በኮሚሽኖቹ ‘የፓንዶራ ሙዳይ’ ቢከፈትስ? | ኢትዮጵያ | DW | 08.02.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

በኮሚሽኖቹ ‘የፓንዶራ ሙዳይ’ ቢከፈትስ?

የፓንዶራ ሙዳይ አንዴ ሲከፈት ከውስጡ ታፍነው የነበሩ ወረርሽኞች፣ የሞት መንፈስ እና ሌሎችም ችግሮች የሚወጡበት ነው። አባባሉ መደረግ የሌለባቸው ነገሮች ሲደረጉ የሚመጣውን ጣጣ ለማመልከት ይውላል።የኮሚሽኖቹ መቋቋምና እና ወደ ሥራ መግባት አሁን ያለውን ‘የሽግግር ፖለቲካ’ የሚመጥን አይደለም፤ የኢትዮጵያን የፓንዶራ ሙዳይ እንዳይከፍተው ያስፈራል።

በቅርቡ የተቋቋሙት ኹለት ኮሚሽኖች በዚህ ሳምንት መባቻ እያንዳንዳቸው 41 ቋሚ ኮሚቴ ተሠይመውላቸዋል። ኮሚሽኖቹ የዕርቀ ሠላም እንዲሁም የአስተዳደር ወሰንና ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ናቸው። የኮሚሽኖቹ ዕድሜ ሦስት ሦስት ዓመታት ነው። ኮሚሽኖቹ ካሁኑ ማወዛገብ ጀምረዋል። ሥራቸውን ሲጀምሩ ደግሞ የበለጠ ጣጣ ያመጡ ይሆን በሚል እንድንሰጋ የሚያደርጉን ቢያንስ ሦስት ምክንያቶች አሉ። ይኸውም የገጠማቸው ተቃውሞ፣ የሚያነሱት ጉዳይ ስሱነት እና የወቅቱ አስቸጋሪነት ናቸው።

የሥጋቶቹ ምንነት

የዕርቀ ሠላሙ ኮሚሽን ከአስተዳደር ወሰንና ማንነት ኮሚሽኑ አንፃር ሲታይ ይህ ነው የሚባል ትችት አልተሰነዘረበትም፤ ምክንያቱ ደግሞ ወቅቱ ‘የሽግግር’ እንደመሆኑ፥ ‘የሽግግር ጊዜ ፍትሕ’ ለመስጠት የተቋቋመ ነው ተብሎ በመታሰቡ ይመስለኛል። ይሁን እንጂ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ድረገጽ የታተመው የዕርቀ ሠላሙ ኮሚሽን ረቂቅ እና የረቂቁ መግለጫ እንደሚያመለክቱት ዕርቁ ከለውጡ በፊት በነበሩት ጥቂት ዓመታት ለተሠሩ ወንጀሎች እና በደሎች በበዳይ እና ተበዳይ መካከል አይወሰንም። ይልቁንም ኢሕአዴግ ከዚህ በፊት “የተጣላ ሕዝብ የለም” በሚል አያስፈልግም ሲል የነበረውን ብሔራዊ ዕርቅ፣ ‘አንዱ በሌላው ላይ ቂም ቋጥሯል’ በሚል ብሔራዊ ዕርቅ መሰል ነገር እንደሚሞክር ይናገራል። ይህ ኮሚሽን ከሽግግሩ ወቅት ምንነት አንፃርም ቢሆን በጣም የተለጠጠ ዓላማ የያዘ ነው።

የሽግግሩ ሁኔታ በግልጽ እንደሚታየው በኢሕአደግ ማዕቀፍ ውስጥ እና ባለው ሕገ መንግሥት ሥር ነው። ስለሆነም የሚመለከተው ጉዳይ ከዚያ በፊት የነበሩትን የፖለቲካ ተቃርኖዎች ወደማስታረቅ መዝለቅ አይገባውም። የብሔራዊ ዕርቅን ጉዳይ መሞከር አሁን ያለውን ብሔርተኝነት አጋግሎ ቡድንተኝነት ሊያባብሰው ይችላል። ከዚያም በላይ የቀድሞዎቹን የፖለቲካ ሥራዎች በአሁኑ የብሔርተኝነት ድባብ ለመዳኘትም ይሁን ለማስታረቅ አይቻልም።

ከዚሁ የራቀ ዓላማ ያለው የማይመስለው የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ኮሚሽንም ከወዲሁ በትግራይ ክልል እና በፌዴራል መንግሥቱ መካከል ያለውን ኩርፊያ ተቋማዊ አድርጎታል። በመቀጠልም ቀድሞ በውሃ እና የግጦሽ መሬት ግጭት ውስጥ ሲገቡ የነበሩ ድንበርተኛ ሕዝቦች፣ አሁን በብሔርተኛ ፖለቲከኞች እየታገዙ ግጭታቸው ተባብሷል። ለነዚህ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ መፈለግ የግድ ነው። ነገር ግን መፍትሔ ለመስጠት ቅቡልነት ያለው፣ በፍትሐዊና ርትዓዊ ምርጫ የተሰየመ ምክር ቤት እና መንግሥት በቅድሚያ መቋቋም ነበረባቸው። አሁን እንደ ሽግግር መንግሥት እየታየ ያለው መንግሥት ሥራውን ማስጀመሩ በራሱ የቅቡልነት (‘ሌጂቲሜሲ’) ችግር ፈጣሪ ነው።

ኢትዮጵያ በመጪው ዓመት ምርጫ ታስተናግዳለች ተብሎ ይጠበቃል። ምርጫው ግጭት ሊያስከትል ይችላል በሚል ከወዲሁ ፍርሐት ነግሧል። በዚያ ላይ የብሔራዊ ዕርቅ እና የአስተዳደር ወሰን ሥራ ለመሥራት መሞከር በቅድመ ምርጫው ሒደት ላይ ተጨማሪ የውዝግብ መንስዔ እንደማርከፍከፍ ነው። በዚያ ላይ የኮሚሽኖቹ ሥራ ከምርጫው በፊት ተጀምሮ ከምርጫው በኋላ ነው ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው።

 

‘የፓንዶራ ሙዳይ’ መከፈት

በግሪክ ተረት ውስጥ ‘የፓንዶራ ሙዳይ’ በመባል የሚታወቅ አለ። የፓንዶራ ሙዳይ አንዴ ሲከፈት ከውስጡ ታፍነው የነበሩ ወረርሽኞች፣ የሞት መንፈስ እና ሌሎችም ችግሮች ፈንድተው የሚወጡበት ነው። አባባሉ አሁንም በዓለማችን መደረግ የሌለባቸው ነገሮች ሲደረጉ የሚመጣውን ጣጣ ለማመልከት ይውላል። እናም የኮሚሽኖቹ መቋቋምና እና ወደ ሥራ መግባት አሁን ያለውን ‘የሽግግር ፖለቲካ’ የሚመጥን አይደለም፤ የኢትዮጵያን የፓንዶራ ሙዳይ እንዳይከፍተው ያስፈራል። የሽግግር ጊዜው ዋና ሥራ መሆን የነበረበት ባለፉት ዓመታት አገሪቱ ገብታበት የነበረውን የአመፅ ስሜት ማረጋጋት እና ሰላም አስፍኖ ለምርጫ መዘጋጀት ነበር። ተጨማሪ፣ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ የተመረጠ መንግሥት ሊሠራቸው የሚደፍራቸውን አገር ዐቀፍ ሥምምነት የሚጠይቁ ሥራዎችን መሞከር በእሳት ለመጫወት እንደመሞከር ሊሆን ይችላል።

የኮሚሽኖቹ ቋሚ ኮሚቴዎች በምክር ቤት ሲሾሙ፣ ምንም እንኳን ሰዎች በኅብረተሰቡ ውስጥ የተሻለ ተቀባይነት አላቸው ተብለው የሚታሰቡ ቢሆንም፥ ጥቂት የማይባሉት በቅድሚያ አልተማከርንም የሚል ቅሬታ አሰምተዋል። ይህ ድርጊት ባለው ክፍተት ላይ ተጨማሪ ሊሆን ይችላል። ለቋሚ ኮሚቴው ተቀባይነቱ ያላቸው፣ ፈቃደኛ የሆኑ እና ሥራውን የመከወን አቅሙ ያላቸው ሰዎች ቢሾሙ ምናልባት የተሻለ ውጤት መጠበቅ ይቻል ነበር።

አሁን ያለው አማራጭ የጉዳዩን ስሱነት በመረዳት ሙዳዩን በሚገባው ከፍተኛ ጥንቃቄ ለመክፈት መሞከር ብቻ ነው።

በፍቃዱ ኃይሉ

በዚህ አምድ የቀረበው አስተያየት የጸሐፊው እንጂ የ«DW»ን አቋም አያንጸባርቅም።