በኢትዮጵያ ተቃውሞዎች 699 ሰዎች ተገድለዋል | ኢትዮጵያ | DW | 18.04.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ተቃውሞዎች 699 ሰዎች ተገድለዋል

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በአገሪቱ ተቀስቅሰው በነበሩ ተቃውሞዎች 699 ሰዎች መገደላቸውን አስታወቀ። ኮሚሽኑ የጸጥታ አስከባሪዎች አለመረጋጋቱን ለመግታት «ተመጣጣኝ ርምጃ» ወስደዋል ብሏል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:10

በኢትዮጵያ ተቃውሞዎች 699 ሰዎች ተገድለዋል

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በአገሪቱ ተቀስቅሰው በነበሩ ተቃውሞዎች 699 ሰዎች መገደላቸውን አስታወቀ። ኮሚሽኑ የጸጥታ አስከባሪዎች አለመረጋጋቱን ለመግታት «ተመጣጣኝ እርምጃ» ወስደዋል ብሏል። ዛሬ ለተወካዮች ምክር ቤት አባላት የቀረበው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የተቃውሞ ምርመራ ዘገባ በአገሪቱ ለተቀሰቀሱት ሕገ-ወጥ የተቃውሞ ሰልፎች የተቃውሞ ፖለቲካውን ጎራ ተጠያቂ አድርጓል።

ኮሚሽኑ በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ የመሩት «የኦሮሞ ነጻ አውጭ ግንባር (ኦነግ)፣ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) እና መቀመጫውን በዩናትድ ስቴትስ ያደረገው የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ» ናቸው ብሏል። ዘገባው በኦሮሚያ  462 የተቃውሞ ሰልፈኞች እና 33 የፀጥታ ኃይላት መሞታቸውን አትቷል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን «በኦሮሚያ ክልል 15 ዞኖች እና 91 ከተሞች፣ በአማራ ክልል 5 ዞኖች እና 55 ወረዳዎች እንዲሁም በደቡብ ክልል ጌዲዮ ዞን በሚገኙ ስድስት ከተሞች የተደረጉ ተቃውሞዎችን መርምሪያለሁ» ብሏል-ዛሬ በኃላፊው ዶ/ር አዲሱ ገብረእግዚአብሔር በኩል ለተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት። በኦሮሚያ ክልል የተካሄዱ ኮሚሽኑ «ሕገ-ወጥ» ባላቸው የተቃውሞ ሰልፎች «የብሔር ጥቃት ተፈፅሟል፤  የኃይማኖት እኩልነት ተንዷል፣ የሰዎች በሕይወት የመኖር መብት ተጥሷል፤ እንዲሁም የአካል ጉዳት ደርሷል» ብሏል ኮሚሽኑ። 

በአማራ ክልል የወልቃይት የማንነት ጥያቄ በቀሰቀሰው ተቃውሞ «110 ሰላማዊ ሰዎች እና 30 የፀጥታ ኃይላት በአጠቃላይ 140 ሰዎች መሞታቸውን» እና 336 ሰዎች መቁሰላቸውን አስታውቋል። በአማራ ክልል በተቀሰቀሰው ተቃውሞ «ኢሳትን በመሳሰሉ የሽብር መጠቀሚያ ሚዲያዎች መልዕክቶች ተላልፈዋል» ሲል ኮሚሽኑ ወንጅሏል።

በደቡብ ክልል ጌዲዮ ዞን በተቀሰቀሰ ተቃውሞ 34 ሰዎች ሲሞቱ 139 መቁሰላቸውን ኮሚሽኑ በዛሬው ዘገባው አትቷል። የኮሚሽኑ ዘገባ በተወሰኑ ሁነቶች ስህተት የፈጸሙ የጸጥታ አስከባሪዎች በሕግ ሊጠየቁ እንደሚገባ ሀሳብ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በተቃውሞዎቹ ወቅት ሰዎችን ያለ ዳኝነት ገድሏል ሲሉ የሚወቅሱት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በገለልተኛ ወገን ምርመራ ሊደረግ ይገባል ሲሉ ይወተውታሉ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የአውሮጳ ኅብረት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉባቸውን ተቃውሞዎች አንድ ገለልተኛ አካል እንዲያጣራ ያቀረቡትን ጥሪ መንግሥታቸው ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆኑን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒሥትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ለውጭ መገናኛ ብዙኅን ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒሥትር ኃይለማርያም ጉዳዩን ሊመረምር የሚችለው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ብቻ ነው ብለዋል።

ጌታቸው ተድላ ኃይለጊዮርጊስ

እሸቴ በቀለ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic