በኢትዮጵያ 776 ሰዎች በአጣዳፊ የተቅማጥ በሽታ ሞተዋል | ጤና እና አካባቢ | DW | 12.06.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

በኢትዮጵያ 776 ሰዎች በአጣዳፊ የተቅማጥ በሽታ ሞተዋል

በኢትዮጵያ ሶማሌ፣ በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብና በአማራ ክልሎች በተከሰተዉ የድርቅና የዉኃ እጥረት አጣዳፊ የተቅማጥ በሽታን ካስከተለ ወራቶች ተቆጥረዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:15

በዝናብ ወራት የአጣዳፊ የተቅማጥ በሽታ ሊባባስ ይችላል፤

ከጥር እስከ ግንቦት ወር 2009 ዓ/ም አጣዳፊ የተቅማጥ በሽታና የዉኃ እጥረት ከ33,000 በላይ ሰዎች እንደተጎዱ፤ 776 ሰዎችም እንደሞቱ በኢትዮጵያ የInternational Rescue Committee ረዳት የጤና አስተባባሪ አቶ ደረጀ አሰፋ ለዶይቼ ቬሌ ገልጸዋል።

አጣዳፊ የተቅማጥ በሽታ ከባለፉት ወራቶች እየቀነሰ የሚገኝ እንደሚመስል ያመለከቱት አቶ ደረጀ ከአምስቱ ክልሎች 97 ወረዳዎች በዚህ በሽታ እንደተጠቁና ከነዚህም 91 በመቶዉ ሶማሌ ክልል ዉስጥ እንደሚገኙም ይናገራሉ። ኮሚቴዉ ማክሰኞ ዕለት ባወጣዉ መግለጫ መንግሥትና የርዳታ ድርጅቶች አፋጣኝ ርምጃ ካልወሰዱ በአገሪቱ የጀመረዉ የዝናብ ወቅት የበሽታዉ ሁኔታ ሊያባባስ እንደሚችል ጠቁሟል።

ይህን ችግር ለመፍታት የመንግሥት ድርጅቶችን ጨምሮ አጋር አገሮች እየተሳተፉ ቢሆንም ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ እጥረት እንዳለ አቶ ደረጀ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል።
በኖርዌይ የስደተኞች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ተጠሪ የሆኑት አቶ አሀመድ ኑር አብዲ ምክር ቤቱ በሶማሌ ክልል የዉኃ ማጠራቀሚያ የመገንባት፣ የመፀዳጃ ጉድጓድ የማዘጋጀት፣ የዉኃ ምንጭ የመጠበቅና በመሳሰሉ የንፅህና ጉዳይ ላይ እየሠራ መሆኑን ይናገራሉ።

ኮሚቴዉ በዘገባዉ የዝናቡ ወቅት አጣዳፊ የተቅማጥ በሽታን ሊያባባስ ይችላል ቢልም፤ አቶ አሀመድ ግን በሶማሌ ክልል ያለዉ የዝናብ እጥረት ድርቁን ሊያባብስ ይችላል ነዉ የሚሉት። አቶ አሀመድ: «በርግጥ ሁኔታዉ አሳስቦናል። ምክንያቱም አነስተኛ መጠን ያለዉ ዝናብ እዚህና እዛ ማገኘት ማለት በድርቁ የተጎዱት ሰዎች ችግራቸዉ ተፈታ ማለት አይደለም። የምናየዉ በአንድንድ ቦታ ላይ ዝናብ ዘነበ የሚባለዉ በቂ አለመሆኑን ነዉ።»

ኮሚቴዉ በመግለጫዉ በኢትዮጵያ፣ በሶማሊያ፣ በኬንያ፣ በደቡብ ሱዳንና በየመን ከጥር ወር ጀምሮ ከ130,000 በላይ ሰዎች በአጣዳፊ የተቅማጥ በሽታና በኮሌራ መጠቃታቸዉን አመልክቷል።  ከነዚህም ከ2, 100 በላይ የሚሆኑት ሰዎች መሞታቸዉንም ጠቅሷል።

ኢትዮጵያን በተመለከተ ስለሁኔታዉ የበለጠ መረጃ ለማግኘት ወደ ጤና ጥበቃ ሚኒሥቴር በስልክ በተደጋጋሚ ያደርገነዉ ሙከራ አልተሳካም።

መርጋ ዮናስ

ሸዋዬ ለገሠ 

Audios and videos on the topic