1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኦሮሚያ በታጣቂዎች መስፋፋት እየተፈተነ ያለው የጉጂ ዞን

ዓርብ፣ የካቲት 18 2014

በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን አምስት ወረዳዎች በከፊልና ሙሉበሙሉ ኦነግ ሸነ በተባሉት ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር መሆናቸውን ነዋሪዎች እና ባለስልጣናት ገለጹ። በዞኑ ታጣቂዎቹ የተቆጣጠሯቸው አከባቢዎች አርሶ አደር ማምረት ማቆሙንና ሰዎች ለተለያዩ እንግልትና ሰቆቃ እንደሚዳረጉም ተነግሯል።

https://p.dw.com/p/47cLJ
Äthiopien Flüchtlinge in Oromia Region
ምስል Seyoum Getu/DW

አምስት ወረዳዎች በሸኔ ቁጥጥር ስር ሆነዋል


በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን አምስት ወረዳዎች በከፊልና ሙሉበሙሉ ኦነግ ሸነ በተባሉት ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር መሆናቸውን ነዋሪዎች እና ባለስልጣናት ገለጹ። በዞኑ ታጣቂዎቹ የተቆጣጠሯቸው አከባቢዎች አርሶ አደር ማምረት ማቆሙንና ሰዎች ለተለያዩ እንግልትና ሰቆቃ እንደሚዳረጉም ተነግሯል። የማህበራዊ አገልግሎትና የመንግስት ስራም በነዚህ አከባቢዎች ሙሉ በሙሉ በመቋረጡ ተማሪያች ከትምህርት ገበታቸው ተፈናቅለዋል፣ ጤና ጣቢያዎችም አገልግሎት አይሰጡም ተብሏል። 
ሳራ ጅብቻ በጉጂ ዞን የጉሚ ኤልዳሎ ወረዳ ነዋሪ ናቸው፡፡ አሁን ላይ ከአራት ወራት በፊት የሶማሌ ክልልን ከኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን የምታዋስነውን ይህቺን ወረዳ ሙሉ በሙሉ መንግስት ሸነ በሚል ስም በሽብርተኝነት በፈረጀውና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር በሚል በሚጠራው ሽምቅ ተዋጊዎች ቁጥጥር ስር በመግባቷ ተፈናቅለው በዞኑ መዲና ነጌለ ከተማ ተጠልለው ይገኛሉ። 
“ጉሚ ኤልዳሎ በሸማቂዎቹ ስር ከገባች አራተኛ ወር እያስቆጠረ ነው፡፡ እኛ ለዓመታት በጦርነት ውስጥ ነው ያሳለፍነው፡፡ አሁንም ሰላም እንደራቀን ነው፡፡ ባንድ በኩል ድርቅ በሌላው ደግሞ ግጭት ጦርነቱ እያሳደደን ግራ በተጋባ ህይወት ውስጥ ነን፡፡ ድርቁ ከብቶቻችንን እየገደ ለርሃብ ሲዳርገን፣ የፀጥታ ችግሩ ደግሞ ትራንስፖርት እንኳ እንዳይኖር በማድረግ የተራቡት ለሞት እየዳረገ ነው፡፡ ሰው በርሃብም በጥይትም በየቀኑ ነው የሚሞተው፡፡ ስቃይ ውስጥ ነን፡፡” 
ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸውን እንዳይጠቀስ የጠየቁን ሌላው በዞኑ የዋደራ ከተማ ነዋሪ በበኩላቸው እሳቸው ከሚገኙበት ከተማ ውጪ ያሉ በርካታ የገጠር ቀበሌዎች በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር ናቸው።
“ታውቃለህ ይህቺ ከተማ ዙሪያዋ በድን የተከበበ ነው፡፡ ሶስት አምስት ኪሎ ሜትር ወጣ ብትል እንኳ ታጣቂዎች ተሰግስገውበታል፡፡ ከዚህ ከተማ ሰው በየትኛውም አቅጣጫ ስወጣ እያገቱ ብር ይለቅማሉ፡፡ ሰው ያለውን ሁሉ ይዘረፋል፡፡ ከገጠር ቀበሌዎችም እየተነሱ ይሄው ወደ ከተማዋ እየተሰደዱ ነው፡፡ የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ሲወጡ በቦታው አያገኙዋቸውም፡፡ ከመንግስት አቅም በላይ ሆኗል ለማለትም ሆነ መንግስት አከባቢውን እያስተዳደረ ነው ለማለት ተቸግረናል። ”
የጉጂ ዞን መንግስት ኮሚዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ዮሓንስ ኦልኮ በቡላቸው ለዶይቼ ቬለ በሰጡት ማብራሪያ በዞኑ አምስት ወረዳዎች በከፊል እና ሙሉ በሙሉ በታጣቂዎች እጅ ስር በመውደቃቸው ከፍተኛ ቀውስ ተከስቷል፡፡ እንደ ኃላፊው ገለጻ ሰው በቁም ከመቀበር ጀምሮ በነዚህ አምስት ወረዳዎች አስከፊ ያሉት ሰቆቃዎች በህብረተሰቡ ላይ ይፈጸማል፡፡ በመንግስት መዋቅር የሚሰሩ ይገደላሉ፤ ተቋማቱም ይዘረፋሉ የሚሉት አቶ ዮሓንስ እየታገቱ ብር የሚጠየቅባቸውም ብዙ ናቸው ብለዋል፡፡ 
ይህ ሁሉ ሲሆን የመንግስት የፀጥታ አካላት ሚና ምን ነበር የተባሉት የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አሁን አሁን እየተወሰደ ነው ባሉት እርምጃ መሻሻሎች መኖራቸውን አውስተዋል፡፡ 
በነዚህ አከባቢዎች ትራንስፖርት ጨምሮ ምንም አይነት የማህበራዊ መገልገያዎች እንደሌሉም ተነግሯል፡፡ ከማህበረሰቡ የተዘረፉ ተሸከርካሪዎችን ታጣቂዎቹ እንደሚጠቀሙም እንዲሁ። ባለፈው ማክሰኞ ስለጉዳዩ ተጠይቀው ለህ/ተ/ም/ቤት ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በዓላማብስነት የፈረጁትን ሸማቂ ቡድን ከሚከተሉት የጦር ስልት አንጻር ለጸጥታ ኃይላቸው ፈታኝ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል። 
የኦሮሞ ነጻነት ጦር የምዕራብ ግንባር አዛዥ ኩምሳ ድሪባ (መሮ) ባለፈው ሳምንት ጦራቸው በህዝብ ላይ ያደርሳል ስለተባለው ሰቆቃ በቢቢሲ ተጠይቀው መሰል ተግባር የፈጸመ ታጣቂያቸው እስከ ሞት እንደሚቀጣ ነበር የመለሱት። 

Äthiopien Flüchtlinge in Oromia Region
ምስል Seyoum Getu/DW
Äthiopien Flüchtlinge in Oromia Region
ምስል Seyoum Getu/DW
Äthiopien Flüchtlinge in Oromia Region
ምስል Seyoum Getu/DW


ስዩም ጌቱ  
አዜብ ታደሰ 
ነጋሽ መሐመድ