በኦሮሚያ አዲስ መንግሥት ሲመሰረት እነማን ተሾሙ? | ኢትዮጵያ | DW | 25.09.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

በኦሮሚያ አዲስ መንግሥት ሲመሰረት እነማን ተሾሙ?

አዲስ በተመሠረተው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ፕሬዝደንት፣ አቶ አወሉ አብዲ ምክትል ፕሬዝደንት ሆነዋል። በምክትል ፕሬዝደንት ማዕረግ 5 ባለሥልጣናት ተሾመዋል። 32 አባላት ካሉት የአቶ ሽመልስ ካቢኔ አስሩ ሴቶች ናቸው። የኦነግን አንድ አንጃ የሚመሩት አቶ አራርሶ ቢቂላ የኦሮሚያ ሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ሆነዋል

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:18

አቶ ሽመልስ አብዲሳ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዝደንት ሆነው ቀጥለዋል

አቶ ሽመልስ አብዲሳ አዲስ የተመሠረተው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዝደንት ሆነው ተሾሙ። ባለፈው ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. በተካሔደው ምርጫ አብላጫ መቀመጫ ያሸነፈው የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ አዲሱን መንግሥት ዛሬ መሥርቷል። በሚያዝያ 2011 ዓ.ም. አቶ ለማ መገርሳን ተክተው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንትነትን የተሾሙት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ዛሬ በተመሠረተው መንግሥት በያዙት ሥልጣን ቀጥለዋል።

በአዳማ ከተማ በሚገኘው የጨፌ ኦሮሚያ የመሰብሰቢያ አዳራሽ በተካሔደው መርሐ-ግብር የሥራ ዘመኑ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ለአንድ አመት ተራዝሞ ለስድስት አመታት ሥራ ላይ የቆየው ምክር ቤት በይፋ ተሰናብቷል።

ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱራህማን ዛሬ በይፋ ሥራ የጀመረው የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ሆነው ሲመረጡ አቶ ኤልያስ ዑመታ የምክትል አፈ-ጉባኤነት ቦታውን ይዘዋል። የክልሉ አፈ-ጉባኤ ሆነው የተሾሙት ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱራህማን ቀደም ሲል በምስራቅ ሐረርጌ ዞን የብልጽግና ጽህፈት ቤት የፖለቲካ አደረጃጀት ኃላፊ ሆነው እንዳገለገሉ በሹመታቸው ወቅት ተገልጿል።

ምክትል አፈ-ጉባኤ ኤልያስ ዑመታ የኢትዮጵያ መንግስት በአሸባሪነት የፈረጀው እና ራሱን "የኦሮሞ ነጻነት ጦር" ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን በስፋት የሚንቀሳቀስበት የምዕራብ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ በመሆን ያለፉትን ጥቂት ዓመታት ማገልገላቸው ተገልጿል።

የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት በዛሬው ውሎው የአቶ ሽመልስ አብዲሳ ካቢኔ አባል የሆኑ የሌሎች 32 ባለሥልጣናትን ሹመት አጽድቋል። ከተሿሚዎቹ መካከል አስሩ ሴቶች ናቸው።

የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ ፕሬዝደንት የነበሩት አቶ አወሉ አብዲ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝደንት ሆነዋል። አቶ አወሉ የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ ጭምር ሆነው ሰርተዋል።

አቶ ፈቃዱ ተሰማ በክልሉ ብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊነታቸው የቀጠሉ ሲሆን በጨፌ ኦሮሚያ የመንግሥት ተጠሪ ሆነው ያገለግላሉ።

አምስት ባለሥልጣናት በምክትል ፕሬዝደንት ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ቢሮዎችን በኃላፊነት እንዲመሩ ተሾመዋል። በዚህም ዶክተር ግርማ አመንቴ በምክትል ፕሬዝደንት ማዕረግ የመንግስት ሐብት አስተዳደር አስተባባሪ፣ ወይዘሮ መስከረም ደበበ በምክትል ፕሬዝደንት ማዕረግ የገቢዎች ባለሥልጣን ኃላፊ፣ አቶ አዲሱ አረጋ በምክትል ፕሬዝደንት ማዕረግ የከተሞች ማስተባበሪያ ክላስተር ኃላፊ፣ አቶ አብዱራሕማን አብደላ በምክትል ፕሬዝደንት ማዕረግ የገጠር ማስተባበሪያ ክላስተር ኃላፊ፣ አቶ አብዱልሐኪም ሙሉ በምክትል ፕሬዝደንት ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪ ሆነው ተሾመዋል። አቶ አብዱልሐኪም ሙሉ የጅማ ዞን አስተዳዳሪ የነበሩ ናቸው።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ለሁለት ከተሰነጠቀ በኋላ አንደኛውን ክንፍ የሚመሩት አቶ አራርሶ ቢቂላ የኦሮሚያ ሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ሆነው ተሾመዋል።

የኦሮሚያ ኮምዩንኬሽን ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ ጌታቸው ባልቻ ከሥልጣናቸው ተነስተው በአቶ ኃይሉ አዱኛ ተተክተዋል። አቶ ኃይሉ የኦሮሚያ ብልጽግና ጽህፈት ቤት ምክትል የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ነበሩ።

በዛሬው ሹመት አቶ አበራ ወርቁ የግብርና ቢሮ ኃላፊ፣ ወይዘሮ አዱኜ አሕመድ የፍትኅ ቢሮ ኃላፊ፣ አቶ ሻፊ ሑሴን የኦሮሚያ አስተዳደር እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ሆነው ተሾመዋል። አቶ ሻፊ የቡኖ በደሌ ዞን አስተዳዳሪ የነበሩ ናቸው።

ወይዘሮ ሚሊዮን በቀለ የውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ፣ አቶ ቶለሳ ገደፋ የገንዘብ ቢሮ ኃላፊ፣ አቶ አበራ ቡኖ የሚሊሺያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ፣ ወይዘሮ ሳሚያ አብደላ የወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ፣ አቶ ጉዮ ገልገሎ የቤቶች እና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ ፣ አቶ አሕመድ ኢድሪስ የሙያ እና ሥራ ዕድል ፈጠራ ቢሮ ኃላፊ፣ወይዘሮ ሐዋ አሕመድ የንግድ ቢሮ ኃላፊ ፣ ዶክተር መንግሥቱ በቀለ የጤና ቢሮ ኃላፊ፣ ወይዘሮ ሰዓዳ ዑስማን የባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ፣ አቶ ጉታ ላቾሬ የመሬት [አስተዳደር] ቢሮ ኃላፊ ፣ወይዘሮ መሰረት አሰፋ የኅብረት ሥራ ማህበራት ማደራጃ እና ማስፋፊያ ኤጀንሲ ኃላፊ  ዶክተር ተሾመ አዱኛ የኢንቨስትመንት እና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ ሆነዋል።

ወይዘሮ ሔለን ታምሩ የመንገዶች እና ሎጂስቲክ ቢሮ ኃላፊ ሆነው ሲሾሙ፤ አቶ ቶላ በሪሶ በኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ኃላፊነታቸው ቀጥለዋል። 

አቶ መሳይ ዳንኤል የመስኖ እና አርብቶ አደር [ጉዳዮች ቢሮ] ኃላፊ፣ ወይዘሮ ጀሚላ ሲምብሩ የሴቶች እና ሕፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ፣ አቶ ሑሴን ፈይሶ የፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ኃይል አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ፣ ዶክተር አብዱልአዚዝ ዳውድ የዕቅድ እና ኤኮኖሚ ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ አቶ ጌቱ ወዬሳ የፕሬዝደንት እና የምክር ቤት ጽህፈት ቤት ኃላፊ፣ ወይዘሮ ኮከቤ ዲዳ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ቢሮ ኃላፊ ሆነው ተሾመዋል።

ምክር ቤቱ የእጩዎቹን ሹመት በ12 ተቃውሞ እና በ13 ድምጸ-ተዓቅቦ አጽድቋል። የኦሮሚያ ክልል ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ከተካሔደው ምርጫ ወዲህ አዲስ መንግሥት በመመሥረት ከተቀሩት የኢትዮጵያ ክልሎች ቀዳሚ ሆኗል።

ስዩም ጌቱ

ታምራት ዲንሳ

እሸቴ በቀለ

 

 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች