በኤርትራ እስረኞችን ለማስፈታት የጀመረ ዘመቻ | አፍሪቃ | DW | 17.09.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

በኤርትራ እስረኞችን ለማስፈታት የጀመረ ዘመቻ

የኤርትራ መንግሥት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ላይ ትችት በመሰንዘራቸዉ ከታሰሩ 18 ዓመት የሞላቸዉ 11 ፖለቲከኞች እና 17 ጋዜጠኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ሲል ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣዉ መግለጫ አሳሰበ።

የኤርትራ መንግሥት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ላይ ትችት በመሰንዘራቸዉ ከታሰሩ 18 ዓመት የሞላቸዉ 11 ፖለቲከኞች እና 17 ጋዜጠኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ሲል ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣዉ መግለጫ አሳሰበ። 28 ግለሰቦች ከታሰሩ ከጎርጎረሳዉያኑ 2001 ዓም ወዲህ ለ 18 ዓመታት ታይተዉ እንደማያዉቁ የገለፀዉ ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት፤  የኤርትራ መንግሥት እስረኞቹን በአስቸኳይ እዲፈታ የሚል ዘመቻ ከዛሬ ጀምሮ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ መጀመሩንም አስታዉቋል። 11 ዱ ፖለቲከኞች ለእስር የበቁት በኤርትራ ምርጫ  እንዲካሄድ ፤ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን እና ሕገ-መንግስቱ እንዲያከበር  በሚል ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ  ግልፅ ደብዳቤ በመፃፍ ግፊት በማድረጋቸዉ ነዉ። 17 ቱ ጋዜጠኞች የታሰሩት ደግሞ ፖለቲከኞቹ ለየፃፉትን ግልጽ ደብዳቤ አስመልክቶ  በመዘገባቸዉ ነበር።  28ቱም ግለሰቦች ከታሰሩ ወዲህ በክስ ፍርድ ቤት ቀርበዉም ታይተዉ አያዉቁም።  በኤርትራ የቀጠለዉ የዘፈቀደ እስር  የፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ መንግሥት ላይ ተቃውሟቸውን የሚያሰሙ ዜጎችን ለማፈን እስከ ጥግ እንደሚሄድ አመላካች ነዉ ያለዉ አምነስቲ በኤርትራ እስር ቤቶች ታጉረዉ እንደሚገኙት በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሁሉ 28 ቱ ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ ሲል በመግለጫዉ አሳስቦአል። ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት   በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ለ 18 ቀናት የሚዘልቅ ዛሬ የጀመረዉ ዘመቻ፤  ልክ የዛሬ ዓመት የቀድሞ የኤርትራ የፋይናንስ ሚኒስትር ብርሃኔ አብርኸ በኤርትራዉ መንግሥት ወደ እስር ቤት የተወረወሩበት ቀንን ምክንያት በማድረግ መሆኑን ገልፆአል። የኤርትራዉ ፋይናንስ ሚኒስትር ብርሃኔ አብርኸ የታሰሩት፤ የኤርትራ ሕዝብ ለዴሞክራሲ በሰላማዊ መንገድ እንዲሰራ ጥሪ ያደረጉበትን መጽሐፍ በማሳተማቸዉ ነበር። ብርሃኔ አብርኽ ከታሰሩ በኋላ ታይተዉ አያዉቁም። በአምነስቲ መግለጫ መሰረት የቀድሞዉ የኤርትራ ፋይናንስ ሚኒስትር እንደሌሎች እስረኞች ሁሉ ፤ ከቀሪዉ ዓለም ጋር እንዳይገናኙ በኤርትራ ምስጥራዊ ቦታ ታስረዋል። 

 

አዜብ ታደሰ 

ኂሩት መለሠ