቅብ ይችላል የሚል ግምት መኖሩንም ሃላፊዋ አመልክተዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዲሞክራቲክ ኮንጎ የሰብዓዊ መብት ቢሮ በበኩሉ ከታማኝ ምንጮች አገኜሁት ባለዉ መረጃ መሰረት  በባኑኑና ባቲንዲ ጎሳዎች መካከል በተደረገ የተኩስ ልዉዉጥ ከ900 በላይ ሰዎች መሞታቸዉን ገልጿል።
እንደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዘገባ ማጣራቱ በተደረገባቸዉ ቦታዎች 50 የጅምላ መቃብሮች ተገኝተዋል።ግድያዉ ለማምለጥ  ጊዜ በማይሰጥ ሁኔታ በፍጥነት የተካሄደና ዘግንኝ እንደነበርም በሪፖርቱ በዝርዝር መቀመጡን ሃላፊዋ ገልፀዋል።


«ዘገባው የሁለት አመት ልጅ ወደ ፍሳሽ ማጠራቀሚያ መወርወርን፤  አንዲት እናት ልጇ አንገቱ ከተቀላ ባለቤቷም ከተገደለ በኋላ በአስከፊ ኹኔታ መደፈሯን ጨምሮ የተፈጸሙ አሰቃቂ ጥቃቶችን ሰንዷል። በአንዳንድ ኹኔታዎች የዐይን እማኞች የኮንጎን ወንዝ ለማቋረጥ ሲሞክሩ በርካቶች መገደላቸውን ሌሎች ከነ ሕይወታቸው መቃጠላቸውን ገልጸዋል። ከቃጠሎዉ በህይወት የተረፉትም ከፍተኛ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል»
በጎሳዎቹ መካከል ዕርቅ ለማዉረድ በድርጊቱ የሚጠየቅ አካል መኖር አለበት  ብለዋል። ግጭቱ በተቀሰቀሰበት አካባቢ የሚገኙ የመንግስት ባለስልጣናትም ህዝቡን ከአደጋ መከላከል ባለመቻላቸዉ ተወቃሾች መሆናቸውን ተናግረዋል።
«ኹከቱ የተቀነባበረዉ ጥቃቱን የሚከላከል የመንግስት እርምጃ በሌለበት ነው። አካባቢያዊ ባለሥልጣናት የሕዝቡን ደሕንነት የመጠበቅ ኃላፊነታቸውን ሳይወጡ ቀርተዋል። በወቅቱ ውጥረቶች እየጨመሩ መሔዳቸውን የሚጠቁሙ ምልክቶች ቢኖሩም እና የኹከት ሥጋት ቢያይልም ከጥቃቶቹ በፊት የጸጥታ ኹኔታውን ለማጠናከር እርምጃ አልተወሰደም። ዘገባው በተለይ ኹከት ሊያገረሽ እንደሚችል ያስጠነቅቃል።
ባለፈዉ ታህሳስ በኮንጎ የተቀሰቀሰዉ ግጭት መነሻዉ  የአንድ ጎሳ  አባላት በሌላኛውን የጎሳ መሪ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ሞክረዋል በሚል ሲሆን፤በግጭቱ 19 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ከቤት ንብረታቸዉ ተፈናቅለዋል። 16 ሺህ ሰዎች ደግሞ ከሀገር መሰደዳቸዉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዘገባ ያመለከታል።

ፀሀይ ጫኔ 

እሸቴ በቀለ

 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች