በኢራቅ የኢራን ተፅዕኖ | ዓለም | DW | 15.08.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

በኢራቅ የኢራን ተፅዕኖ

የኢራቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ኑሪ አልማሊኪ የኢራን መንግሥት ድጋፍ እንዳላቸዉ ይነገራል። የቴህራን መንግሥት አል ማሊኪ ገና በጎርጎሪዮሳዊዉ 2006ዓ,ም ባግዳድ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትርነቱን መንበር ለመጀመሪያ ከያዙበት ጊዜ አንስቶ አዎንታዊ አመለካከቱን ሲቸራቸዉ ታይቷል።

አሁን ከሱኒ አክራሪ ታጣቂ ሚሊሺያዎች ጋም ፍልሚያ ዉስጥ ሲገቡ ሺአ የሆኑት አል ማሊኪ የሺአ አስተዳደር ያላት የጎረቤት ኢራንን ድጋፍ እንደሚያገኙም ያዉቁት ነበር። የኢራን አብዮታዊ ሠራዊትም በዚህ መሳተፉ ተነግሯል። እንዲያም ሆኖ ብሔራዊ ዕርቅ ላለመቀበል አሻፈረኝ ያሉት የመንግሥት መሪ ርምጃ የኢራቅን ግጭት እያጋጋለዉ በመሄዱ ቴህራን ጀርባዋን እንደሰጠቻቸዉ በቦታቸዉ አዲስ መመረጡ ግልጽ አድርጎታል።

ኢራን በኢራቅ ዉስጣዊ አስተዳደር ሳይቀር ቀጥተኛ ተፅዕኖ የማሳደር አቅም እንዳላት በግልፅ የሚያሳዩ ምልክቶች በርካቶች ናቸዉ። በተለይ ከሳዳም ሁሴን ዉድቀት በኋላ ቴህራን በጎረቤቷ ኢራቅ ጉዳይ ጣልቃ ገብነቷ ጨምሯል። ይህ ተፅዕኖ እንደኢራቅ ጉዳይ ተመራማሪዉ ፕሮፌሰር ፈርሃድ ሰይደር ከሆነ እንዲያዉም ወደኋላ ሁሉ ተጉዞ በሳዳም ዘመን በጎርጎሪዮሳዊዉ 1979 እስከ 2003,ም ባለዉ ጊዜ ሺዓቶች በደረሰባቸዉ ጭቆና ወደጎረቤት ኢራን መሰደዳቸዉ ጋ ሁሉ ይያያዛል።

ያኔም ጥብቅ ግንኙነታቸዉ ጎለበተ ይላሉ ፕሮፌሰሩ፤

«የኢራን ተፅዕኖ ከፍተኛ ነዉ። ይህም በሳዳም ሁሴን ዘመን ኢራን ዉስጥ ከነበሩትና ጥብቅ ትስስር ከፈጠሩት የሺዓ ቡድኖችም ያልፋል። የሺዓቶች ማንኛዉም እንቅስቃሴ ማለት ይቻላል፣ ፓርቲዎች ድርጅቶች እንዲሁም ሚሊሺያዎች የኢራን ተፅዕኖ አለባቸዉ። ሁለተኛዉ ደግሞ ኢራን ኩርዶች ላይ ያላት ተፅዕኖ ነዉ። ከምን በላይ የኩርድ ጀግኖች ኅብረት ከኢራን ጋ በጥብቅ የተሣሠረ ነዉ። ኢራን ትልቅ ሀገር ናት፤ እናም በሜሶፖታሚያ አካባቢ ለሚገኙ ሺአዎች እንደከለላ ራሷን ታያለች፤ ኢራቅ ዉስጥም ማለት ነዉ።»

ኢራን ኢራቅ ዉስጥ የምታሳድረዉ ተፅዕኖ በአንድ አቅጣጫ ብቻ የሚታይ አይደለም። በግንባር ቀደምትነት የሚወሰደዉ ግን ፖለቲካዊዉ ተፅዕኖ ነዉ። ኢራን ከሁሉም በበለጠ አልማሊኪ በአባልነት ከሚገኙበት ዳዋ ፓርቲ ጋ ጥሩ ግንኙነት መሥርታለች። በወታደራዊዉ ረገድ ደግሞ የኢራቅን ጦር እና የሺአ ሚሊሺያዎችን ትደግፋለች። በሶሶስተኛነት የሚታየዉ በሁለቱ ሃገራት የሚገኙት ሺአዎችን ያስተሣሠረዉ ሃይማኖታዊ መስመር ነዉ። የኢራቅ በሆኑት ከተሞች ናጃፍ እና ካርባላ ታላላቅ የሺአቶች ሐይማኖታዊ ስፍራዎች ይገኛሉ። በየዓመቱ በመቶና ሺህ የሚገመቱ የኢራቅና ኢራን ሺያዎች ወደእነዚህ ቦታዎች ሐይማኖታዊ ጉዞ ያደርጋሉ። በቤይሩት የመካከለኛዉ ምሥራቅ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር ሊና ኻቲብ እንደሚሉትም የኢራቅ ፖለቲከኞች ለመሪነት ለመመረጥ የኢራንን ቡራኬ ካላገኙ ዋጋ አይኖራቸዉም።

«የኢራን ተፅዕኖ ጥንካሬ የሚታየዉ በአሁኑ ይዞታ ለየትኛዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢራቅ ዉስጥ ለመመረጥ የኢራንን ቡራኬ ካላገኘ የማይታሰብ ነዉ። ይህም ማለት ግን የኢራን ተፅዕኖ ኢራቅ ዉስጥ ሁሉን ያጠቃለለ ነዉ ማለት አይደለም። ምክንያቱም ኢራቅ ከኢራኑ አያቶላህ ጋ ግንኙነት የሌላቸዉ በርካታ ሺአ መሪዎችን የሃይማኖትም ሆነ የሌላ ሊሆን ይችላል አስጠግታለች። ለምሳሌ አያቶላ ሲስታኒ ኢራቅ ዉስጥ የሚደረገዉን የኢራንን ተፅዕኖና ጣልቃ ገብነት በይፋ ይቃወማሉ። እሳቸዉ ደግሞ ከማሊኪ ዋነኛ ተቃዋሚዎች አንዱ ናቸዉ።»

Irak Haider Al Abadi nominiert als Premierminister Archiv 15.07.2014

ሃይደር አል አባዲ

ትናንት ማክሰኞ የኢራን ብሔራዊ የደህንነት ምክር ቤት የአካሄድ ለዉጥ እንደሚኖር ይፋ አድርጓል። ይህም ጠቅላይ ሚኒስትር ኑሪ አልማሊኪ በሌላ የሚተኩበትን ሁኔታ ለመርዳት ማለሙን ያመላከተ ነበር። አል ማሊኪ ባለፈዉ ሚያዚያ ከተካሄደዉ ምርጫ በኋላ የያዙትን ስልጣን ላለመልቀቅ እያንገራገሩ ነዉ። ሆኖም ዩናይትድ ስቴትስና ኢራን በግልፅ እሳቸዉን ወደጎን በማድረግ ድጋፋቸዉን ለምክትል ፕሬዝደንቱ ሃይዳር አል አባዲ ሰጥተዋል። የፓርቲያቸዉ አባል የሆኑት አል አባዲ መንግሥት እንዲመሠርቱ ትናንት የተሰጣቸዉን ሙሉ ድጋፍ አል ማሊኪ በይፋ ተቃዉመዋል። ሕገ መንግሥቱን መጣስ መሆኑን በመግለፅ፤ ጉዳዩ በፍርድ ቤት በመያዙም ዉሳኔዉ ከዚያ ስልጣናቸዉን እንደማይለቁ ዛሬ አስታዉቀዋል። ደጋፊዎቻቸዉ ወደኋላ እንዲሉ ያደረገዉም የእሳቸዉ ሌሎችን ያገገለ መንግሥት ምሥረታና የሙስሊም ታጣቂዎቹ ሶስት የኢራቅ ከተሞችን መቆጣጠር ነዉ። ኢራቅን ከሶስት አቅጣጫ የከፋፈለዉን የታጣቂዎቹን ግስጋሴ ለመግታትም አሜሪካ የአየር ድብደባ ጀምራለች። ጀርመንም በበኩሏ ወታደራዊ ድጋፍ ለኢራቅ ልትሰጥ የምትችልበት ሁኔታ እንዳለ አመላክታለች። ፈረንሳይም ደግሞ ከታጣቂዎቹ ጋ ለሚፋለሙት ኩርዶች መሣሪያ ለመስጠት መዘጋጀቷን ዛሬ አስታዉቃለች።

ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic