በኢትዮጵያ የግል ባንኮች ላይ የወረደው ′ዱብ እዳ′ | ኤኮኖሚ | DW | 12.04.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኤኮኖሚ

በኢትዮጵያ የግል ባንኮች ላይ የወረደው 'ዱብ እዳ'

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያሳለፈው ውሳኔ ለግል ባንኮች 'ዱብ እዳ' ሆኖባቸዋል። ውሳኔው አስመጪ እና ላኪዎች ለሥራቸው የሚያሻቸውን የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት በግል ባንኮች ያላቸውን ተቀማጭ አሟጠው ወደ ንግድ ባንክ እንዲያዘዋውሩ ያደርጋል። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:53

በኢትዮጵያ የግል ባንኮች ላይ የወረደው 'ዱብ እዳ'

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከመጋቢት 9-23 ባሉት ቀናት አንድ ቢሊዮን ዶላር በውጭ ምንዛሪ ለንግድ ባንክ መስጠቱ ተሰምቷል። ከውሳኔው በኋላ አስመጪ እና ላኪዎች በግል ባንኮች የነበራቸውን ተቀማጭ ገንዘብ አሟጠው እያወጡ መሆኑን ዘርፉን በቅርበት የሚከታተሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በብሪታኒው የፖርቶቤሎ ኩባንያ የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ አብዱልመናን መሐመድ የብሔራዊ ባንክ ውሳኔ ከውጭ ምንዛሪ እጥረት እንደሚመነጭ ይናገራሉ። 
ከአንድ አመት በፊት የኢትዮጵያ መንግስት በተመሳሳይ መንገድ 2.3 ቢሊዮን ዶላር ለንግድ ባንክ መስጠቱን አቶ እየሱስወርቅ ዛፉ ያስታውሳሉ።። የሕብረት ባንክ የዲሬክተሮች ቦርድ ሊቀ-መንበር ሆነው የሚያገለግሉት አቶ እየሱስወርቅ የግል ባንኮች የቀደመው ውሳኔ ካሳደረባቸው ተፅዕኖ በአግባቡ ሳያገግሙ ተመሳሳይ እርምጃ መወሰዱ የብር እጥረት ፈጥሮባቸዋል ሲሉ ይናገራሉ። 


። ባለፉት አመታት የከፋው የንግድ ሚዛን ጉድለት፤ኢትዮጵያ ከውጭ አገራት የምታገኘው ብድር እና እርዳታ በድርቅ ምክንያት መቀነስ አገሪቱ ለገጠማት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ገፊ ምክንያት መሆናቸው ባለሙያዎች ይናገራሉ። የኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት ባለፍ አገደም የሚጠቃቅሱት የውጭ ምንዛሪ እጥረት አገሪቱ የምትከተለው ፖሊሲ ጭምር ተፅዕኖ እንዳለው ባለሙያዎች ይናገራሉ። የኢትዮጵያ የእድገት እና ለውጥ እቅድ (GTP) የመንግስት ፕሮጀክቶች 60 በመቶ ወጪ በውጭ ምንዛሪ የሚከፈል እንደሆነ ይገልጣል። የባንክ ባለሙያዎች ከመንግስት ግዢዎች የሚተርፈው የውጭ ምንዛሪ ለግሉ ዘርፍ በቂ አይደለም ሲሉ ይተቻሉ

ከአንድ አመት በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 2.3 ቢሊዮን ዶላር በውጭ ምንዛሪ ለንግድ ባንክ ሲሰጥ ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ ከግል ባንኮች መውጣቱን በቢዝነስ እና ኤኮኖሚ ላይ የሚያተኩረው አዲስ ፎርቹን ጋዜጣ ዘግቧል። የያኔው ውሳኔ በአዋሽ፤ወጋገን፤ሕብረት እና አቢሲኒያ ባንኮች ላይ የከፋ ተፅዕኖ አሳድሮ ነበር። ባንኮቹ እንዲህ አይነት የድንገቴ የብር እጥረት ሲገጥማቸው ጥሪታቸውን አስይዘው ከብሔራዊ ባንክ ለመበደር ይገደዳሉ። «በዱብ እዳ የሚወሰን ውሳኔ የግል ባንኮች ላይ ችግር እየፈጠረ ስለሆነ መንግስት» ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል የሚሉት አቶ አብዱልመናን የችግሩ ምንጭ የንግድ ባንክን የተቀማጭ መጠን ለማሳደግ የተደረገ ውሳኔ ሊሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬ አላቸው። 
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒሥትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ልዩ አማካሪ አቶ አርከበ እቁባይ ከዚህ ቀደም ለብሎንበርግ በሰጡት ቃለ-መጠይቅ የውጭ ምንዛሪ ክምችት እጥረቱ የተፈጠረው በፈጣኑ ኤኮኖሚያዊ እድገት ነው ሲሉ ተናግረው ነበር። አቶ አርከበ አገሪቱ የምትገነባቸው የማምረቻ ፓርኮች ሲጠናቀቁ ችግሩ ይቀረፋል የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል። ለበርካቶች በተለይ በግሉ ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሙያዎች እና

Kaffee Bauer in Äthiopien

የንግዱ ማሕበረሰብ ግን የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዲህ በአጭር ጊዜ ይፈታል የሚል እምነት የላቸውም። የግል ባንኮች ደንበኞቻቸውን "እባካችሁ ቼክ አትፃፉ" ብለው እስከ መማጸን መድረሳቸውን የሚናገሩት አቶ እየሱስወርቅ ዛፉ ተመሳሳይ ውሳኔ ተመልሶ ቢመጣ የተቋማቱ እጣ ፈንታ ያሳስባቸዋል። 

ኢትዮጵያ በጎርጎሮሳዊው 2015/2016 የበጀት ዓመት ከውጭ ንግድ 4 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ብታቅድም አልተሳካላትም። የኢትዮጵያ ንግድ ሚኒሥቴር እንዳስታወቀው አገሪቱ በጎርጎሮሳዊው 2014/15 የበጀት አመት 3 ቢሊዮን ዶላር ስታገኝ በአመቱ በ139 ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ አሳይቷል።  አቶ አብዱልመናን የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን ለመፍታት ሁነኛው መፍትሔ የገቢ እና ወጪ ንግዷን ማጣጣም እንደሆነ ይናገራሉ። እስከዚያው ግን መንግሥት የሚወስናቸው ውሳኔዎች ጥንቃቄ ሊደረግባቸው እንደሚገባ የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ይመክራሉ። 

እሸቴ በቀለ
ኂሩት መለሰ 

Audios and videos on the topic