በኢትዮጵያ የዋጋ ንረት 40% ሊደርስ ይችላል - የተ.መ.ድ. | ኤኮኖሚ | DW | 05.08.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኤኮኖሚ

በኢትዮጵያ የዋጋ ንረት 40% ሊደርስ ይችላል - የተ.መ.ድ.

የተባበሩት መንግሥታት የኮሮና ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ሊያሳድር የሚችለውን ማሕበራዊ እና ምጣኔ ሐብታዊ ጫና በተነተነበት ሰነድ የምግብ ዋጋ ግሽበት በሚቀጥሉት አምስት ወራት 40% ሊደርስ እንደሚችል ጥቆማ ሰጥቷል። እንዲህ አይነት የዋጋ ንረት በኢትዮጵያ የታየው ከአስራ ሁለት አመታት በፊት የነዳጅ ዋጋ በዓለም ገበያ ሲያሻቅብ ነበር።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 13:10

የኮሮና ወረርሽኝ መለስተኛ ከሆነ የዋጋ ግሽበት እስከ 30% ሊደርስ እንደሚችል የተ.መ.ድ. ትንታኔ ያሳያል

በኢትዮጵያ የሐምሌ ወር የዋጋ ግሽበት ወደ 22.3 በመቶ አሻቅቧል። የኢትዮጵያ ስታስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ እንደሚያሳየው የምግብ ዋጋ ግሽበት 24.9 በመቶ ሲደርስ ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች የዋጋ ግሽበት 18.9 በመቶ ደርሷል።

የኢትዮጵያ ስታስቲክስ ኤጀንሲ በሐምሌ ወር "አብዛኛዎቹ የእህል ዓይነቶች እና አትክልት ጭማሪ ያሳዩ ሲሆን ለምግብ ዋጋ ግሽበት መጨመር ከፍተኛ አሰተዋጽዖ አላቸው። አትክልት (በተለይም ቀይ ሽንኩርት፣ ድንች እና ቲማቲም) ፈጣን የዋጋ ጭማሪ አስመዝግበዋል። የበርበሬ ዋጋ በዚህ ወርም እንዳለፉት ወራት በተከታታይ እየጨመረ ነው" ብሏል። በመረጃው መሠረት የምግብ ዋጋ ግሽበት ባለፈው ሰኔ ወር ከነበረበት የተወሰነ ጭማሪ ሲያሳይ ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች ዋጋ ግሽበት በአንፃሩ ቅናሽ አሳይቷል።

የተባበሩት መንግሥታት የኮሮና ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ሊያሳድር የሚችለውን ማሕበራዊ እና ምጣኔ ሐብታዊ ጫና በተነተነበት እና ባለፈው ግንቦት ይፋ ባደረገው ጥናት ግን በተለይ የምግብ ዋጋ ግሽበት በሚቀጥሉት አምስት ወራት ሊጨምር እንደሚችል ጥቆማ ሰጥቷል። የድርጅቱ የኢትዮጵያ ቢሮ ትንታኔ ኮሮና በአገሪቱ ሊስፋፋ የሚችልበትን ፍጥነት፤ ወረርሽኙን ለመቋቋም ገቢራዊ የሚደረጉ ክልከላዎችን ክብደት፤ የበረሐ አንበጣ መንጋ እና የውጭ ምንዛሪ ተመን የሚደርስበትን ጫና ከግምት ውስጥ በማስገባት በሶስት ሁኔታዎች የተከፋፈለ ነው።

በትናንታኔው መሠረት ኮሮና በኢትዮጵያ እጅግ ከከፋ እና ወረርሽኙን ለመከላከል ተግባራዊ የሚደረጉ እርምጃዎች ከጠነከሩ የምግብ ዋጋ ግሽበት እስከ 40 በመቶ ሊያሻቅብ ይችላል። ይኸ ሶስተኛው እና አስከፊው ኹኔታ ሊከሰት የሚችለው በወር በኮሮና የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከ30 ሺሕ በላይ ካሻቀበ እና በመላ አገሪቱ ጠበቅ ያሉ ገደቦች ሥራ ላይ ከዋሉ ነው። የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ አብዱልመናን መሐመድ እንደሚሉት ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የባሰ ገጥሟት ቢያውቅም የዋጋ ግሽበቱ የተባበሩት መንግሥታት ሰነድ ባለው መጠን ከጨመረ ፈታኝ መሆኑ አይቀርም።

Äthiopien | Traditioneller Markt in Debre Markos

በኢትዮጵያ ስታስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ መሠረት ቀይ ሽንኩርት፣ ድንች እና ቲማቲም በሐምሌ ወር ዋጋቸው ጨምሯል

"በኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ከ40 በመቶ በላይም የዋጋ ግሽበት ተከስቶ ያውቃል። በጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር በ2008 ዓ.ም. በአንድ ወር ከነዳጅ ዋጋ መጨመር ጋ በተያያዘ እስከ 62 በመቶ የዋጋ ግሽበቱ ወጥቷል" የሚሉት አቶ አቶ አብዱልመናን ኢትዮጵያ ለእንዲህ አይነቱ የዋጋ ግሽበት እንግዳ እንዳልሆነች መለስ ብለው ያስታውሳሉ። ይሁንና "አሁን ባለው የኑሮ ውድነት ላይ 40 በመቶ ቢወጣ እንደዚህ አይነት ጭማሪ ማሳየቱ በጣም ከባድ ነው የሚሆነው። ባለፈው አስር አመት ውስጥ ካየንው ከፍተኛው ይሆናል። ቀላል አይደለም" በማለት የበረታ ጫና ሊኖረው እንደሚችል ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት ከአመት አመት ጭማሪ ቢያሳይም እጅግ ከፍተኛ በሆነ መጠን የናረው ከአስራ ሁለት አመታት ገደማ በፊት በዓለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ ባሻቀበበት ወቅት ነበር። በወቅቱ የግሽበቱ ዋንኛ ገፊ ምክንያት በዓለም ገበያ የታየው ንረት ወደ ኢትዮጵያ መዛመቱ ነው።

የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ አብዱልመናን የኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት 40 በመቶ ሊደርስ የሚችልበት ዕድል ውስን እንደሆነ ያምናሉ። ቢሆንም የኮሮና ወረርሽኝ ሊያሳድር በሚችለው ጫና፤ አለመረጋጋት በበረታበት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ጠባይ እንዲሁም የብር መዳከም ተደራርበው በሚያስከትሉት ጫና እስከ የዋጋ ግሽበት እስከ 30 በመቶ ሊደርስ እንደሚችል ያስረዳሉ።

አቶ አብዱልመናን "ያለፉትን ወራቶች ብናይ የዋጋ ግሽበቱ በተከታታይ ከ20 በመቶ በላይ ነው። የመካከለኛውን ሲናሪዮ እንኳ ብንወስድ ወደ 30 በመቶ አይሆንም ለማለት ይከብዳል። ለምን የፖለቲካውም ኹኔታ አለ። የኮሮናም ተጽዕኖ ይኖራል። የብር ፈጣን የሆነ መዳከም ስላለ ከውጪ የሚገቡት ዕቃዎች ላይ ተጽዕኖ ስላለው ይኸም በቀጥታ የምግብ ዋጋም ላይ ይንጸባረቃል። እነዚህ ጉዳዮች ከግንዛቤ ውስጥ ሲገቡ ምን አልባት ወደ 30 በመቶ ሊቃረብ ይችላል የሚል እምነት አለኝ። 40 የሚለው ግን እጅግ አስከፊ ኹኔታ ከተፈጠረ ሊሆን የሚችል ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

የአቶ አብዱልመናን ዕይታ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኮሮና ወረርሽኝ በኢትዮጵያ የሚስፋፋበት ፍጥነትን በተመለከተ ካስቀመጠው ሁለተኛ ትንታኔ ጋር የተስማማ ነው። ሁለተኛው በወር በኮሮና የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከ10 ሺሕ እስከ 15 ሺሕ ደርሶ ጠንከር ያለ ወረርሽኝ ከተከሰተ የሚል ሥሌት ነው። በዚህ ሥሌት የወረርኙን ፍጥነት ለመግታት ገቢራዊ የሚደረጉ ገደቦችም ጠንከር ስለሚሉ በኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት ላይ የሚኖረው ጫና ከፍ ይላል። የበረሐ አንበጣ መንጋ ወረርሽኝን ጨምሮ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ገቢራዊ በሚደረጉ የተራዘሙ ክልከላዎች በሚፈጠር የአቅርቦት መስተጓጎል፤ የምንዛሪ ግብይቱ በሚደርስበት ጫና የምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች የዋጋ ንረት እስከ 30 በመቶ ከፍ ሊል ይችላል። 

ትንታኔው በወር በኮሮና የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከ5,000 በታች ከሆነ ወረርሽኙን ለመከላከል ገቢራዊ የሚደረጉ ገደቦች ምጣኔ ሐብታዊ ጫናም አነስተኛ የሚሆንበትን የመጀመሪያ ሁኔታ አስቀምጧል። በኮሮና የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ድርጅቱ ባስቀመጠው ልክ ዝቅ ካለ እና ወረርሽኙን ለመገደብ የሚደነገጉ ገደቦች ላላ ካሉ የምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች የዋጋ ንረት አሁን ከሚገኝበት 25 በመቶ መጨመሩ እንደማይቀር የተባበሩት መንግሥታት የትንተና ሰነድ ይጠቁማል። እንደሌሎቹ ሁለት ኹኔታዎች ሁሉ የበረሐ አንበጣ መንጋ፤ በምንዛሪ ተመን ላይ በሚፈጠር ጫና እንዲሁም በአቅርቦት ላይ የሚፈጠር መስተጓጎል ለዋጋ ንረቱ ተጨማሪ ገፊ ምክንያቶች ይሆናሉ።

በዓለም አቀፍ የምርት ሰንሰለትም ይሁን የግብይት ሥርዓት ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳደረው የኮሮና ወረርሽኝ በኢትዮጵም የዋጋ ግሽበትን ጨምሮ የተለያዩ ምጣኔ ሐብታዊ ዳፋዎች ሊያስከትል እንደሚችል የተለያዩ ተቋማት እና ባለሙያዎች በተከታታይ የሰሯቸው ጥናቶች ይጠቁማሉ። አቶ አብዱልመናን በኢትዮጵያ ገበያ ባለፉት አምስት ወራት ገደማ የኮሮና ወረርሽኝ ከ2 እስከ 5 በመቶ የዋጋ ንረት ሳያስከትል እንዳልቀረ ይገምታሉ። ባለሙያው እንደሚሉት በአገሪቱ ለሚታየው የዋጋ ንረት ብቸኛው መንስኤ ግን ወረርሽኙ ብቻ አይደለም።

Äthiopien Traditioneller Markt in Debre Birhan

የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ አብዱልመናን መሐመድ የኮሮና ወረርሽኝ ከ2-5 በመቶ የዋጋ ንረት ሳያስከትል እንዳልቀረ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል

"ተጽዕኖውን ይኸ ነው ብሎ ለማስቀመጥ ያስቸግራል። ነገር ግን ካለፈው ሁለት አመት ጀምሮ ያየን እንደሆነ የዋጋ ንረት በጣም ጨምሯል። የኢትዮጵያ የዋጋ ንረት ዋንና ችግር የነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት ነው። ባለፉት አራት እና አምስት ወራት ደግሞ ከሶስት እስከ አምስት በመቶ አካባቢ የዋጋ ንረቱ ጨምሯል። ኮሮና አንድ ተጽዕኖ ይኖረዋል ግን ከዚያም ባሻገር የመገበያያ ገንዘብ መዳከም መታሰብ አለበት። እነዚህ ነገሮች በአንድ ላይ ነው የመጡት። የመገበያያ ገንዘብ መዳከም በተለይ ባለፉት ስምንት ወራት አካባቢ ቀላል አይደለም። የእሱም ተፅዕኖ አለ። ችግሮች ተደራርበው ስለመጡ የዋጋ ንረቱ ባስ ብሏል። ኮሮናውም ጫና የለውም ማለት ይከብዳል። ከሁለት እስከ አምስት በመቶ ያለው የእሱ ጫና ሊሆን ይችላል" ብለዋል አቶ አብዱልመናን።

ከሁለት ሳምንታት ገደማ በፊት በአዲስ አበባ በተካሔደ ውይይት ላይ የገንዘብ ምኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ የዋጋ ንረት ለመንግሥታቸው ኹነኛ ፈተና እንደሆነ ተናግረዋል። አቶ አሕመድ "በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዋጋ ግሽበት፣ የኑሮ ውድነት ከፍተኛ ጫና በሕዝባችን ላይ እያስከተለ ይገኛል። በኤኮኖሚው ላይም ከፍተኛ የሆነ ማክሮ ኢምባላንስ እያመጣ ይገኛል። ስለዚህ ይኸን ጉዳይ መቆጣጠር እና ወደ ነጠላ አሀዝ እንዲሆን ማድረግ አንዱ የትኩረት አቅጣጫ ነው" ብለው ነበር።

መንግሥት የዋግ ግሽበትን በነጠላ አሀዝ ለመወሰን በተደጋጋሚ ቃል ሲገባ ቢቆይም የሠመረ አይመስልም። የኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተሳተፉበት እና በ10 አመታቱ የምጣኔ ሐብት ዕቅድ ላይ በተደረገ ውይይት የብሔራዊ ባንክ ገዢ ይናገር ደሴ መንግሥታቸው የዋጋ ንረትን በመቆጣጠር ረገድ ሳይሳካለት መቆየቱን ተናግረዋል።

አቶ ይናገር "ባለፉት አስር አመታት የኢትዮጵያ የዋጋ ንረት በአማካይ ከ15 በመቶ በላይ ሆኖ ነው የቆየው። የአምስት አመት መርኃ ግብሮች ስናዘጋጅ ወደ ነጠላ አሀዝ እናወርዳለን የሚል በተደጋጋሚ የሚቀመጥ ግብ ነበር። ሆኖም ግን ይኸ ሆኖ አይታይም" ሲሉ መንግሥታቸው ያቀደውን ማሳካት እንደተሳነው አምነዋል።

"የዋጋ ንረት የተለያዩ ምክንያቶች አሉት። አንደኛው ለዋጋ ንረት መጨመር የሞነተሪ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ሁለተኛው ደግሞ ከሞነተሪ ውጪ የሆኑ ሌሎች ምክንያቶች የዋጋ ንረትን ሊያስከትሉ ይችላሉ። ለምሳሌ ከአምራቹ ዘርፍ አኳያ የምርት እና ምርታማነት ኹኔታ ከተዛባ ወይ በበቂ መጠን ካልቀረበ ወይም አንዳንዴ ምርቱም ተመርቶ በአግባቡ ካልተጓጓዘ እና እጥረት ካጋጠመ የዋጋ ንረት ሊከሰት ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከአቅም በላይ በሆኑ የጸጥታ፣ የኹከት፣ የግርግር ኹኔታዎች ሲያጋጥሙ እንደዚሁ ለዋጋ ንረት መባባስ እንደ ጊዜያዊ መነሻ ሊሆኑ ይችላሉ" ብለዋል የብሔራዊ ባንክ ገዢው።

Yinager Dessie Belay, äthiopischer Nationalplanungskommissar

"ባለፉት አስር አመታት የኢትዮጵያ የዋጋ ንረት በአማካይ ከ15 በመቶ በላይ ሆኖ ነው የቆየው። የአምስት አመት መርኃ ግብሮች ስናዘጋጅ ወደ ነጠላ አሀዝ እናወርዳለን የሚል በተደጋጋሚ የሚቀመጥ ግብ ነበር። ሆኖም ግን ይኸ ሆኖ አይታይም" የብሔራዊ ባንክ ገዢ ይናገር ደሴ

የኢትዮጵያ መንግሥት ላለፉት አስርት አመታት የተከተለው አሰራር የዋጋ ንረትን የሚፈጥር እንደነበር የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ አብዱልመናን ያስረዳሉ። በብድር እና ብር በማተም የተነቃቃው የኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብታዊ ዕድገት ለዋጋ ንረት ዋንኛ ገፊ ምክንያት መሆኑን የሚያስታውሱት አቶ አብዱልመናን የማምረት አቅም ሳይጠናከር በቁጥጥር ሥር የመዋሉ ነገር እንደማይታሰብ ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል።

"ላለፉት አስር እና አስራ አምስት አመታት የተከተልንው የኤኮኖሚ ፖሊሲ በምንድነው ፋይናንስ የተደረገው ነው? የመንግሥት መሠረተ ልማት ሰፍቷል፤ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሰፍተዋል፤ እንደዚሁም የግለሰብ ኢንቨስትመንት በጣም ሰፍቷል። የዋጋ ንረቱ አንደኛው ምክንያት ይኸ የኤኮኖሚ ዕድገት የመጣበት መንገድ ነው። በዋናነት ከውጪ፤ ከሀገር ውስጥ የተበደርንው እንደዚሁም ደግሞ ብር በማተም የመጣ ነው። ከምግብ ጀምሮ ለሸማች የሚሆኑ ዕቃዎች የማምረት አቅም በደንብ ሳያድግ ፍላጎት ጨምሯል። ስለዚህ ከአስር እስከ አስራ አምስት አመታት ያለው የዋጋ ንረት በዚህ መልኩ የተከሰተ ነው" ሲሉ ሥረ መሰረቱን አስረድተዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰራው ትንታኔ በሚቀጥሉት አምስት ወራት ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ የምታቀርባቸው ምርቶች እና አገልግሎቶች ከ25-30% ሊቀንሱ እንደሚችሉ ጥቆማ ሰጥቷል። አገሪቱ የምትሸምተው ነዳጅ ሊቀንስም ይችላል። ኢትዮጵያ ባለፈው አመት የ2.6 ቢሊዮን ዶላር ነዳጅ ከዓለም ገበያ የገዛች ሲሆን በተባበሩት መንግሥታት ጥናት መሠረት ይኸ በጎርጎሮሳዊው 2020 ዓ.ም. ወደ 1.3 ቢሊዮን ዶላር ዝቅ ሊል ይችላል።  ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ የሚላከው የገንዘብ መጠንም ከ30-50% ይቀንሳል። ይኸ ከ1.71 እስከ 2.85 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ቅናሽ ማለት ነው። 

በተለይ የዋጋ ንረት መባባስ መደበኛ ባልሆነው የኤኮኖሚ ዘርፍ ተሰማርተው የዕለት ጉርሳቸውን በሚያበስሉ ዜጎች ላይ ሊያሳድር የሚችለው ጫና በርካቶችን የሚያሳስብ ሆኖ ይታያል። እንደ ግንባታ ባሉ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ እና በከተሞች አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች ኮሮና ከሌሎች ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሐብታዊ ምክንያቶች ተደራርቦ የሚያስከትለው የዋጋ ንረት ሊበረታባቸው ይችላል። አቶ አብዱልመናን እንደ ገጠሩ ሁሉ በከተሞች ሊቸገሩ የሚችሉ ዜጎችን ለመርዳት የሴፍቲኔት መርሐ ግብሮች እንደሚያስፈልጉ ተናግረዋል።

"ነገሩን በጣም ከበድ የሚያደርገው ሥራ ሳይኖር፤ ወይም ሥራ ተቀዛቅዞ ኑሮ ሲወደድ ጫናው ታች ያለው፤ ገቢው ዝቅ ያለ የሕብረተሰብ ክፍል ላይ ጠንከር ያለ ስለሚሆን መንግሥት ሊያደርግ የሚችለው የከተማ ሴፍቲኔቶች ካሉ በምግብ መልኩ መርዳት ይቻላል። ሁለተኛው ከዓለም ባንክ፣ ከዓለም የገንዘብ ድርጅት እንደዚሁም የልማት አጋር ከሚባሉት አገሮች ዕርዳታ በመጠየቅ ከተማ አካባቢ በይበልጥ ዝቅተኛ ገቢ ያለው የሕብረተሰብ ክፍል ስለሚጎዳ እሱን በተለያየ የሴፍቲኒት ፕሮግራም ለመርዳት ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል" ብለዋል።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ

 

 

Audios and videos on the topic