በእግር ኳስ ታሪክ፤ የሳይንስና ሥነ-ቴክኒክ ድርሻ፤ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 09.06.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

በእግር ኳስ ታሪክ፤ የሳይንስና ሥነ-ቴክኒክ ድርሻ፤

በዓለም ዙሪያ፣ በማራኪነቱ ፤ በአስፈንዳቂነቱም ሆነ በልብ ሠቃይነቱ ወደር ያልተገኘለት ዘመናዊው የእግር ኳስ ጨዋታ በሳይንስና ቴክኒክ ድጋፍ ከፍ ካለ ደረጃ የመድረሱን ያህል፤ ሥነ-ቴክኒኩ የጨዋታውን ስሜት ፈንቃይነትና ለዛውንም እንዳያሳጣው

default

ሙሉ-በሙሉ ሥራ ላይ ማዋል አያስፈልግም ሲሉ፤ የዓለም የአግር ኳስ ፌደሬሽን (FIFA) የአመራር አባላት ፣ባለፈው መጋቢት በድምፅ ብልጫ ከወሰኑ ወዲህ የፌደሬሽኑ ፕሬዚዳንት Sepp Blatter ም፤ ባለፈው እሁድ ፕሪቶሪያ ፤ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በሰጡት መግለጫ ላይ፤ ይህንኑ አቋም በሚያጠናክር መልኩ ነው የተናገሩት።

ኳስ መረብ በመንካት ፣ ግብነቷን ሁሉም ማረጋጋጥ በሚችልበት ሁኔታ ሳይሆን፣ ከግቡ መስመር ፣ የቱን ያህል ሚሊ-ሜትርም ሆነ ሴንቲሜትር አልፋ ወደውስጥ በመግባት ግብ መሆን አለመሆኗን መለየት በሚያዳግትበት ጊዜ፣ አስቸጋሪውን ቅጽበታዊ ውሳኔ አጫዋች ዳኛ እንዲፈርድ ለእርሱ ከመተው፣ ከሜዳው ሥር የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ውጤቱን እንዲያሳይ ይፈቀድ የሚለውን ሐሳብ ነው፣ ብላተር አጥብቀው የተቃወሙት።

የሰጡት ምክንያት፤ በአስታዲዮም ተግኝቶ ጨዋታ የሚመለከተው ህዝብም ሆነ በቴሌቭዥን የሚመለከ,ው ሥፍር ቁጥር የሌለው የአግር ኳስ አፍቃሪ፤ ሁሉም የራሱን ብይን ሰጪ በመሆኑ እንደ ብላተር እምነት የእስፖርቱን ልብ -ሠቃይ ስሜት ፣ እስካሁን ባለው ሁኔታ እንዲጠበቅ ማድረጉ የተሻለ ነው። አለበለዚያ ለዛውን ያጣል፤ የኳስ ጠበብትም ቦታ አይኖራቸውም። ተግባራቸውን ለሥነ-ቴክኒክ አስረክበው ገሸሽ ማለት ስለሚኖርባቸው፤ ይህ እንዲሆን መፍቀድ የለብንም በማለት ነው የሚከራከሩት።

የእግር ኳስ አጀማመርና አሁን የሚገኝበት ደረጃ፣

በፊኛም ሆነ ሌላ ቀለል ባለ ክብ ነገር በእግርና በአጅ የመጫወቱ ልማድ፣ በዓለም ዙሪያ በተለያዩ አገሮች በተለያየ መልኩ የረጅም ጊዜ ታሪክ ያለው ነው። ምናልባት 3,000 እና ከዚያም በላይ ዕድሜ ሳይኖረው እንዳልቀረ ይታሰባል። በ 16ኛውና በ 17ኛው ከፍለ ዘመን ብሪታንያ ውስጥ በኳስ ሜዳ ግቦች ተሠርተው መረቦች ተዘርግተው፤ ጨዋታ ይካሄድ እንደነበረ ቢነገርም ፤ በአሁኑ ዘመን የሚታየውን የእግር ኳስ ጨዋታ፣ እ ጎ አ በ 1863 ዓ ም ፤ (በአፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት መሆኑ ነው) ቅርጽ እንዲይዝ ያበቁት እንግሊዞች ናቸው። በመጀመሪያ በኢንግላንድ ከዚያም በእስኮትላንድና በሌሎቹም የአገሪቱ ክፍሎች በክለቦች ምሥረታ ከተስፋፋ በኋላ ነው፤ ሌሎች ፈለጉን መከተል የጀመሩ። ኔደርላንድና ደንማርክ፤ በ 1889 አርጀንቲና በ 1893፤ ኢጣልያ በ 1898 ጀርመን ደግሞ በ 1900 ዓ ም የአግር ኳስ ማኅበር ማቋቋሟ ይታወሳል። ከመጫወቻው ሜዳ ስፋትና ርዝማኔ አንስቶ የተጫዋቾችና ዳኞች ቁጥር ፣ የኳስ ዓይነትና መጠን የተጫዋቾች ትጥቅ፤ ጨዋታው (ግጥሚያው ) የሚወስደው ጊዜ፤ ሁሉም በሥነ-ቴክኒክ ድጋፍ ብዙ መሻሻል ተደርጎለታል።

የኳሱ ሜዳ በተለያዩ አገሮች የርዝማኔውና ስፋቱ መጠን የጥቂት ሜትሮችም ሆነ ሴንቲሜትሮች ልዩነት ሊኖረው ይችላል። ለምሳሌ ያህል ስፋታቸው ከ45 እስከ 90ሜትር፤ ርዝማኔአቸውም ከ 90 እስከ 120 ሜትር የሆነ እስታዲየሞች አሉ። በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቁት ከ64 እስከ 75 ሜትር ስፋት እንዲሁም ከ 100 እስከ 110 ሜትር ርዝማኔ ያላቸው ሜዳዎች ቢሆኑም ፤ ለዓለም አቀፍ ግጥሚያዎች፣ የፊፋ የአግር ኳስ ደንቦች ተመልካችና ብይን ሰጪ አካል(IFAB) እ ጎ አ በ 2008 ዓ ም፤ አማካዩን መጠን በመምረጥ በወሰነው መሠረት፣ ዓለም አቀፍ መደበኛ የእግር ኳስ ሜዳ መጠን ፤ 105 ሜትር ርዝማኔና 68 ሜትር ስፋት ያለው ነው። ይኸው የአግር ኳስ ሜዳ መጠን የተመረጠው፤ ከግብ ጠባቂዎቹ በስተቀር፣ ሜዳ ውስጥ ወዲያና ወዲህ እየተሯሯጡ ለሚጫወቱት 20 ተጨዋቾች የሚመጥን መሆኑ በጥናት ተደርሶበት ነው። እርግጥ ነው የጂዖሜትሪ ባለሙያዎች 65 X 105 ን እንደሚመርጡ የታወቀ ነው። በተረፈ፤ 660 ካሬሜትር መጠን ባለው የእግር ኳስ ሜዳ፤ ከግብ መስመር 5,5፤ 16,5 ፤ 11, እንዲሁም 9,5 ሜትር ርቀት ለቅጣት ምት ወሳኝ ድርሻ አላቸው።

የእግር ኳስ ጨዋታ፤ በተለይ የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ፤ እ ጎ አ በ 1930 ዓ ም በዑሩጋይ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ፤ ባለፉት 80 ዓመታት በአትሌቲክስ ውድድሮች የተከሠተው ዓይነት ፈጣን ለውጥ እየታየበት ነው ። ተጫዎቾቹ ብቻ አይደሉም፤ በፍጥነት የሚጫወቱት ። የሚጫወቱባት ኳስም ፈጣን ሆናለች። አሠራር ላይ ብዙ ለውጥ በመደረጉ! ታዋቂው ኩባንያ «አዲዳስ»፤ እ ጎ አ ከ 1970 ዓ ም አንስቶ እስካሁን በ 44 ዓመታት ውስጥ የተለያዩ ጥራትና ፍጥነትም ያላቸውን ኳሶች እየሠራ ማቅረቡ ይታወሳል። Telstar የተባለው የኢንዱስትሪ ኩባንያ በ 1970 ዓ ም፤ ሲመታ በሰዓት 100 ኪሎሜትር የሚከንፍ ኳስ ሠርቶ ነበረ። እ ጎ አ በ 1990 ዓ ም፤ ኢጣልያ ውስጥ ተካሂዶ በነበርው ውድድር «ኤርትሩስኮ ዑኒኮ» የሚል ስያሜ የተሰጠው ኳስ በሰዓት 120 ኪሎሜትር ፍጥነት እንደነበረው የሚታወስ ሲሆን፤ ከዚያ ጊዜ አንስቶ በ የ 4 ቱ ዓመት የሚሠሩት ኳሶች የተሻሻለ ለውጥ ታይቶባቸዋል።

ከ 4 ዓመት በፊት በጀርመን አገር ተካሂዶ በነበረው የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ «አዲዳስ» ለ «ፊፋ» ያቀረበው፤ ጀርመኖች Teamgeist(የቡድን መንፈስ) ያሉት ኳስ ፣ አስቀምጠው ሲመቱት በሰዓት እስከ 189 ኪሎሜትር እንደ ጥንግ መብረር እንደሚችል Steven Reid የተባለው የእንግሊዙ «ብላክበርን ሮቨርስ« ተጫዋች አሥመሥክሯል። ሬይድ፤ ቡድኑ፤ ከ «ዊገን አትሌቲክስ» ጋር በተጋጠመበት ጨዋታ ነው የተጠቀሰውን ክብረወሰን ያስመዘገበው። በዘንድሮው የደቡብ አፍሪቃው የዓለም ዋንጫ ውድድር የሚቀርበው ፤ ባለፈው ኅዳር 25 ቀን 2002 ዓ ም ይፋ የሆነው «ጃቡላኒ» የሚል ስያሜ የተሰጠው ኳስ፣ ከ ጀርመኑ «ቲም ጋይስት« የፈጠነ ነው። ጃቡላኒ፣ እግር ላይ እስከመፈንዳት መድረሱ የተገለጠ ሲሆን፣ በሰዓት 200 ኪሎሜትር ድረስ ፍጥነት ሳይኖረው እንደማይቀር ተገምቷል። «ጃቡላኒ» ማለት በዙሉ ቋንቋ፤ በዓል ማክበር እንደማለት ነው፣ እዚህም ላይ የኳስ ጨዋታ ድግስን የሚጠቁም ሊሆን ይችላል።

Durban Stadion in Südafrika Lichtbogen LED Leuchten Flash-Galerie

የንስ ሃይልማን የተባሉት ጀርመናዊ ፎቶግራፍ አንሺ፤ ባለፉት 3 ዓመታት የኦለም የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድሮች የተካሄዱባቸውን አገሮች በመጎብኘት እ ጎ አ ከ 1930 እስከዛሬ ድረስ ፤ በውድድሮች ላይ የቀረቡትን የኳስ ዓይነቶች ፎቶግራፎቻቸውን ከታሪካቸው ጋር ያጣመረ መጽሐፍ ያቀረቡ ሲሆን፤ ስለዘመናዊዎቹ ኳሶች እንዲህ ብለዋል።

«በአሁኑ ጊዜ የሚቀርቡት ኳሶች በሥነ-ቴክኒክ ድጋፍ አሠራራቸው የረቀቀ ነው። በአርግጥ የኳሶቹ ባህርይ የሚታወቅ ይሆን ዘንድ ያልተሞከረ ይህንና የመሳሰለ ነገር የለም። ሌላም ሌላ!-- ይሁንና ፤ የጨዋታ ወሳን ኳስ ሳይሆን ተጫዋቾች ናቸው።»

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻሉ ስለተሠሩ ኳሶች ይህን ያህል ካልን ፤ ታታሪ ተጫዋቾችስ ምን ያህል ነው ሜዳ ውስጥ የሚንቀሳቀሱት? በረቂቅ ሥነ ቴክኒካዊ መሣሪያዎች በተደረገው ክትትል መሠረት በጣም ጥሩ የመሃል ሜዳ አከፋፋይ ተጫዋች ከ 12 ኪሎሜትር በላይ የሚያስጉዝ እንቅሥቃሴ ማድረግ ሳይጠበቅበት አይቀርም። ባለፈው የአውሮፓ ዋንጫ የፍጻሜ ግጥሚያ፤ እስጳኝ፤ ጀርመንን 1-0 አሸንፋ የዋንጫ ባለቤት በሆነችበት ግጥሚያ፣

በአንደኛ ደረጃ፤ 12,56 ኪሎሜትር ርቀት ማስኬድ የሚያስችል እንቅሥቃሴ ያደረገው ፤ የእስፓኙ የመሃል ሜዳ አከፋፋይ ተጫዋች፤ በአጭሩ ሻቪ የሚሰኘው ሻቪር ኤርናንዴዝ ኢ ክሬዎስ ነው። ጀርመናዊው ሚሻኤል ባላክ ፤ ያኔ፣ ሜዳ ላይ 11,4 ኪሎሜትር የሚያስጉዝ እንቅሥቃሤ ማድረጉ ታውቋል።

ብርቱ ፉክክር የሚታይበት አድካሚው የእግር ኳስ ጨዋታ፣ በተጫዎቾች ላይ አልፎ- አልፎ ከሚያደርሰው የጤና እክል ሌላ፤ በተመልካቾችም ላይ የሚያስከትለው ሳንክ ስለመኖሩ የታወቀ ነው። በተለይ ትንሽ የልብ ህመም ቢጤ ያለባቸው ሰዎች ሊጠነቀቁ እንደሚገባ ሀኪሞች ይመክራሉ። በይበልጥ ደግሞ ወሳኝ በሆኑ ግጥሚያዎች ወይም በፍጻሜ ግጥሚያ፤ ውድድሩ በ ፍጹም ቅጣት ምት እንዲለይ የሚደረግ ከሆነ፤ ትንሽ የጤና እክል ያለባቸው ሰዎች አደጋ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ጥናቶች ይጠቁማሉ። ለምሳሌ ያህል፤ እ ጎ አ ሰኔ 30, ቀን 1998 ዓ ም፤ፈረንሳይ ውስጥ ተዘጋጅቶ በነበረው የዓለም የአግር ኳስ ዋንጫ ውድድር፤ ኢንግላንድ፤ በፍጹም ቅጣት ምት፣ በአርጀንቲና ስትሸነፍ፤ ኢንግላንድና ዌልስ ውስጥ በሁለት ቀናት ውስጥ ብቻ በልብ ህመም ሀኪም ቤት የገቡት ሰዎች ቁጥር 25 ከመቶ ጨምሮ ነበር። እ ጎ አ በ 1996 ዓ ም፣ የኔደርላንድ ብሔራዊ ቡድን፤ በፍጹም ቅጣት በለየለት የአውሮፓ ሀገራት የእግር ኳስ ዋንጫ ግጥሚያ፣ በፈረንሳይ በተሸነፈበት ዕለት፤ በልብ ድካም ሳቢያ የሞቱት ኔደርላንዳውያን ቁጥር 50 ከመቶ ንሮ እንደነበረ ታውቋል። በሁለቱም ጊዜያት የልብ ህመም ያገረሸባቸውም ሆኑ በዚህ ሳቢያ የሞቱት፤ ወንዶች እንጂ ሴቶች አይደሉም።

በሌላ በኩል፤ ጀርመን ውስጥ ፤ ከ 4 ዓመት በፊት በተካሄደውና ኢጣልያ አሸናፊ በሆነችበት የዓለም ዋንጫ ውድድር፤ የ 7,2 ሚሊዮን ሰዎችን የጤንነት ይዞታ ከጤና የመድኅን ኩብንያዎች ጋር በመተባበር የመረመረው የኮሎኝ ዩኒቨርስቲ ክሊኒክ ፤ በልብ ድካም ሳቢያ የሞቱት በጣም ጥቂቶች ነበሩ ሲል ልብ የሚሠቅሉም ሆኑ የሚመስጡ ጨዋታዎች፣ ለጤንነት ያን ያህል አደገኞች አይደሉም ሲል ዛሬ ይፋ ባደረገው የጥናት ውጤት አስታውቋል። በሙዑንሸን (ሙዩኒክ) በ 2008 የተካሄደ ጥናት ደግሞ የኮሎኙን ጥናት የሚቃረን ሆኖ ተገኝቷል። የሙዩኒኩ ጥናት ብርቱ የሆኑ ወሳኝ ውድድሮችን በእስታዲየምም ሆነ በቴሌቭዥን ከሚከታተሉ ሰዎች መካከል፤ በጤንነት እክል ሳቢያ ወደ ሆስፒታል የሚወሰዱት ቁጥራቸው ከፍ እንደሚል ተደርሶበታል ይላል።

ድንጋጤ ፣ትካዜ ደስታ ፤ ፈንጠዝያ ፤ ሁሉም መጠናቸውን እንዳይልፉ ራስን ለመቆጣጠር መሞከር አይበጅም አይባልም። ተክሌ የኋላ፣

ተክሌ የኋላ፣

ነጋሽ መሐመድ፣