በካን/ፈረንሳይ ፩ኛውን ሽልማት ያገኘው ያፍሪቃፊልም | ኤኮኖሚ | DW | 27.05.2004
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

በካን/ፈረንሳይ ፩ኛውን ሽልማት ያገኘው ያፍሪቃፊልም

የአፍሪቃው ሲኒማ አባት የሚባሉት የ፹፩ ዓመቱ ጎምቱ ሴኔጋላዊ የፊልም አዘገጃጀት መሪ ኡስማን ሴምቤን ባለፈው ቅዳሜ በካን/ፈረንሳይ በተካሄደው የፊልም ሙያ መገምገሚያ ዝግጅት ላይ ስለሴቶች ግርዘት ውገዛ ላቀረቡት ዝነኛ ፊልማቸው እጅግ ከፍተኛውን ሽልማት ነው ያገኙት።

ከበርካታ የዓለም አካባቢዎች ተጠረቃቅመው ለውድድር ከቀረቡት ከ፳ ከሚበልጡት ፊልሞች መካከል በአንደኛነት የተመረጠው የኡስማን ሴምቤን ፊልም፥ ገምጋሚዎቹ ዳኞችም እንዳሉት፣ ጨቅላ ልጃገረዶች ለአሰቃቂው ግርዛት እንዲዳረጉ የሚያደርገውን አለቅጥ አክራሪ እስላማዊ ልምድ የሚቃረንና የሚያወግዝ ነው። ባለሙያው ኡስማን ሴምቤን ራሳቸው ወደ ካን አልተጓዙም፣ ሆኖም ስለፊልማቸው ይዘት ለጋዜጠኞች ሰፊ ማብራሪያ ነው የሰጡት። “ሴቶች በማኅበራዊው ኑሮ ካደጉ፣ ከተራመዱ፣ ኅብረተሰቡም ያድጋል፣ ይራመዳል” ይላል የከያኒው ማስገንዘቢያ።

ፊልሙ የተቀረፀው፥ እጅግ ጥንታዊ ከሆኑት የምዕራብ አፍሪቃ መስጊዶች አንዱ በሚገኝበት አካባቢ በአንድ የገጠር መንደር ውስጥ ሲሆን፣ በዚያው ቦታ ሴቶቹ ከመጥፎው ልምድ ጋር በተቆራኙት ወንዶች ላይ በመነሳሳት ጨቅሎቹን ልጃገረዶች ከአሰቃቂውና ከአደገኛው የአካል ትልተላ ለማዳን ከፍተኛ ትግል ያደርጋሉ። ኡስማን ሴምቤን እንደሚሉት፣ የሴቶች ግርዛት ፴፰ ያፍሪቃ ሀገሮችን የሚመለከት ከባድ ችግር እንደሆነ ነው የሚገኘው። ካለፈው ዘመን መጥፎ ልምድ ለመላቀቅ የማይፈልጉት ወንዶችና ሴቶችም ብዙ ናቸው ባሁኑም ጊዜ። የፊልሙ ጀግና ሆና የምትቀርበው እናት በውልደት ጊዜ ሁለት ልጆቿን እንድታጣና አሁን ያለቻትን ቅንጣት ልጅ በኦፕራሲዮን እንድትወልድ ያደረጋት ያው የአካል ትልተላ መሆኑን በማስገንዘብ፣ የልጃገረዶች ሕይወት ምኑን ያህል ለአደጋ እንደሚጋለጥ ታስረዳለች። የፊልሙ አዘጋጅ ዓላማ አፍሪቃ ውስጥ ስሉዳዩ ክርክርን ማነቃቃት ነው፣ ሴቶችና ወንዶች እንዲወያዩበትና ጥፋቱን እንዲገነዘቡት ማድረግ። ለዚሁ የእውቀት ዘመቻ የፊልሙ ባለሙያ በማሊ፣ በሴኔጋል፣ በቡርኮናፋሶ፣ በኮትዲቯር፣ እና በጊኔቢሳው ገጠር አካባቢዎች እየተዘዋወሩ ፊልሙን ለማሳየት ነው አሁን የተዘጋጁት።

በሰብዓዊ መብት ጥበቃው ድርጅት አምነስቲ-ኢንተርናሽነል ግምት መሠረት፣ በዓለም ውስጥ ዛሬ ፩፻፴፭ የሚደርሱ ልጃገረዶችና ሴቶች ናቸው ግርዘት ለሚሰኘው የአካል ትልተላ የተዳረጉት፤ በያመቱም ሁለት ሚሊዮን የሚደርሱ ልጃገረዶች ናቸው አደጋው የሚያሠጋቸው። ይህ መጥፎ ልምድ አፍሪቃ ውስጥ አለቅጥ የተስፋፋ ሲሆን፣ በማዕከላይ ምሥራቅም በከፊል የተለመደ ነው።