በኢትዮጵያ የአጎዋ ዕድል ላይ የተነሳው የአሜሪካ ጥያቄ ማንን ይጫናል? | ኤኮኖሚ | DW | 15.09.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኤኮኖሚ

በኢትዮጵያ የአጎዋ ዕድል ላይ የተነሳው የአሜሪካ ጥያቄ ማንን ይጫናል?

ኢትዮጵያ ለሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መፍትሔ ካልተበጀ በአጎዋ ያለ ቀረጥ ምርቶቿን ለአሜሪካ ገበያ የማቅረብ ዕድሏን ልታጣ እንደምትችል የአሜሪካ ባለሥልጣን አስጠንቅቀዋል። አሜሪካ ይኸን እርምጃ ከወሰደች ባለሙያዎች እንደሚሉት ምርቶቻቸውን ከሚልኩ ኩባንያዎች በተጨማሪ በአገሪቱ የሥራ ፈጠራና ድህነት ቅነሳ መርሐ ግብሮች ላይ ጫና ይኖረዋል

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:26

በኢትዮጵያ የአጎዋ ዕድል ላይ የተነሳው የአሜሪካ ጥያቄ ማንን ይጫናል?

የአሜሪካ የንግድ ተወካይ ካትሪን ታይ ከኢትዮጵያ ዋና የንግድ ተደራዳሪ ማሞ ምህረቱ ጋር ባለፈው ነሐሴ ባደረጉት ውይይት በኢትዮጵያ በቀጠለው ግጭት እና ሰብዓዊ ቀውስ ዓለም አቀፍ እውቅና የተሰጣቸው ሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እልባት ካልተበጀለት አገሪቱ ወደፊት በአፍሪካ የዕድገት እና ዕድል ድንጋጌ (African Growth and Opportunity Act) በኩል ያላት ተጠቃሚነት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል መናገራቸውን መሥሪያ ቤታቸው ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። 

የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከፍተኛ አማሪ እና የኢትዮጵያ የንግድ ተደራዳሪ የሆኑት ማሞ ምህረቱ በትዊተር ባሰፈሩት መልዕክት ከካትሪን ታይ ጋር "ገንቢ እና ግልጽ ውይይት" ማድረጋቸውን ገልጸዋል። ማሞ በዚሁ የትዊተር መልዕክታቸው ኢትዮጵያ እና አሜሪካ ጠንካራ የሁለትዮሽ የንግድ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸው አጎዋ በአስር ሺሕዎች የሚቆጠሩ በማምረቻው ዘርፍ የሚገኙ ሥራዎችን እንደሚደግፍ እና ከዚህ መካከል 80 በመቶው በሴቶች የተያዙ መሆናቸውን አስፍረዋል። 

አጎዋ የተወሰኑ የብቃት መሥፈርቶች የሚያሟሉ ከሰሐራ በርሐ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገራት ሸቀጦቻቸውን ቀረጥ ሳይከፍሉ በአሜሪካ ገበያ እንዲሸጡ የሚፈቅድ የግብይት ሥርዓት ነው። ይኸን የግብይት ዕድል በመጠቀም ከምሥራቅ አፍሪካ አገራት ኢትዮጵያ ኬንያን በመከተል በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ የአሜሪካ የንግድ ኮሚሽን በጎርጎሮሳዊው መጋቢት 2020 ዓ.ም. ይፋ ያደረገው ሰነድ ያሳያል። 

አጎዋ ለኢትዮጵያ የውጭ ንግድ ከፈጠረው ገበያ ባሻገር ከሌሎች አገሮች የባለወረቶችን ቀልብ እንድትስብ አድርጓታል። የውጭ ባለወረቶች ከሚያገኟቸው ማበረታቻዎች ባሻገር ለኢትዮጵያ በተፈቀደው የቀረጥ ነጻ ዕድል መሠረት ምርቶቻቸውን ለአሜሪካ ገበያ ማቅረብ መቻላቸው ለመዋዕለ-ንዋይ አገሪቱን እንዲመርጡ የሚያበረታታ ነው። 

መቀመጫውን በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ባደረገው የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት የሚያገለግሉት የምጣኔ ሐብት ባለሙያው ዶክተር ውበት ካሳ ለዶይቼ ቬለ እንደ ተናገሩት በኢትዮጵያ የአጎዋ ተጠቃሚነት ላይ የተነሳው ጥያቄ ወደ ተጨባጭ እርምጃ ከመሸጋገሩም በፊት በእንዲህ አይነቱ መዋዕለ ንዋይ ላይ ጭምር ተጽዕኖ ያሳድራል። 

ዶክተር ውበት "ባለወረቶች የረዥም ጊዜ መዋዕለ-ንዋይ ወይም [ምርቶቻቸውን] ወደ ውጪ ለመላክ፤ ፋብሪካ ለማቋቋም ሲያስቡ ስለ ወደፊቱ እርግጠኝነትን መፍጠር ይፈልጋሉ። ስለዚህ ይኸ አጎዋ ወደ ፊት የመነሳት ሥጋቱ በራሱ ባለወረቶች ላይ ተጨማሪ የሥጋት ምንጭ ነው ማለት ነው" ሲሉ አስረድተዋል። 

ኢትዮጵያ 525 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ሸቀጦች በጎርጎሮሳዊው 2020 ዓ.ም. ወደ አሜሪካ ልካለች።  ኢትዮጵያ በአጎዋ ባላት ተጠቃሚነት ወደ አሜሪካ ከምትልካቸው ሸቀጦች በተለይ የጨርቃ ጨርቅ እና የቆዳ ውጤቶች ዕድገት ማሳየታቸውን በዩናይትድ ኪንግደም የሌስተር ደ ሞንትፎርት ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ኤኮኖሚና የሕግ ፕሮፌሰሩ መላኩ ጎብዬ ይናገራሉ። ፕሮፌሰር መላኩ እንደሚሉት አሜሪካ ጨክና ኢትዮጵያ በአጎዋ በኩል የምታገኘውን የግብይት ዕድል ከከለከለች ችግር መፍጠሩ አይቀርም። 

ፕሮፌሰር መላኩ "በተለይ በቅርቡ በጣም እያደገ የሔደ የተወሰኑ የኤኮኖሚው ዘርፎች ላይ አለ። ለምሳሌ ከጫማ ጀምሮ የቆዳ ውጤቶች ወደ አሜሪካ የሚልኩ ኩባንያዎች አሉ። በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ውስጥ በርከት ያሉ አሉ። ኢትዮጵያ የአጎዋ ተጠቃሚ መሆኗ በአጭር ጊዜ ውስጥ እነዚህ ኩባንያዎች አማራጭ ገበያ ሳያገኙ ቢቋረጥ ለብዙዎቹ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል መገመት ይቻላል" ብለዋል። 

ኢትዮጵያ በአጎዋ በኩል ያላትን ዕድል ብታጣ ለአሜሪካ ገበያ ሸቀጦቻቸውን የሚልኩ ኩባንያዎች ላይ የመጀመሪያው ዳፋ እንደሚያርፍ ዶክተር ውበት ይስማማሉ። የምጣኔ ሐብት ባለሙያው እንደሚሉት ተጽዕኖው ግን በኩባንያዎቹ ላይ ብቻ ተወስኖ የሚቀር አይሆንም።

"በዋናነት የሚጎዳው በጨርቃ ጨርቅ እና በተዛማጅ ዘርፎች ውስጥ የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎች ናቸው። ኢትዮጵያ በቅርቡ ከፍ ያለ የውጭ ኢንቨስትመንት እያስመዘገበች ያለበት ዘርፍ ነው። በተለይ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በዋነኝነት የተሳተፉበት ለውጭ ዕቃን በማምረት ላይ ስለሆነ እነዚህ ዘርፎች ተጽዕኖ ያርፍባቸዋል። እነዚህ ዘርፎች ተጽዕኖ ውስጥ ሲወድቁ ደግሞ ብዙ በእነዚህ ዘርፎች የተሰማሩ [ሰዎች] የሥራ ማጣት፤ የውጭ ንግድ የአገሪቱን የዕድገት ሁኔታ፤ የአገሪቱ ድህነት የመቀነስ መርሐ-ግብር የሚያፋጥን ስለሆነ ይኸም የአገሪቱን የዕድገት፣ የሥራ ፈጠራ ዕቅድ፣ የድህነት ቅነሳ መርሐ-ግብር  በአሉታዊ መንገድ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። የውጭ ምንዛሪ የማግኘት አቅምንም ሊቀንስ ይችላል" በማለት ድምጽ ዶክተር ውበት አስረድተዋል። 

