በኬንያ ወጣቶችን የማነቃቃት እንቅስቃሴ | ወጣቶች | DW | 24.03.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ወጣቶች

በኬንያ ወጣቶችን የማነቃቃት እንቅስቃሴ

የትም ሀገር ይሁን የት ልጆች አድገው ጥሩ ደረጃ ለመድረስ አብዛኛውን ጊዜ ተወልደው የሚያድጉበት አካባቢ ትልቅ ሚና ይጫወታል። አብዛኛዉን ጊዜ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያለዉ ማኅበረሰብ በሚኖርበት ጎስቋላ መንደር የሚያድጉ ልጆች የዕለት ከዕለት ኑሮዋቸው ላይ በማተኮር ስለሚያድጉ የወደፊት ህልማቸውን ዕውን ለማድረግ ሲቸግራቸዉ ይስተዋላል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:36

በኬንያ የአምልኮ ቦታዎችን ቢጫ ቀልም የሚቀቡ ወጣቶች

ይህን ሸክማቸዉን የሚቃልልላቸው ሲገኝ ግን ሁሉም ነገር መልኩን ሊቀይር ይችላል።

የኬንያ ጎስቋላ ሰፈር

የኬንያ ጎስቋላ ሰፈር


በኬንያ ናይሮቢ  አቅራቢያ በሚገኝ አንድ ፀጉር ቤት ውስጥ ዛሬ ሁሉም የፀጉር ማድረቂያዎች በሥራ ላይ ናቸዉ። የፈተና ቀን ነው። አምስት በፀጉር ሥራ ትምህርት የሰለጠኑ ተማሪዎች ባለፉት ስድስት ወራት የተማሩት የሚፈተሽበት ቀን። መምህርት ጃኔ ሙሌ ልክ እንደተማሪዎቻቸው ውስጣቸው ያለመረጋጋት ይስተዋልበታል።«ሦስተኛው ፈተና ፀጉር መጠቅለል ነው። በመጀመሪያ ፀጉር ካጠቡ በኃላ በማድረቂያ ያደርቁ እና ይጠቀልላሉ። ከዛ ፈታኝዋ የሠሩትን በጠቅላላ ትመለከታለች።»
ፀጉር ቤቱ  የእጅ ሙያ ማሰልጠኛው ትምህርት ቤት አንድ አካል ስለሆነ ሁሉም ፈተናውን ካለፉ ሌላ ትልቅ ስኬት ነው። በኬንያ ዋና ከተማ አቅራቢያ የሚገኘው ይህ ማዕከል ከጎስቋላ ሰፈር የመጡ ልጆችን አሰልጥኖ ለተሻለ ደረጃ ሲያበቃ አሁን አራት አመት ሆኖታል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ወንድ እና ሴት ተማሪዎችን በእንጨት ሥራ፣ በኤሌክትሪክ፣ በልብስ ስፌት ወይም በፀጉር ሥራ ያሰለጥናል። ይህንን ትምህርት ቤት የመሠረቱት ጂሚ ኪሎንዚ አብዛኛውን ጊዜ ወደዚህ መጥተው የተማሩት ከዚህ በፊት ምንም እድል ያላገኙ ወይም ተስፋ አጥተዉ የነበሩ ወጣቶች እንደሆኑ ይገልፃሉ። « አብዛኛውን ጊዜ ልጆች ሕጻናት መዋያ፣ መለስተኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ይሄዳሉ። ከዛ  በኋላ እንዴት ብለው የወደፊት መተዳደሪያቸውን እንደሚያገኙ ግን የሚያውቁት ነገር የለም። »

