በኮንጎዉ አማፂ የICC ዉሳኔ | ዓለም | DW | 14.03.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

በኮንጎዉ አማፂ የICC ዉሳኔ

ዓለም ዓቀፉ የጦር ወንጀል ችሎት (ICC)የኮንጎዉ የአማፅያን መሪ ቶማስ ሉባንጋ ልጆችን ለጦርነት በማሰለፍ ክስ ጥፋተኛ ናቸዉ ሲል በየነ። የክስ ዉሳኔዉ እንዳመለከተዉ ሉባንጋ እድሜያቸዉ ከአስራ አምስት ያልበለጠ ሴትና ወንድ ታዳጊዎችን፤

default

ቶማስ ሉባንጋ

የግል ጠባቂዎቻቸዉ በማድረግ አሰልፈዋል፤ በሰሜናዊዉ የሐገሪቱ ግዛትም አሰቃቂ ግጭትም አሳትፈዋል። ተከሳሹ በቀጣይም የእድሜ ልክ እስራት ብይን ሊጠብቸዉ እንደሚችል ተነግሯል። ዓለም ዓቀፉ የወንጀል ችሎትም በጦር ወንጀለኝነት በተከሰሰ ግለሰብ ላይ የጥፋተኝነት ዉሳኔ ሲያሳልፍ የኮንጎዉ አማፂ ቡድን መሪ የመጀመሪያዉ እንደሆኑ ዘገባዎች አመልክተዋል።

በፍልስፍና ዲግሪ እንዳላቸዉ ይነገራል፤ አነሳሳቸዉ ነጋዴና የጎሳ መሪ ነበሩ። በኮንጎ አርበኞች ኅብረት የጦር አዛዥነታቸዉ ከተቆጣጠሩት አካባቢ ኅብረተሰቡን ከብትና ገንዘብ እንዲሁም ልጆቹን እያዋጣ ሚሊሺያዉን ታጣቂ ቡድናቸዉን እንዲያጠናክር ሲያስገድዱ ኖረዋል። የ51ዓመቱ ቶማስ ሉባንጋ በወርቅ ማዕድን የበለፀገ መሆኑ በሚነገርለት የዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ ግዛት ከአዉሮጳዉያኑ 2001 እስከ 2003ዓ,ም ድረስ በዘለቀዉ ጦርነት በነበራቸዉ ሚና ተጠያቂ ተብለዋል። በዚህ ወቅትም እድሜያቸዉ ከአስራ አምስት ዓመት በታች የሆኑ ሴት እና ወንድ ልጆችን በማስገደድ ከግል ጠባቂነት አንስተዉ የኮንጎ አርበኞች ኅብረት ከተሰኘዉ ቡድናቸዉ ጎን በማደራጀት በግጭቱ እስከመማገድ በማሰለፍ ተወንጅለዋል። ዝርዝር ክሳቸዉ እንደሚተነትነዉም ተዋጊ ቡድናቸዉን ለማጠናከር ከየትምህርት ቤቱ፤ ከየጎዳናዉና ከየኳስ ሜዳዉ ለጋ ሕፃናትን እየጠለፉ በመዉሰድ በጦርነት ከመማገድ ሌላ ለወሲብ ባርነትም ዳርገዋል። ሕፃናቱ ላይ የሚፈፀመዉ ጥቃት ዓለም ዓቀፍ ትኩረትን ስቦም በአዉሮጳዉያኑ 2006ዓ,ም ወደዓለም ዓቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ችሎት የተላለፉት ሉባንጋ ከሶስት ዓመታት በኋላ ክስ ተመሠረተባቸዉ።

