በኢትዮጵያ 2016 የጭካኔና የገደቦች ዓመት ነበር ተባለ | ኢትዮጵያ | DW | 13.01.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ 2016 የጭካኔና የገደቦች ዓመት ነበር ተባለ

ሂዩማን ራይትስ ዎች ትናንት ጥር 4 ምሽት ባወጣው ዓመታዊው ዓለም አቀፍ ዘገባ የጎርጎሮሳዊው 2016 “በኢትዮጵያ የጭካኔና የገደቦች ዓመት ነበር” ሲል ጠርቶታል፡፡ ኢትዮጵያ በሰብአዊ መብቶች ቀውስ ዉስጥ መውደቋን ምሳሌዎች እየጠቀሰ የሚያትተው ዘገባው መንግስት ተቃውሞዎችን ለማፈን ያልተመጣጠነና አላስፈላጊ ሀይል ተጠቅሟል ሲል ወንጅሏል፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:41

መንግስት ለህዝብ ቅሬታዎች መልስ መስጠት አለበት ተብሏል

መቀመጫውን በኒውዮርክ ያደረገው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ተቋም ሂዩማን ራይትስ ዎች ትናንት ያወጣው ዳጎስ ያለ ዘገባ በ90 ሀገራት ያለውን የሰብዓዊ መብት ትግበራ የገመገመበት ነው። በጎርጎሮሳዊው 2016 በምስራቅ አፍሪካ የተቃውሞና ሀሳብን የመግለጽ አፈና እንደተስተዋለ የሚያትተው ዘገባው የየሀገራቱ መንግስታት የወሰዷቸው እርምጃዎች በአካባቢው የሰብአዊ መብት ሁኔታን እጅግ አሳሳቢ አደጋ ዉስጥ ከቶታል ብሏል፡፡ 

ዘገባው በምስራቅ አፍሪካ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አካሄደዋል ያላቸውን ኬንያን እና ኡጋንዳን፣ ደቡብ ሱዳንን እና ቡሩንዲን እንደዚሁም ሶማሊያን ቢዳስስም ለኢትዮጵያ ግን ከፍ ያለ ቦታ ሰጥቷል፡፡ ኢትዮጵያ “ሰላማዊ ሰልፎችን በጭካኔ ለመጨፍለቅ የወሰደችው እርምጃ በሰብዓዊ መበት ጥበቃ ረገድ “ከአካባቢው የመጨረሻ ዝቅተኛ ደረጃ” እንድታስመዘግብ እንዳደረጋት ሂዩማን ራይትስ ዎች ገልጿል፡፡ 

የሂዩማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ አጥኚ ፌሊክስ ሆርን ኢትዮጵያን ከሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በተለየ ለምን ትኩረት እንደተደረገባት እንዲህ ያብራራሉ፡፡ 

 “በእርግጥ በሰላማዊ ተቃውሞ ላይ የተሰነዘረ ጭካኔ የተሞላበት አፈና በኡጋንዳም፣ በኬንያም በኢትዮጵያ ተመልክተናል፡፡ በኢትዮጵያ የነበረው ተቃውሞ መጠንና አፈናውም እጅግ ያልተጠበቀ ነው፡፡ ይህ ዓመቱን ሙሉ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሆነ ነው፡፡ እንደምታውቀው በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ተገድለዋል፡፡ በአስርሺህዎች የሚቆጠሩ ታስረዋል፡፡ በ2016 በምስራቅ አፍሪካ በዚያ መጠን የተከሰተ የለም” ይላሉ፡፡  

በጎርጎሮሳዊው 2016  ኢትዮጵያ በሰብአዊ መብቶች ቀውስ ውስጥ መውደቋን የሚያትተው ዘገባው ዓመቱ የ“ጭካኔና የገደቦች” ነበር ሲል ጠንከር ባሉ ቃላት ገልጾታል፡፡ በዓመቱ ውስጥ በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ያስታወሰው ዘገባው በዚህ ወቅትም ሀገሪቱ “በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ ከፈተችው የሚለውን ደም አፋሳሽ አፈናን ቀጥላበታለች” ብሏል።

 

መንግስት በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ማሰሩን የሚያነሳው ዘገባው ከእነርሱ መካከል ጋዜጠኞች፣ ጦማሪዎች፣ ሙዚቀኞች፣ መመህራንና የጤና ባለሙያዎች እንደሚገኙበት ይገልጻል፡፡ “እንደበቀለ ገርባ ያሉ ለዘብተኛ የሚባሉ የፖለቲካ መሪዎች በሽብር ተከስሰው ወደ እስር ቤት ተወርውረዋል” ብሏል፡፡ ታስረው ከተፈቱት ውስጥ ብዙዎቹ በእስር ቤት ዉስጥ ስቃይ አንደደረሰባቸው መናገራቸውንም ይጠቅሳል። “ይህ እስረኞችን የማሰቃየት ችግር ኢትዮጵያ ዉስጥ ለረጅም ግዜ ሳይፈታ የዘለቀ ችግር ነው” ሲልም ዘገባው ይወነጅላል።

ሂዩማን ራይትስ ዎች መንግስት “በጸጥታ ሀይሎች ያደረሱትን በደሎች በተገቢው መልኩ ለመመርመርም ሆና ለዓለማቀፍ ምርመራ ጥሪዎች  መልስ መስጠት አልቻለም” ሲል ተችቷል፡፡ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም የተገደቡ መሰረታዊ መብቶች እንዲከበሩ ጠይቋል፡፡  መንግስት ለህዝብ ቅሬታዎች መልስ ይሰጥ ዘንድም ጥሪ አቅርቧል፡፡ ፌሊክስ ሆርን መንግስት በዓመቱ ውስጥ “ብዙ የማሻሻያ ጥሪዎች ቢቀርቡለትም የህዝቡን ጥያቄዎችን ማስተናገድ አልቻለም” ባይ ናቸው፡፡ 

“የሚቃወሙቱ በርካታ አሳማኝ ቅሬታዎች አሏቸው፡፡ መንግስት እነዚህን ቅሬታዎች ለመፍታት ዕድል ነበረው፡፡ ከሚቃወሙት እና ከማህበረሰቡ ጋር ተቀምጦ ቅሬታዎቹ ላይ መነጋገር ነበረበት፡፡ በዚህ ምትክ ያደረጉት ግን ተቃውሞዎችን ለመስበር ኃይልን መጠቀም ነው፡፡  ጥይት ተኮሰዋል፡፡ በጅምላ አስረዋል፡፡ድብደባ፣ ወከባ እና ማስፈራራትን ተጠቅመዋል፡፡ ለተቃውሞ የወጡትንም መጀመሪያ ጸረ-ሰላም ኃይሎች እያለ የጠራና በውጭ ባሉ ቡድኖች ተጽእኖ የሚደረግባቸው ናቸው ያለ ነው፡፡ እንደ ወንጀለኛ ነው እየተመለከታቸው የነበረው፡፡”

“ከጊዜ በኋላ መንግስት ጉዳዩን የመልካም አስተዳደር ችግር በሚል ማዕቀፍ ውስጥ አስቀምጦታል፡፡ ካነጋገርኳቸው በመቶዎች ከሚቆጠሩት የተቃውሞው ተሳታፊዎች አንዱም እንኳ ለተቃውሞ ያነሳሳቸው የመልካም አስተዳደር ችግር አሊያም ሙስና ነው ያለ የለም፡፡ መንግት ህብረተሰቡ ሰላማዊ ቅሬታውን የሚገልጽበት ምንም ዓይነት ዕድል አልሰጠም” ይላሉ የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ አጥኚው፡፡

ሂውማን ራይትስ ዎች የሚያወጣቸውን ዘገባዎች የኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ “መሰረተ ቢስ” ናቸው በሚል ሲያጣጥላቸው መቆየቱ ይታወሳል፡፡

 

ተስፋለም ወልደየስ

አርያም ተክሌ        

Audios and videos on the topic