በኦሮሚያ የቀጠለው ተቃውሞ | ኢትዮጵያ | DW | 13.02.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

በኦሮሚያ የቀጠለው ተቃውሞ

ከትናንትና ጀምሮ እስከ ነገ ረቡዕ ድረስ እንደሚቆይ የተነገረለት የንግድ ወይም የግብይት እንቅስቃሴ አድማ ዛሬም በተለያዩ ሥፍራዎች ቀጥሏል። በዛሬው ተቃውሞ ጅማ ከተማ ውስጥ ሦስት ሰዎች መሞታቸውን የከተማው አንድ ነዋሪ ለዶይቸቬለ ገልጧል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:37

በኦሮሚያ ዛሬም ተቃውሞ ቀጥሏል

ከትናንትና ጀምሮ እስከ ነገ ረቡዕ ድረስ እንደሚቆይ የተነገረለት የንግድ ወይም የግብይት እንቅስቃሴ አድማ ዛሬም በተለያዩ ሥፍራዎች ቀጥሏል። በጅማ ትናንት የጀመረው ተቃውሞ ዛሬም በተጠናከረ መልኩ ቀጥሎ ሁለት ሰዎች መሞታቸውን በስልክ ያነጋገርነው ነዋሪ ገልጦልናል። «አንደኛው ሰው ሞቷል፤ ሲወጣ ተመልክቸዋለሁ። ሌሎቹን ሁለት ሰዎች በአካል ሄጄ ማረጋገጥ አልቻልኩም» ሲሉም አክለዋል።

በጅማው ተቃውሞ የተከፈቱ ሱቆች እንዲዘጉ፣ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ፣ ኦሮምኛ ቋንቋም ብሔራዊ ቋንቋ እንዲሆን የሚሉ ጥያቄዎች መስተጋባታቸውን ነዋሪው ገልጠዋል። «ጂማ ከዳር እስከዳር እየተናወጠች ነው። ሕንጻዎች እየተቃጠሉ ነው፤ የአማርኛ ጽሑፎች ይቀደዳሉ ፖሊሶችም አስለቃሽ ጢስ ምናምን ተጠቅመው ህዝቡን ለመበተን ሞክረዋል።» 

በስልክ ያነጋገርነው የጅማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ከተቃውሞው ጋር በተያያዘ ለጅማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ምሳ ምግብ አለመግባቱን ተናግሯል። ሌላው ከጅማ ወጣ ባለ ስፍራ ተደብቆ እንደሚገኝ የተናገረው ነዋሪ በበኩሉ ፖሊሶች እንዳባረሯቸው ይናገራል። «እኛ ራሳችን ተደብቀን ነው ያለነው»ብሏል።

የወሊሶ ነዋሪው የዐይን እማኝ በበኩላቸው ከትናንቱ አንጻር የዛሬው ሰልፍ ሰላማዊ መኾኑን ይገልጻሉ። በወሊሶ ትናንት ጠዋት እስከ ረፋዱ አራት ሰአት ድረስ አነስተኛ የመጓጓዣ እንቅስቃሴ የነበረ መኾኑን ረፈድ ብሎም ተቃውሞው ተቀስቅሶ እንደነበር ገልጠዋል። የወሊሶው ተቃውሞ ከሰአት ከሰባት ሰአት በኋላ መጠናቀቁን ነዋሪው አክለው ተናግረዋል። 

የሐረማያው ነዋሪ ደግሞ ዛሬ በከተማው ተቃውሞ ባይኖርም የንግድ ቤቶች ተዘግተው ከተማው ረጭ ማለቱን ይናገራል። «መኪናም አይንቀስም፣ ሱቅም አንድም በር አልተከፈተም ከትናንትና ጀምሮ ነው፤ ዛሬም  ዝግ ነው» ሲል ኹኔታውን አሳይቷል። 

በአዲስ አበባ ዙሪያ የንግድ መደብሮች መዘጋታቸውን እና የመጓጓዣ አገልግሎት መቋረጡም በሮይተርስ እና በፈረንሳይ የዜና አውታሮች እንዲሁም በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ተዘግቧል። በፌስቡክ ገጻችን ከተላኩ አስተያየቶች መካከል ሃያት አህመድ «ወያኔ ችግሮችን በመሳሪያ እፈታለሁ እያለ ይበልጥ ከሚያባብስ ቆም ብሎ ቢያስብ ጥሩ ነው» ብላለች። ሞሳ ሰኢድ በበኩሉ፦ «ሀገሪቷን ሌላ አካል እንደሚቆጣጠራት ትናንት እና ዛሬ አየሁ በቃ አለቀ» ሲል ቅዱስ ያሬድ ደግሞ በአጭሩ፦ «ሥልጣን ለህዝብ ያስረክብ» ብሏል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ
 

Audios and videos on the topic