አንድ የኬንያ ጎስቋላ ሰፈር ትምህርት ቤት

አንድ የኬንያ ጎስቋላ ሰፈር ትምህርት ቤት


ኪሎንዚ፤ ማታሬ በተባለው የኬንያ ጓስቋላ መንደር ለረዥም አመታት በማህበራዊ ኑሮ ባለሙያነት አገልግለዋል። የ 20 ዓመቱ ወጣት ስታንለይምን ጨምሮ አብዛኞቹ ተማሪዎችም ከዚህ አካባቢ ነው የመጡት።«አባታችንም ምንም አይረዳንም ነበር። እናታችን ነበረች ሁል ጊዜ በልተን እንድናድር ትታገል የነበረው። በቃ ይህ ህይወት ማለት ነበር !»
ወጣቱ ወደፊት የኤሌክትሪክ ባለሙያ ለመሆን የኮረንቲ ገመድ የሚገባበት ቀጣዳ እንዴት እንደሚቦረቦር እየተማረ ነው። ተማሪዎቹ በእጅ ሙያ ማሰልጠኛው ትምህርት ቤት ለስድስት ወራት ከሰለጠኑ በኋላ ለሦስት ወራት የሥራ ልምምድ እንዲያደርጉ ትምህርት ቤቱ ከመሥሪያ ቤቶች ጋር ያገናኛቸዋል። 
ትምህርት ቤቱ እኢአ በ2012 ዓም ከተከፈተ አንስቶ  300 የሚጠጉ ተማሪዎች በተለያዩ የሙያ መስኮች አስመርቋል። ደቡብ ጀርመን የሚገኝ አንድ ፕሮሞቲንግ አፍሪቃ የተባለ ማህበር ነው እስካሁን ለትምህርት ቤቱ ድጋፍ የሚያደርገው። አላማው ወደፊት ተማፊዎቹ የሠሯቸውን ቁሳቁሶች በመሸጥ ትምህርት ቤቱ ራሱን ችሎ ወጪውን እንዲሸፍን ነው። ሌላው አማራጭ ደግሞ ክፍያ ነው። ተማሪዎች ለግማሽ አመት ለስልጠናው እና ለመኖሪያ ክፍላቸው 7500 ብር ገደማ መክፈል ይጠበቅባቸዋል።  ይህንን ገንዘብ ግን አብዛኞቹ መክፈል ስለማይችሉ እዛው ሠርተው ገንዘቡን ለማካካስ ይሞክራሉ።« የግድ በጥሬው መክፈል አይጠበቅባቸውም። እዚሁ ግቢ ውስጥ ለምሳሌ በጽዳት፣ ሳር በማጨድ ወይም አትክልት በመትከል ሊያገለግሉ ይችላሉ።»
ይላሉ የትምህርት ቤቱ መሥራች። በዚህም አጋጣሚ ወጣቶቹ ለወደፊት ህይወታቸው የሚጠቅማቸው ትምህርት አግኝተዋል። ወደፊት የኤሌክትሪክ ባለሙያ ለመሆን ስልጠናውን በማጠናቀቅ ላይ ያለው ስታንለይምን መጪውን ጊዜ በቀና ነው የሚጠብቀው።« እዚህ የቀሰምኳቸው ትምህርቶች ወደፊት ብዙ ያራምዱኛል። በፊት ወደ ትምህርት ቤት ስሄድ የሆነ ቦታ እደርሳለሁ ብዬ በፍፁም አስቤው አላውቅም። አሁን ግን መጪው ጊዜ ፈካ ብሎ ነው የሚታየኝ።»
የወጣቱ ተስፋ ምክንያት አለው። ከእሱ በፊት ስልጠናውን የወሰዱት የኤሌክትሪክ ባለሙያዎች በሙሉ አሁን ከፀሀይ የሚገኝ ታዳሽ ኃይል ለሚያመርት አንድ መሥሪያ ቤት ተቀጥረው እና ከጎስቋላ ህይወታቸው ተላቀዋል። 


