በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር ማሻቀብ | ኢትዮጵያ | DW | 14.05.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር ማሻቀብ

በኢትዮጵያ በሰዉ ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ ሳቢያ የሚፈናቀሉ ሰዎችና እርዳታ የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅት ገለፀ።በሀገሪቱ በሚከሰቱ ግጭቶች፣ድርቅና የጎርፍ አደጋን በመሳሰሉ ችግሮች ሳቢያ በኦሮሚያ፣በሶማሌ፣በደቡብ ክልሎችና በሌሎች አካባቢዎች

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:58

በጉጂ ዞን ግጭት ሳቢያ 200 ሺህ ሰዎች ተፈናቅለዋል - ተመድ

በሀገሪቱ በሚከሰቱ ግጭቶች፣ድርቅና የጎርፍ አደጋን በመሳሰሉ ችግሮች ሳቢያ በኦሮሚያ፣በሶማሌ፣በደቡብ ክልሎችና በሌሎች አካባቢዎች ለምግብ እጥረት የተጋለጡና እርዳታ የሚሹ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ድርጅቱ አመልክቷል።

የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ዕርዳታዎች አስተባባሪ በምህጻሩ ኦቻ ሰሞኑን  ባወጣዉ ዘገባ እንዳመለከተዉ በጎርጎሮሳዉያኑ ሚያዚያ 13 ቀን 2018 በምዕራብ ጌዲዎና ጉጅ ዞን አዋሳኝ ቦታዎች በተቀሰቀ ግጭት ሳቢያ 200 ሺህ ሰዎች መፈናቀላቸዉን ገልጿል። በግጭቱ የሰዉ ህይወት መጥፋቱንና ንብረት መዉደሙን ያስታወሰዉ ድርጅቱ  ከሁለቱም ዞኖች እኩል ቁጥር ያላቸዉ ሰዎች መፈናቀላቸዉን አመልክቷል።  ድርጅቱ የደቡብና የኦሮሚያ ክልል የአስተዳደር ሀላፊዎች  በግጭቱ የተፈናቀሉ ሰዎችን ወደ ቀያቸዉ ለመመለስ አደረጉት ባለው ጥረትም 46 ሺህ ሰዎች ከምዕራብ ጉጂ ዞን 39 ሺህ ሰዎች ደግሞ ከጌዲዎ ዞን ተመልሰዋል። ቀሪዎቹ ተፈናቃዮች ለመመለስ ጥረት ቡደረግም አሁንም ድረስ በተፈናቃዮቹ ዘንድ ስጋት መኖሩን የድርጅቱ ዘገባ ያሳያል።እነዚህ ተፈናቃዮች  ዕርዳታ የሚያሻቸዉ ቢሆንም በተገቢዉ ሁኔታ  እያገኙ አለመሆናቸዉንም  አመልክቷል።

በምዕራብ ጉጅ ዞን ቀርጫ ወረዳ ከ 10 ቤተሰቦቻቸዉ ጋር ተፈናቅለዉ በዲላ ከተማ የሚገኙት የአቶ በየነ ዶሪ ይዞታ የድርጅቱን ዘገባ የሚያጠናክር ይመስላል።እሳቸዉ እንደሚሉት አብዛኛዉ ተፈናቃይ ወደ ቀየዉ ለመመለስ  ስጋት አለዉ።

በግጭቱ የተፈናቀሉ በርካታ ሰዎች  የዕለት ጉርስ በማጣት እየተንገላቱ  ነዉ የሚሉት አቶ በየነ መንግስት አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጣቸዉም ጠይቀዋል።
ድርጅቱ ባለፈዉ ሰኞ  ባወጣዉ ሌላ ዘገባም በሶማሌ ክልል ሸበሌና ሊበን ዞኖች 163 ሺህ ሰዎች በጎርፍ መጠቃታቸዉን ገልጾ ፤ከነዚህም ዉስጥ 98 ሺህ ሰዎች ከቤት ንብረታቸዉ መፈናቀላቸዉን ዘገባዉ አመልክቷል።

እንደ ድርጅቱ ዘገባ ከሶማሌ ክልል በተጨማሪ በኦሮሚያ ክልል በአርሲ፣በባሌ፤በቦረናና ምስራቅና ሞዕራብ ሐረርጌ እንዲሁም በጉጅ ዞኖች ተመሳሳይ ችግር ተከስቷል። በ በርካታ ሰዎችም እርዳታ ፈላጊዎች ሆነዋል። 

ከተጠቀሱት ችግሮች በተጨማሪ  በሚያዚያ ወር በተደረገ  ቅድመ ትንበያ የበልግ ዝናብ እጥረት በሀገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች ሊከሰት እንደሚችልና በዚህም ሳቢያ በአርብቶ አደርና በአርሶ አደሩ የሰብል  ምርቶች ላይ ተፅዕኖ ሊፈጥርና ለተረጅነት ሊያጋልጥ እንደሚችል በቤተሰብ ደረጃ በተካሄደ የድህረ መኸር ግምገማ ጥናት አመልክቷል።
በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በድርቅ ሳቢያ 8 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሰዎች ለተረጅነት የተጋለጡ ሲሆን በጎርጎሮሳዉያኑ 2017 አጋማሽ በኦሮሚያና ሶማሌ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች በተከሰተ ግጭትም 1 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች ከቤት ንብረታቸዉ ተፈናቅለዉ እንደሚገኙ ሲገለፅ መቆየቱ ይታወቃል። 

በአጠቃላይ ቁጥራቸዉ እየጨመረ የመጣዉን የሰብዓዊ ዕርዳታ ፈላጊዎች ለመደገፍ በመንግስት በኩል የሚደረገዉን ጥረት  በዘገባዉ ለማካተት 
የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ሀላፊና የጌዲዮ ዞን የኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ሀላፊን በስልክ ለማነጋገር ያደረግነዉ ጥረት አልተሳካም።

ፀሀይ ጫኔ

ሂሩት መለሰ

 

Audios and videos on the topic