በኢትዮጵያ በሰብአዊ ቀውስ ለተጎዱ የአሜሪካ ተራድዖ ድርጅት 80 ሚሊዮን ዶላር ርዳታ መደበ
ቅዳሜ፣ መጋቢት 7 2016የአሜሪካ ህዝብ ተራድኦ ድርጅት (USAID) ረዳት የቢሮ አስተዳዳሪ ሶናሊ ኮርዴ በአዲስ አበባ፣ ትግራይ እና አፋር ክልሎች አደረኩ ባሉት የውስን ቀናት ቆይታ አሜሪካ የኢትዮጵያ ህዝብን ለመርዳት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ ነው ሲሉ ነው መግለጫቸውን የጀመሩት፡፡ ጉብኝታቸው በመላው አገሪቱ የሚስተዋሉትን የአስቸኳይ ምግብ እርዳታን ለማዳረስ ያለመ እንደሆነም ነው የጠቆሙት፡፡
ከዚህ በፊት የአሜሪካ ህዝብ ተራድኦ ድርጅት (USAID) ከሌሎች ዓለማቀፍ ረጂ ድርጅቶች ጋር በመሆን በኢትዮጵያ አጋጥሟል የተባለውን የእርዳታ ምግብን ላልተገባ ዓለማ የማዋል ተግባርን በመኮነን ድጋፉን መግታቱ ይታወሳል፡፡
ይሁንና ከባለፈው ጎርጎሳውያን ዓመት 2023 መጨረሻ ወዲህ የእርዳተው ዳግም መጀመርን ተከትሎ ዩናይትድ ስቴትስ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን በባለፈው ጥር ወር ብቻ 2.4 ሚሊየን ኢትዮጵያውያንን ተደራሽ ያደረገ ድጋፍ ማድረጓ ነው የተገለጸው፡፡ የአሜሪካ ህዝብ ተራድኦ ድርጅት (USAID) ረዳት የቢሮ አስተዳዳሪ ሶናሊ ኮርዴ በአሁኑ ጉብኝታቸውም ይህንኑን የእርዳታ ተደራሽነት ማሳለጥ ላይ ያተኮረ ጉብኝት ስለማድረጋቸው ነው በዛሬው መገለጫቸው ያመለከቱት፡፡
የኃላፊዋ የአፋርና ትግራይ ክልሎች ጉብኝት
“በአፋር በነበረኝ ቆይታ በበራህሌ ወረዳ ያለውን የምግብ ማከፋፈያ ማዕከል ጎብኝቻለሁ፡፡ በዚያ የአሜሪካ ህዝብ ተራድኦ ድርጅት (USAID)፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም (WFP) እና ማህበረሰቡ ቅድሚያ ልንሰጣቸው የምንፈልገውን ለከፋ ጉዳት የተዳረጉትን ሰዎች በትብብር የመለየት ተግባር እያከናወኑ ነው፡፡ በዚህም በያንዳንዱ አባወራ የልየታ ስራ ተከናውኖ እርዳታው በትክክል ለተቸገሩት እንደሚደርስ ተመልክቻለሁ” ነው ያሉት፡፡
ኃላፊዋ ጉብኝታቸውን ያደረጉበት ሌላው ክልል ትግራይ ነው፡፡ በዚህ ክልል በተለይም በጦርነት እና ድርቅ እጅግ የተጎዳውን አቤርጌሌ አከባቢ መጎብኘታቸውን ጠቅሰው፤ ረጂ ተቋማት ከታህሳስ ወር ወዲህ በዚህ አከባቢ ለአራተኛ ዙር የምግብ እርዳታ ማከፋፈል መፈጸማቸውን እንዳረጋገጡ አስረድተዋል፡፡ “እንዲሁም በትግራይ ህጻናትን እና እናቶችን የሚረዱ ሆስፒታሎችን ጎብኝቻለሁ፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ በአሜሪካ ህዝብ ተራድኦ ድርጅት (USAID) እና ጎል በዚህ በእጅጉ ለምግብ እጥረት ለተዳረጉ ከ3 ሺህ በላይ ሰዎች ድጋፍ ተደርጓል፡፡ በዚያና በመላው አገሪቱ ጀብዱ የሰሩትን የሰብዓዊ ድጋፍ ሰራተኞችን ማድነቅ እፈልጋለሁ፡፡ በተለይም እንደ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ያሉ ረጂ ድርጅቶች በእጅጉ ለአደጋ የተጋለጡትን ተደራሽ ለማድረግ የሚሰሩት ስራ እውቅና የሚሰጠው ነው” ብለዋል፡፡
ኃለፊዋ በጉብኝታቸው እጅግ አስከፊ ያሉት የድርቅ እና ግጭት ተጠቂዎችን መመልከታቸውንም አንስተዋል። “በጉብኝቴ ወቅት በአይኔ እና በልቦናዬ የተመለከትኩት ብኖር በእጅጉ የተጎዱና እርዳታ የሚሻቸውን ሰዎች በህብረተሰቡ ውስጥ መኖራቸውን ነው፡፡ እነዚህ ማህበረሰቦች ከዓመታት የግጭት ተጽእኖ ለመውጣት ጥረት በሚያደርጉብት ወቅት ያጋጠማቸው ድርቅ ደግሞ ለሌላ መከራ ዳርጎአቸው ተመልክቻለሁ፡፡ በመላው አገሪቱም ተመሳሳ ፍላጎቶች መኖራቸውን ከሰብኣዊ ድጋፍ ባለሙያዎች ብረዳም በአገሪቱ የተስፋፋው ግጭት እርዳተው የሚሻቸው ጋ መድረስን ከባድ ማድረጉን ተገንዝብዬያለሁ” ብለዋልም፡፡
የአሜሪካ ተጨማሪ ድጋፍ
የአሜሪካ ህዝብ ተራድኦ ድርጅት (USAID) ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር ከሚያደርጉት የእርዳታ አቅርቦት በተሻለ ድጋፉ ያስፈልጋል ያሉት ኃላፊዋ፤ ዛሬ ይፋ ያደረጉት የ80 ሚሊየን ዶላር ተጨማሪ እርዳታ ያስፈለገም ለዚሁ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በዚህም የገንዘብ ድጋፍ ለአደጋ እጅግ ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ አካላትን እንደሚረዱ፣ ግብርና እና የስነምግብ ስራዎችም እንደሚደገፉ ተጠቁሟል፡፡ በድጋፉ ከ5 ዓመት በታች የሆኑ 1.5 ሚሊየን ህጻናት፣ ከ600 ሺህ በላይ በእርግዝና ላይ ያሉ እናቶች እና ህክምና የሚያሻቸው እናቶች እንደሚደገፉ ተብራርቷልም፡፡
በተጨማሪም የአሜሪካ ህዝብ ተራድኦ ድርጅት (USAID) በኢትዮጵያ 8 ክልሎች 4.5 ሚሊየን ህዝብ የእርዳታው ተደራሽ ለማድግ ወጥኖ እንደሚሰራም ነው የተነገረው፡፡
ግጭት፣ ድርቅ እና የጎርፍ አደጋዎች ደጋግሞ የሚጎበኟትን ኢትዮጵያ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎቿ ለከፋ ሰብዓዊ ድጋፍ ስለመዳረጋቸው የሰብአዊ ተቋማት ተደጋጋሚ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ የአሜሪካ ህዝብ ተራድኦ ድርጅት (USAID) ረዳት የቢሮ አስተዳዳሪ ሶናሊ ኮርዴ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ መግለጫ ሲሰጡ አብሯቸው የተገኙት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት ሰብዓዊ ቀውስ እየፈጠረ ያለውን ግጭት ለማርገብ አሜሪካ አበክራ ትሰራለች ነው ያሉት።
ሥዩም ጌቱ
እሸቴ በቀለ