JAHRESRÜCKBLICK 2003 JUNI KONGO

ከዓለም ዓቀፉ ችሎት ፊት ቀርበዉ ቃላቸዉን ከሰጡ ምስክሮች እንደተሰማዉም ለጦርነትና ለወሲብ ባርነት የተዳረጉት ሕፃናት ከዚያ ለማምለጥ ከሞከሩ ህይወታቸዉን እስከማጣት  ቅጣት ይፈፀምባቸዋል። ራሱም በአንድ ወቅት የዚህ አማፂ ቡድን ባልደረባ የነበር ምስክር «በቅጣት ስም የተገደለ ሰዉ ያየህበት አጋጣሚ እንዳለ» ተጠይቆ፤ «አንድ ታዳጊ ወንድ ልጅ ለማምለጥ ሞክሮ ሲገደል ማየቱን፤ ከወታደራዊዉ ዘመቻ ለመዉጣት የሚፈልግ የትኛዉም ልጅ እጣ ፈንታዉ ያ እንደሆነ ለማሳየት አማፅያኑ ያንን በግላጭ እንደሚያደርጉት ገልጿል።

የወቅቱ የICC ዋና አቃቤ ሕግ ሉዊስ ሞሬኖ ኦካምፖ ጉዳዩን ወደዓለም ዓቀፉ ችሎት ያደረሰዉ ከምንም በላይ ህፃናቱ ላይ የተፈፀመዉ በደልና ከታጣቂ አማፅያኑ ጋ በግጭት ተሰልፈዉ ሳሉ ይወሰድባቸዉ የነበረዉ ቅጣት እንደሆነ ነዉ ያመለከቱት፤

«ዋናዉ ጉዳይ ለእኔ ቅጣቱ ነዉ። ሉባንጋ ላይ የሚቀርቡት ሌሎች ክሶች ቢኖሩም በተለየ ምክንያት እንዲህ ላለዉ ወንጀል የሚሰጠዉን ይህን ቅጣት መርጠናል፤ ምክንያቱም ልጆቻችን ገዳዮች እንዲሆኑ የሚደረግ ከሆነ የወደፊት ተስፋ የለም ማለት ነዉ።»

ዛሬ ኔዘርላንድስ ሄግ የዋለዉ ችሎት ዳኛዉ አድሪያን ፉልፎርድ ክሱ በበቂ ማስረጃ መረጋገጡን ጠቅሰዉ የጥፋተኝነት ዉሳኔዉን አሰምተዋል።

Flash-Galerie Internationaler Strafgerichtshof in Den Haag ICC

«ችሎቱ በአንድ ድምፅ ዉሳኔ ላይ ደርሷል፤ ችሎቱ ክሱ ካለአንዳች ጥርጥር መረጋገጡን ወስኗል። አቶ ቶማስ ሉባንጋ ዳይላ ከ15ዓመት በታች የሆኑ ልጆችን በኮንጎ አርበኞች ኅብረት አስገድዶ በመመልመል፤ በግጭቶች እንዲሳተፉ በማድረግ ክስ ጥፋተኛ ሆነዉ ተገኝተዋል።»

ከዚህ በፊት በተከሰሱበት ጉዳይ ጥፋተኛ እንዳይደሉ የተናገሩ ቶማስ ሉባንጋ በዳኛዉ የጥፋተኝነታቸዉ ዉሳኔ ሲተላለፍ ተቀምጠዉ ቢያደምጡም ያደመጡት ያሳዩት ሆነ የተናገሩት ነገር አልነበረም። በጠባቂዎች ተከበዉ ከችሎቱ ሲወጡ ግን ጉዳዩን ይከታተሉ ለነበሩ ደጋፊዎቻቸዉ በፈገግታ ምልክት ሲሰጡ ታይተዋል። የመጨረሻዉ የቅጣት ዉሳኔ የሚሰጥበት ጊዜ የሚቀጠር ሲሆን ሉባንጋ ምናልባትም ከፍተኛዉን የእድሜ ልክ እስራት ሊበየንባቸዉ እንደሚችል ተገምቷል። የችሎቱን ዉሳኔ ያወደሱት የመብት ተሟጋቾች ሌሎች ተመሳሳይ ወንጀል ለሚፈፅሙ ቡድኖችም ግሩም መልዕክት ነዉ ብለዉታል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