በኢሬቻ ዋዜማ ቢሾፍቱ ሥጋት ተጭኗታል | ኢትዮጵያ | DW | 30.09.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

በኢሬቻ ዋዜማ ቢሾፍቱ ሥጋት ተጭኗታል

ዓመታዊውን የኢሬቻ በዓል ለማክበር በዝግጅት ላይ የምትገኘው ቢሾፍቱ ሥጋት እንዳንዣበበባት የከተማዋ ነዋሪዎች እና የዶይቼ ቬለ ዘጋቢ ገለጡ። ነገ ለሚከበረው የኢሬቻ በዓል አምቦ እና ጅማን ጨምሮ ከተለያዩ አካባቢዎች እንግዶች ወደ ቢሾፍቱ እየገቡ ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:50
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:50 ደቂቃ

በከተማይቱ ጥብቅ የጸጥታ ቁጥጥር ነበር

በዋዜማው በከተማዋ አደባባዮች በባህላዊ ልብሶች ያጌጡ የአካባቢው ነዋሪዎች እና እንግዶቹ ይታያሉ። መዝናኛ ቤቶች እርጥብ ሳር (ቄጤማ) ጎዝጉዘዋል። በዓሉ የሚከበርበት የሆራ አርሰዲ ሐይቅ አቅራቢያን ጨምሮ በተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች ኢሬቻን የሚዘክሩ ማስታወቂያዎች ተሰቅለዋል። ወጣቶችም ጽዳት በማካሔድ ላይ ይገኛሉ። 

ከትናንትናው ዕለት ጀምሮ ወደ ከተማዋ የሚዘልቁ እንግዶች እና መንገደኞች ከሚጓዙበት ተሽከርካሪ ወርደው በጸጥታ ኃይሎች ይፈተሻሉ። እንግዶች ከየት መጣነታቸውን እና የጉዞ ዓላማቸውንም ይጠየቃሉ። የከተማዋ ነዋሪዎች የምሥጋናው በዓል እንደ ባለፈው ዓመት ተቃውሞ ሊደመጥበት ይችላል የሚል ሥጋት እንዳላቸው ለዶይቼ ቬለ ወኪል ተናግረዋል። 

ከአንድ አመት በፊት በኢሬቻ በዓል አከባበር ላይ ከተከሰተው አደጋ ለጥቂት የተረፈው የ28 ዓመቱ ፊሮሚሳ ዳራሳ ፍርሐት ከሚሰማቸው ተሳታፊዎች አንዱ ነው። "በውስጤ ፍርሐት ይሰማኛል። ነገር ግን እኔ ካልመጣሁ በዙሪያዬ ያሉ ሰዎችም አይመጡም" የሚለው ፊሮሚሳ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲወራረስ የመጣውን የኢሬቻ በዓል ልንጠብቀው ይገባል ሲል ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ተናግሯል። 

በኢሬቻ ክብረ-በዓል የጦር መሳሪያ የታጠቁ የጸጥታ አስከባሪዎች በዓሉ ወደ ሚከበርበት አካባቢ እንደማይገቡ የትኛውም ሰንደቅ ዓላማም እንደማይውለበለብ የኦሮሚያ ክልል አስታውቆ ነበር። የዘንድሮውን በዓል የሚያስተባብሩ 300 ወጣቶች ከአባ ገዳዎች ተመርጠው ሥልጠና መውሰዳቸውን የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወ/ሮ አልፊያ ሐጂ ይሱፍ ለዶይቼ ቬለ ከቀናት በፊት ተናግረዋል። 

ባለፈው ዓመት በመንግሥት ተቃዋሚዎች ላይ ጸጥታ አስከባሪዎች አስለቃሽ ጭስ መተኮሳቸው በቀሰቀሰው መረጋገጥ በርካታ ሰዎች መገደላቸው አይዘነጋም። የሟቾቹ ቁጥር እስካሁን በግልፅ አይታወቅም። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሒውማን ራይትስ ዎች ተቃዋሚዎችን ጠቅሶ እንደዘገበው በባለፈው ዓመት በተከሰተው አደጋ 700 ገደማ ሳይሞቱ እንዳልቀሩ አትቷል። በአደጋው የሞቱት 55 ሰዎች መሆናቸውን የገለጠው የኢትዮጵያ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ገቢራዊ ያደረገው ከጥቂት ቀናት በኋላ ነበር።  

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አደጋው ከተከሰተበት አካባቢ ራቅ ብሎ ለሟቾች የመታሰቢያ ኃውልት አቁሟል። በሐውልቱ ላይ "ድንገተኛ ሞት" ተብሎ መፃፉ ያስተቸው የክልሉ መንግሥት ግን ዘግየት ብሎ ፅሁፉን ለማረም ተገዷል። በበርካቶች ዘንድ ቁጣን የቀሰቀሰው እና በሐውልቱ ላይ ሰፍሮ የነበረው "ድንገተኛ" የሚል ቃል እንዲወጣ ተደርጓል። 

ስለቢሾፍቱ የኢሬቻ የዋዜማ ውሎ ከባልደረባችን ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ የድምጽ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ። 

እሸቴ በቀለ

ተስፋለም ወልየስ 

 

Audios and videos on the topic