1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኢትዮጵያ አሳሳቢው በሰዎች የመነገድ ወንጀል

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 18 2016

በኢትዮጵያ በተለይም በሀገር ውስጥ በሴቶችና በሕፃናት የመነገድ ድርጊትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ሁሉን አቀፍ ሕጋዊ፣ ፖለቲካዊ፣ አስተዳደራዊና ማኅበራዊ ስልቶች ሊነደፉ ይገባል ሲል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጠየቀ። የኮሚሽኑ የክትትል ዘገባ ወንጀሉን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በቂ ፍትህ ሲሰጥ እምብዛም አይስተዋልም ብሏል።

https://p.dw.com/p/4af4s
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን
በኢትዮጵያ በተለይም በሀገር ውስጥ በሴቶችና በሕፃናት የመነገድ ድርጊትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ሁሉን አቀፍ ሕጋዊ፣ ፖለቲካዊ፣ አስተዳደራዊና ማኅበራዊ ስልቶች ሊነደፉ ይገባል ሲል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጠየቀ። ምስል Ethiopian Human Rights Commission

በኢትዮጵያ አሳሳቢው በሰዎች የመነገድ ወንጀል

በሰዎች የመነገድ ወንጀል ምንነት

እንደ ኢሰመኮ የክትትል ሪፖርት በሰዎች የመነገድ ድርጊት በሰዎች ሕይወት፣ አካል፣ ደኅንነትና ክብር ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ፣ የሰዎችን መብትና ነጻነት የሚያግድ አሊያም ሙሉ በሙሉ እንዳይጠቀሙ የሚያደርግ ነው። ሴቶች እና ሕፃናት በሰው በመነገድ ወንጀል በከፍተኛው ተጋላጭ መሆናቸው ታሳቢ ተደርጎም ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ማዕቀፎች ልዩ ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል ብሎ ደንግጓል።

ይህንኑን መነሻ በማድርግ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን(ኢሰመኮ) በሀገር ውስጥ በሰዎች የመነገድ ድርጊት መነሻ፣ መተላለፊያና መዳረሻ ተብለው በተለዩ ቦታዎች በሁለት ዙር ክትትል ማካሄዱን አሳውቋል፡፡ አማራ ክልል በባሕር ዳር ከተማ፣ አፋር ክልል በሰመራና ሎጊያ ከተሞች፣ በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ ብሎም አዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የኦሮሚያ ክልል ቢሮዎች፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ዞን፣ በሲዳማ ክልል ሃዋሳ ከተማ በሚገኙ ተቋማት እንዲሁም በአዲስ አበባ የፌዴራል ተቋማት ላይ በሁለት ዙር ክትትል ማድረጉን ያሳወቀው ኢሰመኮ፤ በክትትሉ 23 የክልል ቢሮዎች፣ ስድስት የፌዴራል ተቋማት፣ አራት ከተማ አስተዳደር ጽሕፈት ቤቶች፣ 14 የዞን መምሪያዎች እና የፖሊስ ጣቢያዎች፣ 13 መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጀቶች፣ አራት የሥራ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች፣ 21 ተጎጂዎች እና ሰነዶች ታይተዋል ብሏል፡፡

በሴቶችና ጻናት ላይ የሚፈጸመው በሰዎች የመነገድ ወንጀሎች

በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈጸሙ በሰዎች የመነገድ ድርጊት በሀገር ውስጥ የሚፈጸም ወይም ድንበር ተሻጋሪ የመሆን መልክ ይዟል ያለው ኮሚሽኑ፤ ሴቶች እና ሕፃናት በሰው በመነገድ ድርጊት ሳቢያ ከጾታዊ እና አካላዊ ጥቃት የመጠበቅ፣ ብሎም ፍትሕ የማግኘት መብቶቻቸው መጣሱን አስረድቷል። በተለይም ሕፃናት በሰው የመነገድ ድርጊት ተጎጂ በመሆናቸው የትምህርትና ጤናን ጨምሮ የሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶችን የማግኘት መብቶቻቸውን አጥተዋል ነው የተባለው። ትምህርት እና የተሻለ ሕይወት ፍለጋ  በዘመድ አሊያም በደላላ ወደ ከተማ በመምጣት ለድብደባ፣ ጾታን መሠረት ላደረጉ ጥቃቶች፣ ለጉልበት ብዝብዛ እና የግዳጅ ሥራ እንዲሁም ለኢ-ሰብአዊ አያያዝ ተጋልጠዋል ነው ያለው የኢሰመኮ በክትትል ሪፖርቱ።

በኮሚሽኑ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአረጋውያን እና የአካል ጉዳተኞች መብቶች ክትትል ኃላፊ ርግበ ገብረሐዋርያ ለዶቼ ቬለ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፤ በተለይም በአገር ውስጥ የሚደረግ በሴቶችና ሕጻናት የመነገድ ተግባር ጎልቶ ይስተዋላል። ኮሚሽኑ በሀገር ውስጥ በሴቶች እና ሕፃናት መነገድን የመከላከል ሥራዎች አናሳ መሆን፡ ኢትዮጵያ ባጸደቀቻቸው በሴቶች እና ሕፃናት መነገድን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወጡ ስምምነቶች መሠረት መንግሥታት በሴቶች እና በሕፃናት መነገድን ለመከላከል ሁሉን አቀፍ ሕጋዊ፣ ፖለቲካዊ፣ አስተዳደራዊ እና ማኅበራዊ ስልቶች መንደፍ እንዳለባቸው ያመለክታል ነው ያለው። በሰው መነገድን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በብሔራዊ ደረጃ የተቋቋመው ብሔራዊ የትብብር ጥምረት ሪፖርቶች፣ የሥራ ዕቅዶች እና ጥናቶችም በዋናነት የትኩረት አቅጣጫቸው ድንበር ማሻገር እና ከሀገር ውጪ በሰው መነገድ ድርጊቶች ላይ ብቻ መተኮሩን የሚያሳ ነው ተብሏል።

ጥቃት የመከላከል የእጅ ምልክት
በሴቶች እና ሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች እንዲቆሙ የሚጠይቅ የእጅ የመከላከል ምልክት። ምስል Colourbox

 መንግሥት ድርጊቱን ለመከላከል የተቀናጀ፣ ቀጣይነት ያለው እና ሊመዘን የሚችል ለሕዝቡ በተለይም ተጋላጭ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ግንዛቤ ማሳደግ ቢኖርበትም፤ ድርጊቱን ለመከላከል ተገቢው ትኩረት አልተሰጠም ተብሏል።

ተጎጂዎችን የመርዳት እና ፍትህ የማንገስ ጥረቶች ይዞታ

ተጎጂዎችን ወደ ቤተሰብ መልሶ ለመቀላቀል የሚሰጡ ኢኮኖሚያዊ ድጋፎች፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የቴክኒክ ክህሎትና የንግድ ሥራ አመራር ሥልጠናዎች ከውጭ ሀገር ተመላሾች ላይ ብቻ ያተኮሩ ናቸውም ተብሏል። በሀገር ውስጥ በሰው የመነገድ ወንጀል ፈጻሚዎችን ለማስቀጣት የሚያስችል የተደራጀ ሥርዓት አለመኖር፣ መንግሥት ድርጊቱን ለመክሰስ እና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ዐቅም መፍጠር እንደምኖርበትም ያሳል ነው የተባለው፡፡ ጉድለቱን በስፋት የፈጠረውስ በአገሪቱ ያለው የሕግ ክፍተት ወይስ የማስተግበር ቁርጠንነት ማነስ ነው የተባሉት ኃላፊዋ፤ «የፖለቲካ ቁርጠኝነት እና የቅንጅታዊ ሥራ ማነስ ትልቁ ሊሠራበት የሚገባ ክፍተት ነው» የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

የኢሰመኮ ምክረ-ሃሳብ

ኮሚሽኑ እንደ ምክረሃሳብ ያቀረበውን መፍትሄ በተመለከተም የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአረጋውያን እና የአካል ጉዳተኞች መብቶች ክትትል ኃላፊ ርግበ ገብረሐዋርያ  ሲናገሩ፤ «ለሕግ አስከባሪ አካላት የሚሰጡ ስልጠናዎች በቂ አለመሆን፣ ክትትል በተደረገባቸው የፖሊስ ጣቢያዎች እና መምሪያዎች የሀገር ውስጥ በሰዎች የመነገድ ወንጀልን የሚመለከቱ የተሟላ መረጃዎች አለመኖር፣ በየእርከኑ ያሉ መረጃዎችን መለያየትና የተደራጀ አለመሆኑን ኢሰመኮ ተገንዝቧል።» ካሉ በኋላ፤ «በመሆኑም፤ መንግሥት ኢትዮጵያ ባጸደቀቻቸው በሰዎች መነገድን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የሚያገለግሉ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ የሕግ እና የሰብአዊ መብቶች ሰነዶችን ገቢራዊ ማድረግ፣ ብሔራዊ ትብብር ጥምረቱ በሀገር ውስጥ በሴቶች እና በሕፃናት መነገድን ለመከላከል ተገቢ እርምጃዎች እንዲወሰዱ፤ በክልሎች ያሉ የትብብር ጥምረት መዋቅሮች አስፈላጊው በጀት ተመድቦላቸው ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ፣ የፍትሕ ሚኒስቴር እና የፌዴራል ፖሊስ ከክልል ፍትሕ ቢሮዎች እና ከሌሎች ባለድርሻ አካለት ጋር በመቀናጀት የሀገር ውስጥ በሰዎች የመነገድ ድርጊቶች መነሻና መዳረሻዎችን የሚያስከትላቸውን የመብት ጥሰቶች በሚያሳይ መልኩ ለፖሊሲ ማሻሻያዎች ግብአት ሊሰጡ በሚችል መልኩ የመረጃ ሥርዓት እንዲዘረጋ፤ የፍትሕ አካላት በሀገር ውስጥ በሚደረጉ በሰዎች የመነገድ ድርጊቶች ላይ ምርመራ በማድረግ ክስ በመመስረትና አጥፊዎችን ተጠያቂ በማደረግ ተጎጂዎች ካሳን ጨምሮ ውጤታማ መፍትሔ እንዲያገኙ የሚያስችሉ እርምጃዎችን እንዲወስዱ» የሚጠይቁ ምክረ ሃሳቦች መቅረባቸውን ዘርዝረዋል።

ሥዩም ጌቱ

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