በኢትዮጵያ የካንሰር ተጠቂዎች ቁጥር ጨምሯል | ጤና እና አካባቢ | DW | 22.10.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

በኢትዮጵያ የካንሰር ተጠቂዎች ቁጥር ጨምሯል

ተላላፊ በሽታዎች በግንባር ቀደምትነት ያሳስቧት በነበረችው ኢትዮጵያ ውስጥ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የካንሰር ታማሚዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን መረጃዎች ያመለክታሉ። በተለይ የጡት ካንሰር ዕድሜያቸው በወጣትነት ክልል ውስጥ የሚገኙ ሴቶች ላይ በዝቶ መታየቱን አንድ የዘርፉ የህክምና ባለሙያ ገልጸዋል። ወንዶችም እንዲሁ የዚህ ካንሰር ተጠቂዎች ናቸው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:34

«ከጡት ካንሰር ተጠቂዎች ሴት ወጣቶች ይበረክታሉ»

ኢትዮጵያ ውስጥ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በጡት ካንሰር የሚያዙም ሆነ ሕይወታቸው የሚያልፍ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሄዱን ዶክተር ቢንያም ተፈራ ከጎርጎሪዮሳዊው 2016 እስከ 2017 ባሉት ጊዜያት ያካሄዱት ጥናት ያመለክታል። ከጠቅላላው ሕዝብ ከአምስቱ አንዱ፤ ከሦስት ሴቶች ደግሞ አንዷ ለዚህ በሽታ የተጋለጡ መሆናቸውን ይኸው ጥናት ጠቅሷል። ጥናቱን ያካሄዱት ዶክተር ቢንያም ካንሰር በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የጤና ችግር እየሆነ መምጣቱን ይናገራሉ።

«እንግዲህ በኢትዮጵያ ውስጥ በአጠቃላይ ከሚፈጠረው የካንሰር መጠን ወደ 33 ከመቶ የሚሆነው የጡት ካንሰር ነው። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ በፊት ተላላፊ በሆኑ በሽታዎች ነበረ በጣም የምትታወቀው ትልቁም የጤና አቅጣጫ ወደዚያ ነበረ። አሁን ግን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በተለይም እንደነካንሰር ያሉት በጣም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመሩ ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው።»

Krebs Krebszelle Illustration Symbolbild

የካንሰር ሴል

ምንም እንኳን የዶክተር ቢንያም ጥናት ጎንደር ላይ ቢያተኩርም የካንሰር ታማሚዎች ይዞታ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎችም ተመሳሳይ ነው ይላሉ። ቀደም ሲል የበለፀጉት ሃገራት በሽታ ተደርጎ ይታይ የነበረው ካንሰር አሁን ኢትዮጵያን ጨምሮ በድሀ እና በአዳጊ ሃገራት ሁሉ ተበራክቶ መታየቱ የችግሩን አሳሳቢነት እንዳጎላው ነው የሚነገረው። ከሰሞኑ ጋና ውስጥም በርካታ ሴቶች እና ወንዶች የበሽታውን አሳሳቢነት በመረዳት ለምርመራ ወደሀኪም ዘንድ መሄዳቸውን የዶቼ ቬለ ዘጋቢዎች ከስፍራው የላኳቸው መረጃዎች ያመለክታሉ። ካንሰር ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ሊደርስ የቻለበት ምክንያት ራሱን ችሎ ጥናት ሊደረግበት እንደሚገባ ነው ተመራማሪው የሚገልፁት።

«በጥቅሉ ካንሰር መነሻው ይሄ ነው ተብሎ በትክክል መናገር ይከብዳል። ነገር ግን የካንሰር ተጋላጭነት መጠንን የሚጨምሩ ነገሮች ግን የታወቁ አሉ። ለምሳሌ በዘር የሚተላለፍ ሊሆን ይችላል፣ በዚያ ላይም ደግሞ ምናልባት ረዥም የሆነ የሆርሞን ተጋላጭነት ሊኖር ይችላል፤ በተለይ በዕድሜ የወር አበባ ቶሎ መምጣት እንደዚሁም ዘግይቶ መመለስ፤ ውፍረት ሊሆን ይችላል ሲጋራ ማጨስ ሊሆን ይችላል፤ እንደዚሁም በኬሚካሎች ፣ የአካል እንቅስቃሴ አለመሥራት፤ የሚባሉ ነገሮች የጡት ካንሰር ተጋላጭነት የሚጨምሩ ናቸው። ግን ኢትዮጵያ ላይ ያለው ነገር ካለው ሳይንስ ካወቀው ነገር ለየት ይላል።»

Symbolbild Brustkrebsvorsorge

በዓመት አንዴ ለማድረግ የሚመከረው የማሞግራፊ ምርመራ

የጡት ካንሰር በተለይ ሴቶች ላይ ቢበረክትም ወንዶችም ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ነው የሚነገረው። በጉዳዩ ላይ በተለያዩ ጊዜያት ያነጋገርናቸው ኢትዮጵያውያን የካንሰር ከፍተኛ ሀኪሞች እንደሚሉት ታማሚዎች ወደሃኪም ዘንድ የሚሄዱት በሽታው ስር ከሰደደ በኋላ መሆኑ ታክሞ የመዳን ዕድልን ያሳንሳል። ዶክተር ቢንያምም ሰዎች ራሳቸውን በግላቸው እየመረመሩ የተለየ ነገር ሲያስተውሉ ቶሎ ወደሀኪም ቤት እንዲሄዱ ነው የሚመክሩት።በተለይ ህክምናን የሚማሩ የወደፊት ሀኪሞች በትምህርታቸው ላይ ይህ ትኩረት ተሰጥቶት ስልጠና እንዲወስዱም ይመክራሉ። ኅብረተሰቡ ይህን የጤና ችግር እንዲረዳም በመገናኛ ብዙሃን የሚቀርቡ መረጃዎችን ጨምሮ ለቅስቀሳ የሚሆኑ መንገዶችን ሁሉ መጠቀም እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።

የዓለም የጤና ድርጅት በየዓመቱ በመላው ዓለም በጡት ካንሰር ምክንያት 458 ሺህ ሰዎች እንደሚሞቱ ያመለክታል። 1.3 ሚሊዮን ሰዎችም በበሽታው ይያዛሉ። ለሰጡን ማብራሪያ የካንሰር ከፍተኛ ሀኪም ዶክተር ቢንያም ተፈራን በማመስገን ለዕለቱ ያልነውን በዚሁ እናብቃ።

ሸዋዬ ለገሠ

ተስፋለም ወልደየስ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች