በኤርትራ ፖለቲካና ኤኮኖሚ ጉዳይ ላይ ዉይይት | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 15.09.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

በኤርትራ ፖለቲካና ኤኮኖሚ ጉዳይ ላይ ዉይይት

ኤርትራ እንደ አገር ከተመሰረተች በቅርቡ የ25 ዓመት ጉዞዋን ደፍናለች። በ1980ዎቹ ለፖለቲካና ለኢኮኖሚ ዕድገት አንግባ የተነሳችዉ ኤርትራ በጎዞዉ ከባድ ፈተና አጋጥሟታል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:33

በኤርትራ ጉዳይ ላይ ዉይይት

አገሪቱን የሚያስተዳድርዉ መንግስት በዜጎች ላይ ከረር ያለ የአስተዳደር ስልት መከተሉ፣ እስካሁን ዜጎችና መንግስትን ሊመራ የሚችል ህገ-መንግስት ቦታ ላይ አለመኖሩ፣ እንዲሁም የዉጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ አገሪቱ ከሌሎች ሃገራት ጋር ሊኖራት የሚችለዉ ግንኙነት በከፍተኛ ሁኔታ እንደቀነሰ ዘገባዎች ያመለክታሉ። በዚህም ምክንያት አገሪቱ በሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብት መጣስ ትተቻለች። ኤርትራ ለስደት ቀዉስ ተዳርጋለች። በዚህም ጉዳይ ላይ ለመወያየት የኤርትራ መንግሥት የልዕካን ቡድን ከጀርመን ባለስልጣናቶችና ባለሙያዎች ጋር ባለፈዉ ሳምንት በርሊን ዉስጥ ዉይይት አድርገዋል። የዛሬዉ አዉሮጳና ጀርመን ዝግጅት በዉይይቱ ላይ ያተኩራል።

«ኤርትራን ከሰሜን ኮርያ ጋር ማወዳደር በሕይወቴ ዘመኔ ሰምቼ የማላዉቀዉ ትልቅ ስህተት ነዉ። የትኛዉም አሳቢ ሆነ ፖለቲከኛ ይህን አገላለፅ መጠቀም የለበትም፤ ምክንያቱም ዉሸት ነዉና።»


ይህን ያሉት ጀርመናዊትዋ ፖለቲከኛና የጀርመን-አፍሪቃ ድርጅት ፕሬዚዳንት ዶክተር ኡሺ አይድ ሲሆኑ ይህንንም ያሉት የኤርትራን ፖለቲካና ኤኮኖሚ ነባራዊ ሁኔታ በተመለከተ በበርሊን ከተማ በሁምቦልት ካሬ አዳራሽ የተዘጋጀዉን ዉይይት በንግግር ሲከፍቱ ነዉ። ባለፈዉ ኃሙስ የተካሄደዉ ዉይይት ላይ የኤርትራ የዉጭ ጉዳይ ሚንስትር በአቶ ኦስማን ሳሌ የሚመራዉ ልዑካን የፕሬዚዳንት እሳያስ አፈወርቂ አማካሪ ፤ አቶ የማነ ገብረአብን ጨምሮ የብሔራዊ ልማት ሚንስቴር ዶክተር ጊዮርጊስ ተ/ሚካኤልን አሳትፈዋል። በጀርመን በኩል ከዉጭ ጉዳይና ከጀርመን ፓርላማ፣ የሚድያ ተቋማትን እንዲሁም መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የመጡንም አሳትፈዋል።

የኤርትራ ጉዳይን በቅርብ የሚከታተሉት ባለሙያዎች ኤርትራን ከሰሜን ኮርያ ጋር ማወዳደር ዝም ብሎ ከሰማይ የወረደ እንዳልሆነ ይናገራሉ። ኤርትራ እንደ ሰሜን ኮርያ የኒዉክሌር ጦር መሳርያ እስከ አፍንጫ ባትታጠቅም፣ እንዲሁም ለምዕራባዊያን ስጋት ባትሆንም፣ ኤርትራን ከሰሜን ኮርያ ጋር ማወዳደሩ በተወሰነ መልኩ እንደሆነ፣ በተለየም በሰብዓዊ ጉዳይና ዴሞክራስያዊ መብቶች ረገጣ፣ እንዲሁም ራሷዋን በፖለቲካም ሆነ በኤኮኖሚ ከዉጭ ግንኙነቶች ራስዋን ማግለሏዋ እንደሆነ የሚከራከሩም አልጠፉም።


በርካታ ትችት አቅራቢዎች ኤርትራ የመድበለ ፓርቲ ማቀፍና በ1989 የረቀቀዉ ሕገ መንግስት ስራ ላይ መዋል ያልቻለበት ምክንያት ለምንድነዉ ብሎ የሚጠይቁ አልጠፉም። የኤርትራ ፕሬዚዳንት አማካሪና የገዢዉ ፓርቲ ሃላፊ አቶ የማነ ገብረዓብ ለዚህ መልስ አላቸዉ።

«የቅኝ አዘገዛዝ ካበቃለት ጊዜ ጀምሮ በአፍሪቃ ያለዉ የፖለቲካ አስተዳደር እኛን በጣም ያሳስበናል። የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ብዙ ቦታዎች አልተሳካም። ለምሳሌ የኛ አጎራባች አገር የሆነችዉ ኢትዮጵያ ብዙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢኖርዋትም የህዝቡን ፍላጎት ለማሟላት በረጅም ርቀት ላይ ትገኛለች። የኛ ፍለጎት አንድ ህዝቡን ያማከል የአገዛዝ ስልት መምስረት ነዉ፣ በዚህም የዜጎች እኩልነትና ሰብዓዊ መብቶች የሚከበርባት አገር መገንባት ነዉ። እኛ የምንፈለገዉ የአገሪቱን ሁኔታና የህዝቡን ፍላጎት ግምት ዉስጥ ያስገባ የፖለቲካ ስርዓት መገንባት ነዉ። አሁን እኛ ያለንበት የሙከራ ደረጃ ላይ ነዉ፣ ቢሆንም እንዲህ አይነቱን የፖለትካ ስረዓት ለኤርትርያ መገንባት እንቀጥልበታለን።»


ኤርትራ ከ25 ዓመት በፊት ያረቀቀችዉ ሕገ- መንግሥት እስካሁን ስራ ላይ ያልዋለበት ምክንያት ለምንድነዉ?


«በአብዛኛዉ የአፍሪቃ አገር በህግ-መንግስቱ ላይ የተፃፈዉና በመሬት ላይ የሚደረገዉ ሰማይና ምድር ነዉ። አብዛኛዉ የአፍሪቃ አገር ፕሬዝዳንቱን በስልጣን ላይ ለማቆየት ሲባል ህግ-መንግስታቸዉን ይለዋዉጣሉ። ለኛ ህገ-መንግስት ማለት ዘላለም የሚኖር ሰነድ ነዉ። ህገ-መንግስት ለኛ በቀጣይ የሚኖር ነዉ። በ1991 ዓ, ም ህገ-መንግስቱ በኤርትራ ሲረቀቅ፣ አሁን አገሪቱ ዉስጥ የሚኖሩ ከ60-70 በመቶ የሚሆኑ ወጣቶች የሂደቱ አካል አልነበሩም። ለዚህም ነዉ ለሁሉም የህዝቡ አካል እኩል እድል ዳግም መስጠት የምንፈልገዉ። ለዚህም ሁሉም አቀፍ የሆነና የኛን ጉዳይ ያማከለ ህግ-መንግስት እንደዘጋጅ እንጥራለን።» ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማድመጫዉን በመጫን ይከታተሉ።

መርጋ ዮናስ

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic