በኬንያ የተከሰተዉ ድርቅና አርብቶ አደሩ | አፍሪቃ | DW | 26.01.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

በኬንያ የተከሰተዉ ድርቅና አርብቶ አደሩ

በኬንያ እንደ አዲስ በተከሰተዉ ድርቅ ሳቢያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አርብቶ አደሮች ለረሃብ አደጋ መጋለጣቸዉ ተገለፀ። በኬንያ ሁለት የዝናብ ወራቶች ባጋጠመ የዝናብ እጥረት ሳቢያ የተከሰተዉን የረሃብ አደጋ ለመቀነስ የኬንያ ቀይ መስቀል ለየት ያለ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ መርሃ-ግብር መዘርጋቱን ገልጿአል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:04

ድርቅ በኬንያ

ኤል ሊኖ በተባለዉ የአየር ንብረት መዛባት ሳቢያ የምስራቅ አፍሪቃ  ሀገራት ለላለፉት ሦስት ዓመታት በድርቅ እየተጠቁ ይገኛሉ። በዚሁ የአየር ንብረት መዛባት ምክንያት በድርቅ ከተጎዱ የቀጠናዉ ሃገራት መካከል ኬንያ አንዷ ናት። በሀገሪቱ የበልግና  የመኸር ወቅት ዝናብ መዘግየትና ስርጭቱ በቂ አለመሆን ህይወታቸዉ ከግጦሽ መሬትና ከዉሃ ጋር ለተቆራኘዉ የሰሜን ኬንያ አርብቶ አደሮች ፈተና እየሆነ እንደመጣ ዘገባወች ያመለክታሉ።
 ለአርብቶ አደሮቹና ለከብቶቻቸዉ ወሳኝ የተባለዉ ከመጋቢት እስከ ግንቦት ያለዉ የዝናብ ወቅት በመስተጓጎሉም በአሁኑ ወቅት በርካታ የሀገሪቱ አርብቶ አደሮች ለአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ተጋልጠዋል ሲል የኬንያ ቀይ መስቀል ገልጿል። አርብቶ አደሮቹ  ከብቶቻቸዉን በመሸጥ ችግሩን ለመቋቋም  ቢሞክሩም   የረሃብ አደጋዉን ግን መቆም እንዳልቻሉ ከኬንያ ቀይ መስቀል ለይላ ቸፒኬምቦይ ይናገራሉ።

«ስለ አርብቶ አደሮች የገቢ ሁኔታ ስናወራ ከብቶቻቸዉን በመሸጥ ገቢ ለማግኘት ይሞክራሉ ።ነገር ግን እየሞቱ ነዉ ቤት ዉስጥ ምግብ የለም ፣ለልጆቻቸዉ የሚሰጧቸዉ ወተትም የለም።ያሉበት ሁኔታ በጣም የከፋ ነዉ።»
በእነዚህ አካባቢወች ካለፈዉ ሚያዚያ ወር ጀምሮ  ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ ኬንያዉያን በአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ላይ ናቸዉ ። ከ 4 ህጻናት አንዱም በከፋ የምግብ እጥረት ይጠቃል  ተብሏል።  

ችግሩን የተገነዘበዉ የኬንያ ቀይ መስቀል ታዲያ አብዛኛወቹ አርብቶ አደሮች በሚገኙበት  በታና  ወንዝ ደለል  አካባቢ ለየት ያለ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ጀምሯል። የእርዳታ መርሃ-ግብሩ ከተለመደዉ የምግብና የቁሳቁስ አቅርቦት ወጥቶ የአርብቶ አደሮቹን ከብቶች ገበያ ላይ ሊሸጡ ከሚችሉበት ዋጋ ጨምሮ ይገዛል። እንስሳቱን ለእርድ በማቅረብም ለምግብነት የሚዉል ስጋ ለአርብቶ አደሮቹ በነጻ ያከፋፍላል።
የኬንያ ቀይመስቀል  ሰራተኛ ሀሰን ሙሳ እንደሚሉት ይህን መሰሉ እርዳታ ለአርብቶ አደሮቹ ገንዘብ እንዲያገኙ ለማድረግ ጠቀሜታዉ የላቀ ነዉ።

«ሃሳባችን ምግብ መስጠት አይደለም።የተነሳሳነዉ «አወ እናንተን መርዳት እንችላለን« ብለን ለማበረታት እና  እንደ ትምህርት ቤት ክፍያና ምግብ መግዛት የመሳሰሉ  ሌሎች ለህይወት አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች ገንዘብ እንዲያገኙ መርዳት ነዉ ፍላጎታችን።»
 የኬንያ ቀይ መስቀል በዚህ ሁኔታ እስካሁን  ሁለት ሺህ  ከብቶችን ከአርብቶ አደሮቹ የገዛ ሲሆን መርሃ ግብሩ  የእንስሳቱን ቁጥርና የሚያስፈልጋቸዉን  የዉሃ ፍጆታ ለመቀነስ ያግዛል ሲሉ ሀሰን ሙሳ ተናረግዋል።  

«ስለዚህ ለከብቶች ግጦሽና ዉሃ ፍለጋ ከመታገል ይልቅ ፤ከብቶችን በመሸጥ ቁጥራቸዉን መቀነስና ገንዘብ መያዝ።ከዚያም ዝናብ በተስተካከለ ሁኔታ ሲጀምር  ከብቶችን ገዝቶ እንደገና ህይወት መቀጠል።»
የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ መርሃግብሩ  በቀጥታ የገንዝብ ልዉዉጥ የሚካሄድ ሲሆን በመጭወቹ ሦስት ወራት ብቻ ከ6 መቶ ሺህ በላይ ዩሮ ያስፈልጋዋል ተብሏል።የኬንያ  ቀመስቀል ገንዘቡ ዉድ ቢሆንም ተግባሩ  ግን አስፈላጊና የተቀደሰ ነዉ ብሎታል።
ፀሐይ ጫኔ 
አዜብ ታደሰ
 

Audios and videos on the topic