በኢራን ወቅታዊ ይዞታ ላይ የጀርመን ፓርላማ ውይይት፣ | ዓለም | DW | 18.06.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

በኢራን ወቅታዊ ይዞታ ላይ የጀርመን ፓርላማ ውይይት፣

የጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ም/ቤት (ቡንደስታኽ)፣ ኢራን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በኋላ ካካሄደች በኋላ በምትገኝበት ሁኔታ ላይ ተወያይቷል።

ከሞላ-ጎደል ሁሉም ፓርቲዎች የኢራን ይዞታ በሰላማዊ መንገድ እልባት እንደሚያገኝ፣ ያላቸውን ተስፋ ነው ያንጸባረቁት። የጥምሩን መንግሥት ፓርቲዎችም ሆነ የተቃውሞ ፓርቲዎችን በመወከል ንግግር ያሰሙት ሁሉ፣ ምርጫው ሳይጭበረበር አልቀረም በሚለው ጉዳይ ላይ አስተያያት ከመስጠት ይቆጠቡ እንጂ፣ ለተቃውሞ አዳባባይ የወጡትን ኢራናውያን እንደሚደግፉ ነው ያስታወቁት። የበርሊኑ የዶቸ ቨለ ባልደረባ ፔተር ሽትትሰል የላከውን ዘገባ ተክሌ የኋላ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል።

የነጻ ዴሞክራቱ ፓርቲ (FDP) የውጭ ጉዳይ ፖለቲከኛ Werner Hoyer በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት መድረክ፣ የሚከተለውን ንግግር ካሰሙ በኋላ፣ ከሁሉም ወገን፣ ይበል! ያሰኘ ጭብጨባ ነበረ ያጀባቸው።

«የአካል ጉዳት ሊያጋጥማቸው፤ ህይወታቸውንም ሊያጡ እንደሚችሉ እያወቁ፣ ለአገሪቱ የተሻለ መፃዔ ዕድል ሲሉ በአደባባይ ድምጻቸውን ለሚያሰሙት፣ በመቶ ሺ ለሚቆጠሩት ኢራናውያን ፣ ባርኔጣዬን በማውለቅ አድናቆቴን እገልጻለሁ። ኢራናውያኑ ሰልፈኞች ብርቱ አደጋ ቢደቀንባቸውም፣ ድምፅ ያላቸው መሆኑ እንዲታወቅላቸው፣ የሰጡት ድምፅ ሊቆጠር እንደሚገባ ለማሳሰብ የፈለጉት። እኛ ግን በአስተማማኝዋ አውሮፓ ተቀምጠን የራስን ድምፅ መስጠትና ለድምፅ መቆጠርም መቆም እንድንችል፣ ያስገኘልንን የመብት እሴት ትንሽ በመዘንጋታችን ሊያሳፍረን ይገባል። »

የአረንጓዴው ፓርቲ በመወከል ለመራኂተ-መንግሥትነት የሚወዳደሩት Jürgen Trittin ፣ ኢራን ውስጥ ከሰሞኑ በከተሞች አደባባይ እየታየ ያለው ተንቀሳቃሽ ስዕል፣ በ 1979 ዓ ም፣ ሻሁ ከሥልጣን ተወግደው እስላማዊ ሪፓብሊክ የተመሠረበትን ወቅት የሚያስታውስ መሆኑን ከገለጡ በኋላ፣ አሁን ስላለው ተቃውሞ ቀጠል በማድረግ---

«ይህ ያሁኑ ተቃውሞ፣ በሙላዎቹ ላይ ያነጣጠረ አይደለም። ብዙ የሃይማኖት ሰዎች፣ ለዘብ ያለ አቋም ያላቸውና ወግ አጥባቂዎች፣ እንዲሁም ወጣት ከጎልማሳ፣ ተማሪዎችና ምሁራን ፣ የንግድ ሰዎችና ሠርቶ-አደሮች ናቸው በኅብረት በጎዳና ሠልፍ ላይ የሚታዩት።»

ትሪቲንም ሆኑ ሌሎቹ ተናጋሪዎች፣ የምርጫውን አካሄድ ከመገምገም የተቆጠቡ ሲሆን፣ መጠኑ አይታወቅ እንጂ የማጭበርበር ተግባር ስለመፈጸሙ ሁሉም አይጠራጠሩም። በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ሊቀ-መንበር የክርስቲያን ዴሞክራት ፓርቲ አባል Ruprecht Polenz…

«የምርጫው አካሄድ፣ ህዝብ ድምፅ የሰጠባቸው ካርዶች ቆጠራና የመሳሰለው ከመጀመሪያውም ዴሞክራሲያዊ ምርጫ አልነበረም። መራጮች ግን በቁርጠኛነት የተሰለፉበት ምርጫ ነበረ። ከ 400 በላይ ከነበሩት እጩ ተወዳዳሪዎች መካከል 4 ብቻ እንዲቀርቡ ነበረ የተፈቀደው። የተቀሩት ግልጽ ባልሆነ አሠራር፣ በአብዮት ጠባቂው ም/ቤት ከመጀመሪያው እንዳይቀርቡ ታግደዋል።»

በቡንድስታኽ በተሰማው ንግግር ብዙኀኑ የፓርላማ አባላት፣ በኢራን አመራር ላይ ያላቸውን አቋም የነቀፉ ብቸኛ ተናጋሪ፣ የግራው ወገን ዲስኩረኛ Norman Paech ነበሩ። እርሳቸውም ባለፈው ሳምንት የተካሄደውን የኢራኑን ምርጫ፣ እ ጎ አ ፣ በ 2006 ዓ ም፣ በፍልስጤም ከተካሄደው፣ ነጻና ፍትኀዊ ነበረ ካሉት ጋር አመሳስለውታል ።

«ይህ የለየለት የዴሞክራሲ ተመጻዳቂነት ነው። በመጀመሪያ ምርጫ እንዲካሄድ መወትወት፣ ከዚያ ደግሞ ምርጫውን አለመቀበልና አሸናፊውን ማግለል!ቁጣው የት ገባ? ፓርላማ ውስጥ፣ ለዴሞክራሲ ጥብቅና በመቆም፣ ምነው የቁጣ ድምፅ አልተሰማ!?»

የኢራኑ የምርጫ ውጤት አጠራጣሪ ነው ስለመባሉ፣ Paech ፣ ነጻው የአሜሪካ የምርምር ተቋም ፣ ፕሬዚዳንት ማህሙድ አህማዲነጃድ ያላንዳች ጥርጥር ብልጫ ያሳያሉ ሲል አስቀድሞ ተንብዮ እንደነበረ ጠቅሰዋል። የባየርኑ የክስስቲያን ሶሺያል ኅብረት (CSU) ባልደረባ ኤድዋርድ ሊትነር ይህን አባባል በመቃወም፣ አህማዲነጃድ በመጀመሪያ ዙር ምርጫ ድል ይቀዳጃሉ ሲል የጠቆመ አንዳች የህዝብ አስተያየት መመዘኛ ጥናት አልቀረበም ካሉ በኋላ፣ የምርጫውን ውጤት እመረምራለሁ ላለው የኢራን መንፈሳዊ አመራር የሚከተለውን ተማጽኖ አቅርበዋል።

«ሃይማኖትና የሃይማኖት መሪዎች፣ ምንጊዜም፣ እውነትን የመናገር ኀላፊነት እንዳለባቸው ሊሰማቸው ይገባል። ይህን ይግባኝ ከፍተኛው መንፈሳዊ መሪ ኻሜኔይ፣ ብይን በሚሰጡበት ጊዜ፣ የኢራን ምርጫ በትክክል መካሄዱን ማረጋገጥ ኀላፊነታቸው መሆኑ ሊሰማቸው ይገባል። »

የሊትነር ባልደረባ ፣ ሆልገር ሃይባህ ፣ በተጨማሪ እንዳሉት፣ ከምርጫው ውጤት ጋር ያልተጣጣመ፣ የተዛባ አሠራር ነበረ። ምርጫን እንደሚያሸንፍ እርገጠኛ መሆኑ የሚሰማው ፣ ምርጫን ማጭበርበር አይኖርበትም ፣ ትርጉም የለሽ ነውና!

ፔተር ሽትትሰል/ተክሌ የኋላ/አርያም ተክሌ