የአጎዋ ቅድመ-ሁኔታዎች

የአጎዋ ዕድል ተጠቃሚ አገሮች ማሟላት የሚጠበቁባቸው በርከት ያሉ ቅድመ-ሁኔታዎች ይገኛሉ። አገራቱ ገበያ መር የኤኮኖሚ ሥርዓት የሚከተሉ፣ የሕግ የበላይነት የሚከበርባቸው፣ የፖለቲካ ሥርዓታቸው ብዝኃነትን የሚቀበል ሊሆን ይገባል። ወይም ወደዚያ እያመሩ የሚገኙ መሆን አለባቸው። ከዚህ በተጨማሪ መንግሥታቱ የግለሰቦችን ሕጋዊ መብቶች ማክበር ይጠበቅባቸዋል። ለአሜሪካ ንግድ እና መዋዕለ-ንዋይ መሰናክሎችን ማስወገድ፣ ድህነትን ለመቀነስ ያለመ የኤኮኖሚ ፖሊሲ መከተል፣ ሙስና እና ጉቦን ለመዋጋት የተወጠነ ሥርዓት መዘርጋት እና ዓለም አቀፍ እውቅና የተሰጣቸው የሰራተኞች መብቶችን መጠበቅ ከቅድመ-ሁኔታዎቹ መካከል ይገኙበታል። አገራቱ የአሜሪካን ብሔራዊ ደሕንነት እና የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ፍላጎት በሚያደናቅፉ እንቅስቃሴዎች መሳተፍም ሆነ ዓለም አቀፍ እውቅና የተሰጣቸው ሰብዓዊ መብቶች መጣስ አይኖርባቸውም። ኢትዮጵያን ጨምሮ እነዚህን ቅድመ ሁኔታዎች ያሟሉ አገራት የተመረጡ ሸቀጦችን ቀረጥ ሳይከፍሉ በአሜሪካ ገበያ ለሸማቾች ያቀርባሉ። 

Äthiopien Textilindustrie Fabrik Näherinnen

ፕሮፌሰር መላኩ "በተለይ በቅርቡ በጣም እያደገ የሔደ የተወሰኑ የኤኮኖሚው ዘርፎች ላይ አለ። ለምሳሌ ከጫማ ጀምሮ የቆዳ ውጤቶች ወደ አሜሪካ የሚልኩ ኩባንያዎች አሉ። በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ውስጥ በርከት ያሉ አሉ። ኢትዮጵያ የአጎዋ ተጠቃሚ መሆኗ በአጭር ጊዜ ውስጥ እነዚህ ኩባንያዎች አማራጭ ገበያ ሳያገኙ ቢቋረጥ ለብዙዎቹ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል መገመት ይቻላል" ብለዋል። 


 

"አጎዋ በተመረጡ ወደ 2 ሺሕ የሚጠጉ ቁሳቁሶች ላይ ኢትዮጵያ እና ሌሎች 38 ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የአፍሪካ አገሮች ቀረጥ ሳይከፍሉ የሚገቡበት መርሐ-ግብር ነው። ይኸ ሲነሳ ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ ምርቶቻቸውን የሚልኩ ኩባንያዎች ተጨማሪ ቀረጥ መክፈል ይጀምራሉ ማለት ነው። ጨርቃ ጨርቅን ብትወስድ እንደ ጨርቃ ጨርቁ አይነት ይለያያል ግን በአማካኝ ወደ 11 በመቶ ቀረጥ ነው ወደ አሜሪካ ለመላክ የሚከፈለው። ይኸ በላኪዎች ላይ ትልቅ ወጪ ነው" ሲሉ ዶክተር ውበት ለውጡን ያስረዳሉ።

የነ ማዳጋስካር መንገድ

ማዳጋስካር በመፈንቅለ-መንግሥት፣ ኮትዲቯር በየርስ በርስ ግጭት እንዲሁም ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የተነሳ በአጎዋ የነበራቸውን ዕድል ተቀምተው ያውቃሉ። ሶስቱ አገሮች በአጎዋ በኩል የሚያገኙት ዕድል ከመመለሱ በፊት ኤኮኖሚያዊ ጫና አድሮባቸዋል። ዶክተር ውበት አሜሪካ አምርራ እርምጃ ከወሰደች ኢትዮጵያ ሊገጥማት የሚችለው ከማዳጋስካር ሊመሳሰል እንደሚችል ያስረዳሉ።

"ማዳጋስካር በጣም ትልቅ የጨርቃ ጨርቅ ምርት ወደ አሜሪካ ትልክ ነበር። በዚያ ውስጥ አጎዋ እንደታገደ ትልቅ መቀነስ ነው የታየው። ያ በኤኮኖሚው ላይ ትልቅ ጉዳት አድርሷል። ምክንያቱም ወደ አሜሪካ ሸቀጥ መላክ በጣም አስፈላጊ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት፤ የአገሪቷን የዕድገት ሁኔታ፣ የአገሪቷን የድህነት ቅነሳ መርሐ-ግብር በጣም የሚያፋጥን ስለሆነ ትልቅ አሉታዊ ተጽዕኖ ነው የነበረው። በኮትዲቯር እና በኮንጎም ተመሳሳይ ሁኔታ ነው የፈጠረው። በተለይ ከእኛ ጋ የሚገናኘው ማዳጋስካር ነው። ምክንያቱም ማዳጋስካር በዚያ ጊዜ በጣም ብዙ ጨርቃ ጨርቅ ትልክ ነበር" በማለት ዶክተር ውበት አስረድተዋል። 

Äthiopien Schuhfabrik Fabrik Herstellung Schuhe

የውጭ ባለወረቶች ከሚያገኟቸው ማበረታቻዎች ባሻገር ለኢትዮጵያ በተፈቀደው የቀረጥ ነጻ ዕድል መሠረት ምርቶቻቸውን ለአሜሪካ ገበያ ማቅረብ መቻላቸው ለመዋዕለ-ንዋይ አገሪቱን እንዲመርጡ የሚያበረታታ ነው። 

ማዳጋስካርን ያሳገዳት በጎርጎሮሳዊው 2008 ዓ.ም. የተቀሰቀሰ ቅልጥ ያለ የፖለቲካ ቀውስ ነው። በያኔው የአገሪቱ ፕሬዝደንት ማርክ ራቫሎማናና ላይ በተፈጸመ መፈንቅለ መንግሥት ምክንያት አገሪቱ ከአፍሪካ ኅብረት እና ከደቡብ አፍሪካ የልማት ማኅበረሰብ (Sadc) ታግዳ  ነበር። በወቅቱ ኖርዌይ እና አሜሪካን የመሳሰሉ አገራት ለማዳጋስካር የሚሰጡትን ዕርዳታ ከልክለዋል።  አገሪቱ ተረጋግታ በጎርጎሮሳዊው ጥር 2010 ዓ.ም. የተነጠቀችውን የአጎዋ ዕድል መልሳ ያገኘችው ከአምስት አመታት በኋላ ነው። 

ዶክተር ውበት "በ2014 እና 2015 አጎዋ ተመልሶ ሥራ ላይ ሲውል ወይም ጥቅማ ጥቅሞቹ ሲመለሱ ኢንቨስትመንት ወይም ወደ ውጪ የምትልከው ሸቀጥ ከአጎዋ በፊት በነበረው ሁኔታ ላይ አልተመለሰም። ምክንያቱም ኢንቨስትመንት የረዥም ጊዜ ዕቅድ ነው። እነዚህ ነገሮች በአጭር ጊዜ የሚለወጡ አይደሉም። ስለዚህ የአጎዋ ጥቅማጥቅም ቢመለስ እንኳን ኢንቨስትመንት እና ወደ ውጪ የሚላከው ሸቀጥ ወደነበረበት ላይመለስ ይችላል። ስለዚህ የአጎዋ መነሳት የአጭር ጊዜ ተጽዕኖ ብቻ አይደለም የሚኖረው" ብለዋል። 

ሊገባደድ ሶስት ገደማ ወራት በቀሩት የጎርጎሮሳዊው 2021 ዓ.ም. ኢትዮጵያን ጨምሮ 39 አገሮች በአሜሪካ ፕሬዝዳንት ውሳኔ የአጎዋ ዕድል ተጠቃሚ ናቸው። ይኸ የኢትዮጵያ ጎረቤቶች የሆኑትን ኤርትራ፣ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳንን አያካትትም። 

እሸቴ በቀለ


 

Audios and videos on the topic