ቢጫዎቹ የኬንያ መስጊዶች እና ቤተ ክርስትያኖች

ቢጫ የተቀቡት የአምልኮ ቦታዎች

ቢጫ የተቀቡት የአምልኮ ቦታዎች


ኬንያ ውስጥ 47 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ይኖራሉ። ከነዚህም ውስጥ 80 በመቶ ያክሉ የክርስትና፤ 10 በመቶዉ ደግሞ የእስልምና እምነት ተከታዮች ናቸው። የሁለቱም እምነት ተከታዮች ተቻችለው ቢኖሩም ጎረቤት ሀገር ያለው ፅንፈኛዉ አሸባሪ ቡድን አሸባብ ኬንያ ላይ አልፎ አልፎ ጥቃት በጣለ ቁጥር በእምነት ተከታዮቹ መካከል መራራቅ ይስተዋላል። ነገር ግን ይህ ክፍተት እንዳይጠነክር በቅርቡ አንድ ፕሮጀክት ተጀምሯል ትላለች፤ በስፍራው ተገኝታ የተመለከተችዉ ጋዜጠኛ አንቲ ዲክሀንስ፤
በጅዳ መስጊድ በርካታ ወንዶች ለፀሎት ተሰብስበዋል። መስጊዱ ናይሮቢ ከሚገኙ መስጊዶች አንዱ እና ታዋቂው ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መስጊዱ ፈካ ብሎ እና ጎልቶ ይታያል። ይህም ከግድግዳ እስከ ጣሪያው በደማቅ ቢጫ ቀለም በመቀባቱ ነው። ሙስሊም እና ክርስትያን ወጣቶች ናቸው አንድ ላይ ሆነው  ቀለሙን የቀቡት ይላል ከቀቢዎቹ አንዱ የሆነው ቪንሰት አያኮ፤
ልክ እንደ መስጊዱ ትንሽ መቶ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ አንድ ቤተ ክርስትያንም ቢጫ ቀብተዋል። ኪቤራ በተባለው ጎስቋላ ሰፈር ሙስሊምም ይሁኑ ክርስትያኖች ቅርብ ለቅርብ ነው የሚኖሩት።«ሰዎች እርስ በርሳቸው አይዋደዱም» ይላሉ ቄስ አልበርት ዋሬሻህ። «ይህንን ነው ልጆቻቸውም የሚማሩት፤»


በተለይ አለመዋደዱ የሚጠነክረው አሸባብ ኬንያ ላይ ጥቃት በሚሰነዝር ጊዜ ነው። ቡድኑ ከሶስት ዓመት በፊት በአንድ የገበያ አዳራሽ ላይ ጥቃት ፈጽሟል። በከፍተኛ የትምህርት ተቋም እና አውቶቢስ ላይም የቦምብ ፍንዳታ አድርሷል። እንደዚህ አይነት ጥቃቶች ሲከሰቱ ሙስሊሞች ወደ ጎን ይባላሉ ይላሉ የጅዳ መስጊድ ሼህ ዩሱፍ ናሱር፤« በጣም አስከፊ ሁኔታ ነበር። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ክርስቲያኖች በመላው ኬንያ ሙስሊሞችን ይፈሩ ጀመር። የእስልምና ጥላቻ ማለት ይቻላል።»
መስጊዶች እና ቤተ ክርስቲያኖችን ቢጫ የመቀባቱ አላማ ይህንን ፍርሀት እና አለመግባባት ለማስቀረት እንዲረዳ ታልሞ ነው።  „Colour in Faith“ ብለውታል ። ለመተማመን ምልዕክት ነው ያሉት ቀለም። ከአስተባባሪዎቹ አንዷ ናቢላ አሊባሂ ለምን ቢጫ ቀለም እንደመረጡ ታስረዳለች።« ቢጫ ተስማሚ ቀለም ነው። የብርሃን ቀለም ነው። ጭለማን የሚያጠፋ። የድሮ የቤተ ክርስቲያን ሥዕሎችን ስንመለከት መልአኮች በቢጫ ቀለም ፈክተው ይታያሉ።»
ከኪቢራ መንደር አልፎ በአንዳንድ የኬንያ የወደብ አካባቢዎችም ቢጫ መስጊዶች እና ቤተ ክርስቲያናት ይታያሉ። ከቀለም ቅቡ ይበልጥ ዋናው ነገር ግን በሁለቱ የእምነት ተከታዮች መካከል ያለው ግንኙነት ነው። የ17 ዓመቷ ሊላን በዚህ አጋጣሚ ከዚህ በፊት ያልነበሯት ብዙ ሙስሊም ጓደኞች እንዳፈራች ትናገራለች።ወጣቶቹ አንድ ላይ ሆነው ይጸልያሉ ፣ ይዝናናሉ ይጫወታሉ። የ 24 ዓመቱ ኢምራን ሌላ አንድ ምኞት አለው። 
« ይህንን በክርስቲያን እና ሙስሊሞች መካከል ብቻ ሳይሆን ከሂንዱዎች እና ቡዳዎች ጋርም ማድረግ ብንችል።» ይላል የሁሉም ኬንያውያን አንድነትን ለማመላከት። 
አንቲ ዲካንስ /ልደት አበበ
አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic