በኬሚካል ድጋፍ የተፈጥሮ ጋዝ ማምረት | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 24.07.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

በኬሚካል ድጋፍ የተፈጥሮ ጋዝ ማምረት

ማዕድን፣ በተለይም የተፈጥሮ ጋዝን ለመዛቅ፣ እንደ ዘመናዊ ዘዴ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚሠራበት ብልሃት ፣ አንድ ቦታ ላይ ፣ በጥልቅ መቆፈርና ፤ «ኬሚካል» ውሃና አሸዋ ቀላቅሎ በኃይለኛ ግፊት ፣ በከርሠ ማድር የሚገኘው ዐለት እንዲፈረካከስ በማድረግ፤ ጋዙ ወይም ማዕድኑ ወደ ላዕላዩ የየብስ ክፍል እንዲዘልቅ ማብቃት ነው።

በኢንዱስትሪ በገሠገሡት አገሮች ብቻ ሳይሆን በማደግ ላይ ባሉትም ፤ የኃይል ምንጭ ተፈላጊነት እየጨመረ ነው የመጣው። ከብዙዎቹ አንዱና ተፈላጊው የኃይል ምንጭ የተፈጥሮ ጋዝ መሆኑ የታወቀ ነው። የተፈጥሮ ጋዝ ከድንጋይ ከሰልም ከነዳጅ ዘይትም በተሻለ ሁኔታ የሚቀጣጠል መሆኑ የታወቀ ነው።

በጀርመን ፤ ሀገሪቱ ያላት የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት፤ ቀስ በቀስ እየተሟጠጠ በመሄድ ላይ ስለነበረ፤ እ ጎ አ ከ 2006 ዓም አንስቶ አውጥቶ የመጠቀሙ ተግባር 30 ከመቶ እንዲገታ ነው የተደረገው። ጀርመን ያላት የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ለ 13 ዓመታት ብቻ የሚያበቃ ነው ፣ በ 13 ዓመታት ውስጥ ተሟጦ የሚያልቅ ነው ማለት ነው። በአሁኑ ጊዜ ፤ ከሚያሻት የኅይል ምንጭ መካከልም እንግዲህ 12 ከመቶውን የሚሸፍነው ፣ በምድርዋ የሚመረተው የተፈጥሮ ጋዝ ነው። ሰላሳ ከመቶ የራሷን የጋዝ መጠን በመቀነስ ለመቆጠብ እርምጃ የወሰደችበትን ድርጊት ለማካካስ፣ የኃይል ምንጭ ኢንዱስትሪዎቿ፣ እስካሁን ባልሞከሩት ሥነ ቴክኒክ በመጠቀም የተፈጥሮን ጋዝ ጥልቀት ካለው ቦታ አውጥቶ መጠቀም ይበጃል የሚል እምነት አሳድረዋል። እርሱም በከርሰ ምድር በጥልቀት በመቆፈርና ፤ በሚሊዮን ሊትር የሚቆጠር ውሃ ፣ ኬሚካልና አሸዋ ወደ ውስጥ በመላክ በግፊት ኃይል ዐለቱ ላይ እንዲፈነዳ ማድረግ ነው።

ፍንዳታው ቀዳዳ ያለባቸውን ዐለቶች ፈረካክሶ ፣ ፈንጠር -ፈንጠር ብለው የሚገኙ ፣ ጋዝ የተከማቸባቸውን አካባቢዎች ሁሉ እንዲገናኙና ፣ ጋዙን አጠቃሎ ወደ ላይኛው የየብስ አካል በመምጠጥ ጥቅም ላይ ማዋል የሚቻልበት ዘዴ ነው በእንግሊዝኛው አጠራር Fracking የሚባለው! የተጀመረው በዩናይትድ እስቴትስ ነው። በዚህ ዘዴ በመጠቀም አሜሪካውያኑ፤ በሰፊው የተፈጥሮ ጋዝ ከከርሠ-ምድር በማውጣት ተጠቃሚዎች ሆነዋል። ይሁንና እስካሁን ዐቢይ ጥያቄ ያስነሳበት ሁኔታ መኖሩ እሙን ነው። በዚያው በዩናይትድ እስቴትስም ፣ በአውሮፓም!

«ፍራኪንግ» ምን ዓይነት አደጋ አለው? የጀርመን የቋጥኝና ዐፈር ጠበብት ፣ በአገሪቱ በዚህ ረገድ ሊያስከትል የሚችለው አደጋ አለ ፣ የለም መርምረው፤ በጥብቅ ቁጥጥር ጀርመን ጋዝ ፍለጋ ዐለት የመሠርሠሩን ተግባር ልትገፋበት እንደምትችል ፤ ፌደራሉ መንግሥት ያቀረበውም ሆነ የተስማማበት ረቂቅ ህግ ይጠቁማል።

በላይፕዚኽ ፣ የጀርመን መልክዓ ምድራዊ ማኅበር ከተለያዩ የምርምር ተቋማት ፣ ጠበብትን ሰብስቦ ቢያወያይም፤ ጠበብቱ፤ ጀርመን ውስጥ ፣ እንዲያው በደፈናው አይሞከርም ብሎ መከልከሉ አይበጅም፤ ቀስ በቀስና በጥሞና በሚካሄድ ጥናት መሠረት በተጠቀሰው ልዩ ዘዴ የተፈጥሮ ጋዝ ማውጣት የሚቻልበት ብልሃት ይኖራል ነው ያሉት። የተለያዩ አካባቢዎች ኑዋሪዎች ግን፤ የተፈጥሮ አካባቢ ተንከባካቢ ማኅበራትን አሰባስበው፤ ስነ ቴክኒኩ፤ የሚጠጣ ውሃን የሚበክል፤ የተፈጥሮ አካባቢን የሚመርዝና ሰው ሠራሽ የምድር ነውጥን የሚጋብዝ ነው በማለት ብርቱ ተቃውሞአቸውን ማሰማታቸው አልቀረም።

የውሃ ኢንጂኔሪንግ ባለሙያ፤ ማርቲን ዛውተር እንደሚሉት ከሆነ፤ ጀርመን ፣ ዩናይትድ እስቴትስ ከሠራችው ስህተት መማር ትችላለች።

በጀርመን ፣ ጥንቃቄውም ፣ ጥርጣሬውም የመኖሩን ያህል በምሥራቅ ጎረቤቷ በፖላንድ ይህ ፈጽሞ አይታይም። የፖላንድ መንግሥት፤ እ ጎ አ ከ 2010 ዓ ም አንስቶ፣ አከራካሪውን ከከርሰ ምድር ፣ በኬሚካል አጋዥነት ጋዝ እንዲወጣ የሚደረግበትን አሠራር የሙጥኝ ነው ያለው። ይህን ያደረገበት አንደኛው ምክንያት፣ የኃይል ምንጭ ጉዳይ ጥናት ባልደረባ አንድሬዥ ሲኮራ እንደሚሉት፣ አገሪቱ የአውሮፓው ኅብረት አባል በሆነችበት ጊዜ የተቃጠለ አየር (CO2) ልቀት ለመቀነስ የገባችውን ቃል ለማክበር ነው። ስለሆነም፤ በከርሠ ምድር ከዐለት ውስጥ የተፈጥሮ ጋዝ ማውጣት መቻሏን በደስታ ነው የምትመለከተው። እርግጥ ነው፤ የተፈጥሮ ጋዝ የሚገኝበት የከርሰ ምድር ዐለት ፤ ከዩናይትድ እስቴትስ ይልቅ በአውሮፓ ምድር ይበልጥ ወደ ውስጥ ጠለቀ ብሎ እንደሚገኝ ነው የተገለጠው። ስለሆነም ጋዝ ፍለጋው ብዙ የሚያደክምና ወጪም ይበልጥ የሚያስወጣ ሲሆን፤ አዲስ የመቆፈሪያ ሥነ ትክኒክም ያሻል።

ይኸው፣ በከርሠ-ምድር ጥልቅ ቁፋሮ የሚካሄድበት፤ ኬሚካል፤ ውሃና አሸዋ ተቀላቅሎ የተነጠፈ ዐለትን እንዲሠረሥር የሚደረግበትና ፤ በየቦታው የታመቀው የተፈጥሮ ጋዝ ተጠምዶ በአንድ መሥመር ወደላይ የሚወጣበትና ጠቀሜታ እንዲሰጥ የሚደረግበት ሁኔታ በአውሮፓ ሃገራት ፤ ከእስፓኝ ፤ ከብሪታንያ እስከ ቡልጌሪያ እንዳከራከረ ነው። አፍሪቃ ም ውስጥ ፤ ሜድታራንያን ባህር ዳር የምትገኘው ንዑሷ ሰሜን አፍሪቃዊት ሀገር ቱኒሲያ፣ ከባህር ሳይሆን ፣ በየብስ ከከርሰ ምድር በ«ፍራኪንግ» የተፈጥሮ ነዳጅ ዘይት ለማውጣት የቀረበ ሐሳብም ሆነ እቅድ ተቀባይነት አላገኘም።

ለምሳሌ ያህል፤ በሰሜን እስፓኝ፤ በአንዲት ንዑስ ከተማ የሚኖሩ ሰዎችየተፈጥሮ ጋዝ የሚያወጣ ትልቅ የኃይል ምንጭ ኩባንያ ቦታውን ስለሚፈልገው ፤ ይሸጡለት ዘንድ ተጠይቀው እንደነበረ ተመልክቷል።

«የካንታብሪያ ፓርላማ ፣ በሙሉ ድምፅ፣ የተፈጥሮ ጋዝ ለማውጣት፣ በውሃ ነክ ኢንጂኔሪንግ ድጋፍ፣ በከርሠ ምድር ዐለት የሚፈረካከሥበትን ድርጊት(Fracking)ከልክሏል።»

እንዲህ ዓይነት እርምጃ ለመውሰድ ፣ በእስፓኝ ፣ ካንታብሪያ የመጀመሪያው አካባቢ ነው። የተፈጥሮ አካባቢ ተንከባካቢዎች፤ እንደሚሉት፤ «ፍራኪንግ»፣ በትኅተ-ምድር የሚገኘውን የተጠራቀመ ንጹህ የሚጠጣ ውሃ ይበክላል። እንዲሁም ለምድር ነውጥ አስተዋጽዖ ያደርጋል።

ኻቪር ፌርናንዴስ የተባሉት የአካባቢው የተፈጥሮ ክብካቤ ጉዳይ ኀላፊ አዲስ ረቂቅ ህግ ተቀባይነት አግኝቶ ከመጽደቁ በፊት ከተፈጥሮ አካባቢ ይዞታ ሥጋት አኳያ ጉዳዩ በጥሞና መመርመር አለበት።

ሆሴ ቢልባዎ የተባሉት ፀረ-ፍራኪንግ ታጋይ--

«በ «ፍራኪንግ ላይ ሰፊ የማኅበራዊና ሳይንሳዊ ክርክር በመካሄድ ላይ መሆኑን ተገንዝበናል። በሥነ ፍጥረትና በማህበራዊ ሳይንስ ረገድ ማለት ነው።»

በዓለም ዙሪያ ፣ የህዝብ ቁጥር እየጨመረ የመባልዕትና የኃይል ምንጭም ዋጋ እየተወደደ በሚሄድበት ባሁኑ ዘመን፤ ለተፈጥሮ አካባቢ ጉዳይ በማያስከትሉ፤ ተስማሚ በሆኑ አማራጭ በሆኑ ታዳሽ የኃይል ምንጮች መጠቀሙ የቱን ያህ ል እንደሚበጅ የሚያጠራጥር አይደለም። አማራጭ ታዳሽ የኅይል ምንጮች ሲባል፤ በፀሐይ፤ ውሃና ነፋስ የኤልክትሪክ አገልግሎት ማግኘት የሚቻልበት ዘዴ ነው። የተፈጥሮ ጋዝንም ቢሆን፣ እንደተወሳው፣ የሚጠጣ ውሃን ሳይበክል፣ በተፈጥሮ ለሚከሠተው የምድር ነውጥም ተጨማሪ አፍራሽ እገዛ ሳያደርግ ፣ የኃይል ምንጩን ጥቅም ላይ ማዋል የሚቻልበት አማራጭ መላ መሻቱ ፣ ምንጊዜም ሊደገፍ የሚችል እርምጃ እንደሚሆን ይታሰባል።

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic